የፋሽን ትዕይንቶች (ሾዎች) ባደጉት ሀገራት የተዘጋጁ አልባሳትና ጌጣጌጦችን ከማሳየት አልፈው ብዙ ርቀው ሄደዋል:: የፋሽኑና የመዝናኛው ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በሚዘጋጁ የፋሽን ትዕይንቶች ላይ ለመታደም አሕጉር አቋርጠው ሲጓዙ ማየት ተለምዷል:: በተለይ የፈረንሳይዋ ፓሪስ፣ የጣልያኗ ሚላን የአሜሪካኗ ኒውዮርክና የእንግሊዟ ለንደን ከተሞች የሚዘጋጁትና በከተሞቹ በተሰየሙት የፋሽን ሳምንታት መሳተፍ ለፋሽኑ ዘርፍ ባለሙያዎች ትልቅ ትርጉም አለው:: ከተሞቹ ያን ሰሞን በጎብኚ ይጨናነቃሉ:: የፋሽን ኢንዱስትሪው ገበያ ይደራለታል::
በፋሽን ሳምንታቱ ማን ሥራውን አቀረበ?፤ የትኛው ታዳሚ ተገኘ?፤ የትኛው መገናኛ ብዙኃን ምን ዘገበ?፤ የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የትኛውን ልብስና ጫማ ተጫሙ?፤… ብቻ ብዙ ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ይነሳሉ::
ታዲያ በየመድረኩ ሥራቸውን የሚያቀርቡ ዲዛይነሮች፣ በመድረኩ ሽር ብትን የሚሉ ሞዴሎች፤ የተመረቱትን ምርቶች ገዝተው ለቀጣይ የሚሸጡ ነጋዴዎች፤ የመድረክ ገጽ ግንባታ ባለሙያዎች፤ በመድረኩ ሥራቸውን የሚያቀርቡ የሙዚቃ ባለሙያዎች፤ መድረክ መሪዎች፤ የአልባሳትና የጌጣጌጥ አምራች ፋብሪካዎች በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ከሚሆኑት ባለፈ በፋሽን ሾው የቀጥታ ተጠቃሚ ከሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው:: ከዚህ በተጨማሪ የተሠራውን አይተው፣ በመስኩ ለመሠማራት የሚነሳሱ በርካቶች ሲሆኑ ለእንግዶቹ አገልግሎት በመስጠት (የሆስፒታሊቲ ዘርፍ) በርካቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ::
በሀገራችንም የፋሽን ትዕይንቶች ሲዘጋጁ ማየት የተለመደ ቢሆንም ከተወሰኑት በስተቀር ቋሚ ጊዜ የላቸውም:: ዲዛይነሮቹ ሲሞላላቸው ይዘጋጃል፤ ሳይሆን ሲቀር ይቀራል:: በሀገራችን በዘርፉ ካለው የተለየ አልባሳት፤ የጥሬ እቃ ሀብት፤ የባሕል አልባሳት ስብጥር አንጻር መጠቀም ያለብንን ሳንጠቀም ቆይተናል:: ይህን ክፍተት ከመሙላት አንጻር የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት የሚችል የፋሽን ሳምንት ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ‹‹አዲስ ፋሽን ዊክ›› በሚል ስያሜ ተዘጋጅቷል:: የፋሽን ትዕይንቱ በሜሊስ ፋሽንና በብሊንግ ኤቨንትና ኢንተርቴመንት የተዘጋጀ ነው::
ሜሊስ ፋሽን የዓለም አቀፍ ልምድ ባላት ዲዛይነርና ሞዴል ሜላት ሚካኤል እ.አ.አ በ2020 የተመሠረተ የፋሽን ድርጅት ነው:: ድርጅቱ በቻይና በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ ሱቆች ጋር በአጋርነት እንደሚሠራ የፋሽን ሳምንቱን መዘጋጀት አስመልክቶ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል:: በዘርፉ ከአስር ዓመት በላይ ልምድ እንዳላት የተገለጸ ሲሆን በመድረኩ ከ40 በላይ የሚሆኑ በዲዛይነሯ የተሠሩ ልብሶች ይቀርባሉ:: የፋሽን ሳምንቱን በአጋርነት ያዘጋጀው የብሊንግ ኤቨንትና ኢንተርቴመንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ብሊንግ ጎይትዖም በመድረኩ ፋሽንን ከቴክኖሎጂ ጋር አጣምረው ለማቅረብ መነሳታቸውን ይገልጻል::
የፋሽን ዲዛይነሯ በተለያዩ ሀገራት የቀሰመችውን ልምድና ተሞክሮ ይዛ ወደ ሀገሯ መግባቷንና በሥራዋ የሀገሯን ባሕል ከዘመናዊ ጋር በማዋሓድ ለዓለም ለማስተዋወቅ ስትነሳ፤ በሀሳቡ በመስማማታቸው አብረው እየሠሩ መሆኑን አስረድቷል:: መድረኩ ፋሽን በኢትዮጵያ እንደሚጠቅም የምናሳይበት ኢትዮጵያን እንዴት እናስተዋውቅ ብለን የተለየ ነገር ይዘን የመጣንበት ነው ብሏል ዳይሬክተሩ::
እንደ ብሊንግ ማብራሪያ፤ የፋሽን ትርዒቱ ከመድረክ ግንባታ፣ ከድምፅ፣ ከላይት አጠቃቀም ጀምሮ እስከዛሬ በሀገራችን ከተለመዱ የፋሽን ትርኢቶች በተለየ መልኩ ለመምጣት የተዘጋጁበት ነው:: ዝግጅቱ ላይ ለሚታደሙ ሰዎች የተሰራጨው የመጥሪያ ካርድ በተለየ መንገድ ዲጂታል ካርድ ተጠቅመዋል:: ተጋባዦች የጥሪ ካርዱን ሲከፍቱ ከሚነበብ ጽሑፍ ይልቅ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለዝግጅቱ እንዲታደሙ ጥሪ የምታስተላልፍ ሞዴል የቪድዮ መልዕክት ይጠብቃቸዋል:: የዘመኑ ሴቶች ውበት መጠበቂያ የሆነው ጥፍር የፋሽን ሾው አካል ሆኗል:: ጥፍሩ ‹‹በቺፕ›› መልክ የተዘጋጀ ሲሆን ጥፍሩን የሚጠቀሙ ሴቶች የግላቸውን መረጃ ለአብነት የስልክ ቁጥር የማኅበራዊ ድረ ገጾች ከስልካቸው ጋር በመገናኘት በቀላሉ መረጃዎችን ይይዛል:: የጥፍሩ ‹‹ቺፕ›› በመድረኩ ለታዳሚዎች ይሰጣል::
እንደ ዲይዛነሯ ማብራሪያ፤ በአዲስ ፋሽን ሳምንት ላይ ከ40 በላይ በዲዛይነሯ የተዘጋጁ ልብሶች ይቀርባሉ:: በመድረኩ ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ ተሰጥዖ እያላቸው ዕድሉን ያላገኙ ሞዴሎች በዲዛይነሯ የተዘጋጁ ልብሶችን ለብሰው በመድረኩ ይዋባሉ:: ፋሽን ትዕይንቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፤ በመድረኩ የባሕል መሣሪያ በተለይ በመሰንቆና በክራር የታጀበ ነው:: የባሕል አልባሳታችን የክት ልብስ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአዘቦት ጥቅም ላይ ለማዋል ምቹ ሆነው መዘጋጀታቸው ተነግሯል::
የፋሽን ዲዛይነሯ ለኢትዮጵያ መድረክ አዲስ ስለሆነች የአሁኑ ሥራዎቿን ለማስተዋወቂያ በአንድ ቀን ቢጠናቀቅም፤ በቀጣይ በየስድስት ወሩ የሌሎች ፋሽን ዲዛይነሮች ሥራ በመቀላቀል ይዘጋጃል:: ዲዛይነር ሜላት በተለይ ተሰጥዖ እያላቸው ዕድል ያላገኙ ወጣት ዲዛይነሮችን በማካተት ለዓለም ገበያ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት እድል ለማመቻቸት እንደሚሠሩ ተናግራለች:: ያኔ የበርካታ ዲዛይነሮች ሥራ ሲካተት ልክ እንደስሙ የፋሽን ሳምንት ይሆናል::
በሀገራችን ነገሥታት ከወርቅ የተሠሩ ዘውድ፣ ጫማዎች እንደነበሯቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሙዚየሞች አስረጂ ናቸው:: በቀደመው ጊዜ ኑሮ የሞላላቸው ወርቅን የማጌጫ አይነት ከማድረግም ባለፈ የቀሚሳቸው ማስጌጫ ነበር ሲባል በታሪክ ሰምተናል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን ለመመለስ በምትሠራቸው ልብሶች ላይ በትእዛዝ በወርቅና በብር የምታስውብ ዲዛይነር ተመልክተናል:: ታኅሣሥ አራት በሚካሄደው አዲስ ፋሽን ዊክ ላይ ደግሞ አንድ ምዕራፍ ተሻግሮ ሁለት በአልማዝ የተሠሩ መኖራቸው ተጠቁሟል::
የፋሽን ሳምንቱ ታኅሣሥ አራት ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ላይ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ይጀመራል:: በዕለቱ ወጣቷ ድምፃዊ ዊሃ የሙዚቃ ሥራዋን ታቀርባለች:: ድምፃዊቷ በዲዛይነሯ የተዘጋጁትን ልብሶች ለብሳ የሙዚቃ ሥራዋን የምታቀርብና ልብሶቹን የምታስተዋውቅ ይሆናል:: ዝግጅቱ ያለምንም ክፍያ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመጥሪያ ካርድ የሚታደሙበት መሆኑ ተነግሯል::
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም