በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የታየው የአመራር ቁርጠኝነት የሚበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው!

ከፕሮጀክቶች ጋር የተያያዙ መልከ ብዙ ችግሮች የሀገር ፈተና ስለመሆናቸው በስፋት የተነገረለት ጉዳይ ነው። በዚህም እንደ ሀገር ሲባክን የነበረው ሀብት ግምቱ ከፍ ያለ ስለመሆኑም በጅምር የቆሙ፣ ተጀምረው ያላለቁ ፣ ብዙ ሀብት ፈሶባቸው ድምጻቸው የጠፋ ፕሮጀክቶችን ማስታወስ በቂ ነው።

አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች በአደባባይ ብዙ ተብሎላቸው፤ ከውጪ አበዳሪ ተቋማት ሳይቀር በሀገር እና በሕዝብ ስም በብድር ከፍተኛ ሀብት ፈሶባቸው የውሃ ሽታ የሆኑ ናቸው። እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስም የሀገሪቱን ልማት የሚፈታተን የዕዳ ጫና ምንጭ ሆነዋል።

አግባብ ያለው የአዋጭነት ጥናት እና የተሟላ የዲዛይን ዝግጅት አለመኖር፣ የተቋራጮች የአቅም ውሱንነት ፣ የበጀት እጥረት፣ የግብአት አቅርቦት ፣ የካሳ ክፍያ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለፕሮጀክቶች መዘግየት በዋንኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። ችግሮቹ ዘርፉን በከፋ መልኩ ለሙስና ተጋላጭ የማድረጋቸውም ነገር ማስረጃ ጥቀሱ የሚያስብል አይሆንም፡፡

በውስብስብ ችግሮች የሚፈተነውን ሀገራዊ የፕሮጀክት አፈጻጸም ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አዳዲስ አሠራሮች ተግባራዊ ሆነዋል፤ በዚህም በሀገሪቱ ተግባራዊ እየሆኑ ባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሳይቀር ተጨባጭ የሆኑ ስኬታማ የፕሮጀክት አፈጻጸሞች እየተስተዋሉ ነው።

ችግሩ ከነበረበት ስፋት እና ጥልቀት አኳያ አሁንም እንደ ሀገር ፈተና የመሆኑ እውነታ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ ገና ብዙ ፣ብዙ መሥራት የሚፈልግ ፣ መሠረታዊ የአስተሳሰብ እና የአሠራር ለውጥም የሚጠይቅ ነው። ከሁሉም በላይ የፖለቲካ አመራሩን ሁለንተናዊ ቁርጠኝነት የሚፈልግ ነው።

ከዚህ አኳያ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ጨረታ የወጣባቸው ሦስት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እና ስምንት የጥናትና ዲዛይን ጨረታዎች እንዲቋረጡ ያደረገበት መንገድ የሚበረታታ እና ተገቢው እውቅና ሊሰጠው የሚገባ የአዲስ እሳቤ ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአሁን በፊት የግንባታ ሥራዎች የሚመረጡበት፣ ውሳኔ የሚያገኙበትና ወደ ግንባታ የሚገቡበት መንገድ ግልጽ በሆነ ፍኖተ ካርታ የማይመራ መሆኑን ተገንዝቦ፤ አዲስ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ወደ ሥራ የገባበት መንገድም ችግሩን ለዘለቄታው በመፍታት እንደ ሀገር የተጀመረውን አዲስ የፕሮጀክት አፈጻጸም ባህልን ለማስፋት የሚያስችል ነው ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከደረጃዎች ኢንስቲትዩትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር ካዘጋጀው ስታንዳርድ በተጨማሪ በራሱ በኩል ያለውን ክፍተትም ተመልክቶ፤ ከአሁን በፊት በተቋሙ የሌለ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ቢሮ በመክፈት እያንዳንዱን ፕሮጀክት በቦታው ሆኖ የመከታተል ሥራ እየሠራ መሆኑም ተገቢው እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡

ጨረታ የወጣባቸው ሦስት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እና ስምንት የጥናትና ዲዛይን ጨረታዎች ስታንዳርድን ያልተከተሉ፤ ለጊዜ ብክነት፣ ለተጨማሪ ወጪና ለጥራት ጉድለት የሚዳርጉ መሆናቸውን አጥንቶ በእርምት እርምጃ ጨረታዎቹ እንዲሰረዙ ማድረጉም የአመራሩን ቁርጠኝነት ያመላከተ ነው።

“ፕሮጀክቶችን መቁጠር ብቻ ሳይሆን ወደ ውጤት መቀየር፤ ለረዥም ጊዜ ሀብት እየፈሰሰባቸውና ሕዝብ እያለቀሰባቸው ያሉ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለሕዝቡ ተስፋ መስጠት፤ አዲስ ፕሮጀክት ከመሥራትና አዲስ ሀብት ከማፍሰስ በፊት እስከ አሁን የፈሰሰውን ሀብት ወደ ውጤት ለመቀየር በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል” በሚል እየተጓዘበት ያለውም መንገድ ስህተቶቹን በማረም በቀጣይ ስኬታማ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መሠረት የሚጥል ነው።

ይህ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የታየው የአመራር ቁርጠኝነት፤ በተለይም ሀገሪቱ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ በመጠቀም ለጀመረችው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጉዞ ሆነ በቆላማ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ሕይወት ለመለወጥ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል!

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You