አዲስ አበባ፡- በሲዳማ ክልል ከመኸር እርሻ ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለጸ፡፡ በበጋ መስኖ ልማትም ከ11 ሚሊዮን በላይ ኩንታል የሆርቲካልቸር ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁሟል፡፡
የሲዳማ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ መምህሩ ሞኬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን በዋና ዋና ሰብሎች ከለማው 106ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡
የእርሻ ግብዓት አጠቃቀም፣የማሳ እንክብካቤ አና የሰብል ጥበቃ ስራዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ መሰራታቸውን ተናግረው፤የመኸር ሰብል ብዙ ጊዜ ለተባይ እና ለበሽታ የተጋለጠ በመሆኑ ተጋላጭነት ለመቀነስ ከመጀመሪያው ጀምሮ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሲዳማነት የተጋለጡ ቦታዎች 35 ሺህ ኩንታል ኖራ በመኸር እርሻ ጥቅም ላይ መዋሉን አውስተው፤ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ከሚውለው 12ሺህ ኩንታል ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ልዩነት እንዳለው አውስተዋል፡
ሥራዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሰሩ በመሆኑ እና ያጋጠሙ ችግሮችን መቆጣጠር በመቻሉ የታቀደውን ያህል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት የቢሮ ኃላፊው፤ ከታህሳስ ወር መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ጥር ወር ድረስ ለሚዘልቀው የመኸር ምርት አሰባሰብ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ስነ ምህዳር አቀማመጥ ከፍ ያለ በመሆኑ ትልልቅ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖችን ማስገባት የማይመች በመሆኑ በእጅ የሚጎተቱ አነስተኛ የሰብል መውቂያ ማሽኖች እንዲገቡ መደረጉን ያመላከቱት የቢሮ ኃላፊው፤ 30 የሰብል መውቂያ ማሽኖች በ15 ወረዳዎች የማሰራጨት ስራ መሰራቱን አመላክተዋል፡፡ 15 የወጣት ማህበራት ለስራው መዘጋጀታቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡
ጎን ለጎን በተጀመረው የበጋ መስኖ ሥራም በሆርቲ ካልቸር ምርቶች ላይ በትኩረት ለመስራት መታቀዱን ጠቁመው፤ በዓመቱ ከ72ሺ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ እንደሚለማ እና እስካሁን ከ22ሺ በላይ ሄክታር መሬት መልማቱን ጠቁመዋል፡፡
ለበጋ መስኖ ልማቱ አቅም ሊፈጥሩ የሚችሉ ከሁለት ሺህ 200 በላይ የውሃ ፓምፖች ከዚህ በፊት መሰራጨታቸውን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊው፤ በዚህ ዓመት እጥረት ላለባቸው ወጣቶች እና ማህበራት 130 የውሃ ፓምፖች መሰራጨታቸውን አስረድተዋል፡፡
በበጋ መስኖ ልማት ከሚለማው 72ሺህ ሄክታር መሬት ከ11 ሚሊዮን በላይ ኩንታል የሆርቲካልቸር ምርቶች ለመሰብሰብ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡
በመስኖ በሚለማባቸው አካባቢዎች ብዙ ጊዜ በኩታ ገጠም እንደሚለማ ተናግረው፤ ከ80 በመቶ በላይ የመስኖ ገብ ማሳዎች በኩታ ገጠም እንደሚለሙ ተናግረዋል፡፡
ወቅቱ ምርት የሚሰበሰብበት በመሆኑ አርሶ አደሩ ምርት ሳይባክን የተለያዩ አካላትን በማስተባበር በጥንቃቄ እንዲሰበስብ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም