በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን የመከላከሉ ሥራ የጋራ ርብርብን ይሻል!

ሴቶች ፆታን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶች እና ጥቃቶች ይደርሱባቸዋል፡፡ እነዚህን ጾታዊ ጥቃቶችና አድሏዊ አሠራሮች ለማስወገድ በርካታ ዓለምአቀፍ ስምምነቶች እና ሀገር አቀፍ ሕጎች ቢኖሩም የሴቶችን መብቶች ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

እስከዛሬ በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች የተነሳ ጉልህ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ሙሉ በሙሉ የፆታ እኩልነትን ለማስመዝገብ ታላቅ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ በመቀጠል ላይ ነው። ሴቶች በተለያዩ የዓለም ሀገራት መድልዎ፣ ጥቃት፣ የትምህርትና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ውስንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ልዩነቶች ይደርስባቸዋል።

በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል የሚታይበት ቢሆንም፤ አሁንም በርካታ ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉት እሙን ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ የሴቶችን ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናና ከለላ እንዲኖረው በማድረግ ጭምር በከተማና በገጠር የሚኖሩ ሴቶች መብታቸው ተረጋግጦላቸው እንዲኖሩ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡

በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ መንግሥት እንደ አዲስ ባዋቀረው ካቢኔ ውስጥ 50 በመቶውን ሴቶች እንዲይዙ በማድረግ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ አርአያነት ያለው ተግባር ማከናወን ተችሏል፡፡

የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ የተሠራውም ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ከጤና ጋር በተያያዘም ‹‹አንድም ሴት በወሊድ የተነሳ አትሞትም›› በሚል ሴቶች የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

በመዲናችን አዲስ አበባም የሴቶች የተሐድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ተገንብቶ ወደ አገልግሎት መግባቱ የዚሁ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ማዕከሉ በዋነኛነት በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን በመቀበል ሙያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ፣ ክትትልና ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችል ሲሆን፤ በአንድ ዙር ብቻ 10 ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም ያለው ነው፡፡ “ለነገዋ” በሚል የተሰየመው ይኸው የሴቶች ተሐድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የሴቶችን እኩልነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ሚና ይኖረዋል፡፡

ሆኖም ሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ መሻሻሎች ቢታዩም አሁንም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ተበራክተው ቀጥለዋል፡፡ በተለይም ግጭት እና ጦርነት በሚታይባቸው አካባቢዎች ሴቶችን ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይሄዱ በማድረግ ፣ በመድፈር እና በመጥለፍ ጭምር የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ካለፈው ህዳር 16 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ ለአስራ ስድስት ቀናት የቆየ የጸረ ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ተካሂዷል፡፡ በዚሁ ንቅናቄ ወቅት እንደተገለጸው፤ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተበራክተዋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች በቅርብ ቤተሰብ፣ በአብሮ አደግ ጓደኛ ፣ በትምህርት ቤቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥቃቶች ደግሞ ከባህል እና አኗኗር ተጽዕኖ በተጨማሪ የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት ትኩረት ማነስ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ምርመራ አለማካሄድ፣ አጥፊዎችን በሚፈለገው መልኩ ወደ ሕግ ለማቅረብ እንቅፋት ሆነዋል፡፡

ስለዚህም በተለያዩ ደረጃዎች ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለማጥበብ እና አጥፊዎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ የሕግ ማሻሻያዎችን መተግበር፣ የትምህርት እና ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ማካሄድ፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ በማብቃት፣ ጤናን እና ደህንነትን በማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጎልበት የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማምጣት መሠራት አለበት፡፡ እያንዳንዷ ሴት መብቷን የምትጠቀምበት እና አቅሟን የምታሳይበት ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ግለሰቦች፣ ማኅበረሰቦች እና መንግሥታት በጋራ መትጋት አለባቸው፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ያስገባ የሕግ ረቂቅ እየተከናወነ መሆኑ እና የጥቃት አድራሽ ግለሰቦችን አድራሻ እና ማንነት የሚገልጽ ቴክኖሎጂ ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆኑ የሚያበረታቱና ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ተግባራት ናቸው!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You