ዛሬ ላይ ሆነን እነ እገሌ ዲግሪያቸውን ሊቀበሉ ነው የሚል ዜና ብንሰማ ውሃ የማያነሳና ለጆሮ የሚጎረብጥ ከመሆኑም በላይ እንደ እብደትም እንቆጥረው ይሆናል። ይህ ግን በአንድ ወቅት ትልቅ ዜና፤ ግዙፍ ርዕሰ ጉዳይም ነበር። ዛሬም በድሮው የሀገራችን የዘመን ምዕራፎች ውስጥ ስንሰነብት፤ በዋናነትም ሀገራዊና አህጉራዊ ሁነቶችና ታሪካዊ የሆኑ ጉዳዮችን እናገኛለን። ከእነዚህም ዲግሪ ሊቀበሉ ነው፤ የ46 ሚሊዮን ብሩ የኢትዮጵያ መርከብ፤ ኮንትሮባንዲስቷ አህያን ጨምሮ በአህጉራዊ ጉዳዮች ደግሞ፤ ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ መሠረት በሆነው የአፍሪካ የነጻ መንግሥታት ጉባኤ፤ ግርማዊነታቸው ጋዜጠኞቹን አስደሰቱ፤ እነዚህና ሌሎችም በርከት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በማካተት ትውስታ አቅርበናል።
ዲግሪ ሊቀበሉ ነው
ሦስት ኢትዮጵያውያን መምህራኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ትምህርት በዚህ ዓመት መጨረሻ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የቢ ኤ ዲግሪ ሊቀበሉ የተዘጋጁ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የትምህርት ክፍል ዳይሬክተር፤ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ በሰጡት ወሬ ገልጸዋል።
የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዋነኛ ቋንቋ በሆነው በአማርኛ ትምህርት፤ የቢ ኤ ዲግሪያቸውን ለመቀበል የታደሉት የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያንም፤ አቶ አምደ ሥላሴ ጀምበሬ፤ አቶ ክንፉ ዱሬሣ፤ አቶ ደምሴ ማን አህሎት የተባሉት በኮሌጅ አራተኛ ክፍል የመምህርነት ትምህርት የሚከታተሉ ወጣቶች ናቸው።
(አዲስ ዘመን ሰኔ 12 ቀን 1952ዓ.ም)
46 ሚሊዮን ብር የተገዛው መርከብ ሥራ ጀመረ
ምፅዋ፤(ኢ.ዜ.አ) ኢሠፓና አብዮታዊው መንግሥት የኢትዮጵያን የውጭ ንግድና የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ለማስፋፋትና ለማጠናከር በቀየሱት መርሐግብር መሠረት በ46 ሚሊዮን ብር የተገዛው አንድ ዘመናዊ የንግድ መርከብ ትናንት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
“አንድነት” የተባለውና ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ሰማንያ ፈረስ ጉልበት ያለው ይኸው ዘመናዊ መርከብ የናቪጌሽንና ሌሎችም መሣሪያዎች፤ 4 ባለ 12.5፤ 2 ባለ 20 እና 1 ባለ 5 ቶንስ የመጫኛና የማራገፊያ ክሬኖች ያሉት ሲሆን 10ሺህ 886 ቶንስ እቃ ለመጫን የሚችል መሆኑ ታውቋል።
(አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 1979ዓ.ም)
አህያ የኮንትሮባንድ እቃ ጭና ተያዘች
ባለቤትነቷ የማን እንደሆነ ያልታወቀች አንዲት አህያ፤ ግምቱ አንድ ሺ አምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ብር የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተጭና ጨረቲ ከተባለው ቀበሌ በፊናንስ ፖሊሶች ተያዘች።
ኮንትሮባንዲስቷ አህያ ፤ ማንነቷን ለማጣራት ተይዛ የጫነችው እቃ በተመረመረ ጊዜ፤ ቀረጥ ያልተከፈለበት አሥራ ሦስት ጣቃ ናይለን ጨርቅና ዘጠና ስምንት እስቴካ ሮዝማንስ ሲጋራ ይዛ መገኘቷን የከሚሴ የፊናንስ ፖሊስ አዛዥ ሻምበል ሰብሉ ክብረት ገልጠዋል።
ወዲያው አህያዋ ቀረጥ ካልተከፈለበት ጭነቷ ጋር ይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ፍርድ ቤት ቀርባ፤ ከነጭነቷ ለመንግስት በውርስ ስም ገቢ የተደረገች መሆኗን የፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ አቶ አበበ ኦዳ ገልጠዋል።
(አዲስ ዘመን ነሀሴ 12 ቀን 1962 ዓ.ም)
ሁለተኛው የአፍሪካ ነጻ መንግሥታት ጉባኤ
ከ9 ቀን ስብሰባ በኋላ መፈጸም
አሥራ ሁለት ቀኖች ያህል የግልና የይፋ ስብሰባ በማድረግ ላይ ሰንብቶ የነበረው፤ ሁለተኛው የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት ጉባኤ የሥራ ውጤት በሦስት ምድብ አማካይነት ከሰማና በእያንዳንዱ ድምፅ አንቀጽ ከሰጠ በኋላ በክቡር ፕሬዝዳንቱ አማካይነት ሰኔ 18 ቀን 1952ዓ.ም ተዘግቶአል።
(አዲስ ዘመን ሰኔ 19 ቀን 1952ዓ.ም)
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ከየሀገሩ ለመጡ ጋዜጠኞች ፕሬስ ኮንፈረንስ ስለማድረጋቸው
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ሰኔ 17 ቀን 1952ዓ.ም ከእኩለ ቀን በላይ 10 ሰዓት ተኩል በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥታቸው ላይ ተገኝተው አዲስ አበባ ላይ በተከፈተው የአፍሪካ ነጻ መንግሥታት ጉባኤ ላይ የጉባኤውን ሁኔታ ለመመልከት ከየሀገሩ የመጡትን 38 ጋዜጠኞችን ተቀብለው ፕሬስ ኮንፈረንስ አድርገውላቸዋል።
በዚህም ጊዜ እያንዳንዱ ጋዜጠኛ እየተነሳ ስለ አፍሪካ ነጻ መንግሥታት ጉባኤና በጠቅላላው አፍሪካን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች ግርማዊነታቸው ያላቸውን አስተያየት እንዲገልጹላቸው ላቀረቡላቸው ጥያቄ አጥጋቢ የሆነ መልስ በመስጠት አስደስተዋቸዋል።
(አዲስ ዘመን ሰኔ 18 ቀን 1952ዓ.ም)
አዲስ ከተማ መቆርቆር
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ለሕዝባቸው የኑሮ መሻሻልና ለሀገራቸው ልማት ባቀዱት የአምስት ዓመት ፕላን መሠረት በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ባሕርዳር ላይ አንድ ከተማ እንዲሠራ ትእዛዝ ሰጥተው የከተማው ፕላን ተሠርቶ ለከተማው ውበትና በከተማው ውስጥ ለሚኖረው ሕዝብ ምቾት የሚያስፈልጉት ልዩ ልዩ የዘመናዊ ከተሞች ዕቅዶች በመጠናትና በመሠራትም ላይ ይገኛሉ።
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 23 ቀን 1952ዓ.ም)
መገናኛዎች
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ የሕዝባቸውን ችግር ማስወገድ የዘወትር ተግባራቸው በመሆኑ በሸዋና በጎጃም ጠቅላይ ግዛቶች ካንዱ ወዳንዱ የሚሔደው ሕዝባቸው ታላቁን የዓባይ ወንዝን በሚሻገርበት ጊዜ በውሀው ኃይልና በውሀው ውስጥ በሚገኙት አዞዎች በሚደርስበት አደጋ የገጠመውን ጉዳት በመመልከት፤ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የፈጀ ታላቅ የሆነ ዘመናዊ ድልድይ አሠሩለት።
….
እንዲሁም ደግሞ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት አዲስ በሚሠራው ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ አንድ ኤንተርናሽናል የሆነ ታላቅ ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ እንዲሠሩ ታቅዶ ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ጥናቱ በሚያስቸኩል በመራመድ ላይ ይገኛል።
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 23 ቀን 1952ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም