የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው ፈተናዎች

ዜና ትንታኔ

ሀገራት ወደ ውጭ የሚልኩት ምርትና ከውጭ የሚያስገቡት ምርት መመጣጠን እንደሚገባው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ቀርፃ የሀገር ውስጥ ፍጆታን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየሰራች ትገኛለች። በስትራቴጂው ቅድሚያ የተሰጠው ደግሞ የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ነው፡፡ በዚህ ረገድ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው ተስፋ ሰጪ እምርታ ቢታይበትም ፈተናም ተጋርጦበታል።

በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ አላምረው አያልነህ፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 30 በመቶ የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ወደ 60 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዞ ያለፉትን አራት ዓመታት እየተሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በዚህም ጥረት ተስፋ ሰጪ እምርታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አላምረው ገለጻ፤ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ አራት የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች ተለይተው ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት እየተደረገ ነው። እነሱም የሀገር መከላከያና የሌሎች የጸጥታ አካላት አልባሳት፣ የተማሪ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም)፣ የጅንስ ጨርቅና የጤና(ሜዲካል) ጋውን ናቸው፡፡

አሁን ላይ የሜዲካል ጋውን ፍላጎትን መቶ በመቶ በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ተችሏል። 96 በመቶ የጸጥታ ኃይል አልባሳትንም በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል። በእነዚህ አራት ምርቶች የተጀመረው ስትራቴጂክ ተኪ ምርት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳን ተችሏል። በአራቱ ምርቶች የተገኘውን ውጤት መነሻ በማድረግም አጠቃላይ የሀገሪቱ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ተነድፏል ነው ያሉት፡፡

በስትራቴጂው 98 ያህል ምርቶች የተለዩ ሲሆን፤ በ2016 ዓ.ም 34 የጨርቃጨርቅ ምርቶች መመረት የሚችሉ መሆናቸውን በመለየት ወደ ተግባር ተገብቷል። ከዚህ ውስጥ በአጭር ጊዜ ሊተኩ የሚችሉ 15 የምርት አይነቶችን በመለየት የሦስት ዓመት የስትራቴጂው ማስፈጸሚያ መርሃግብር ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መሸጋገሩን ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል።

የጨርቃጨርቅና አልባሳትን ፍላጎት በሀገር ውስጥ የመተካት ጉዳይ ሲታሰብ አንዱ ፈተና በሸማቹ ዘንድ ያለው የተዛባ አስተሳሰብ ሲሆን፣ ሌላው በምርቶቹ ጥራት ላይ የሚነሳው ጥያቄ ነው። “በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ቃል ባለፉት ዓመታት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጨርቃጨርቅና አልባሳትን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከፍተኛ ሚና ነበረው ይላሉ፡፡

እንቅስቃሴው ለሀገሩ ምርት የተሻለ እይታ ያለው ሸማች እንዲፈጠር እንዲሁም አምራቾች እንዲበረታቱ ማድረጉን ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ። እንዲሁም፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ሲታሰብ ለገበያ የሚቀርቡት ምርቶች ጥራት ሊጠበቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አላምረው ማብራሪያ፤ ሳይንሱ በጥራት ማምረት ወጪ እንደሚቀንስ ያስቀምጣል። ይህም በተግባር የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ በአምራች ኢንዱስትሪዎች አካባቢ “የተሻለ ጥራት ያለው ምርት ቢመረት ብዙ ወጪ ስለማይወጣበትና ገበያው ይሄንን መሸከም አይችልም” በሚል በዝቅተኛ ጥራት አምርቶ ማቅረብ ይሻላል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤና አመለካከት ይታያል፡፡ ይሄ ሊስተካከል የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ከሚከናወኑ ሥራዎች አንዱ ጥራትን ማምጣት የሚያስችሉ ሥልጠናዎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ።

በየዓመቱ ከሁለት ሺ በላይ የኢንዱስትሪ ሠልጣኞችና ኢንዱስትሪውን የሚደግፉ አካላት በማእከሉ ሥልጠና እንደሚያገኙ የሚገልፁት አቶ አላምረው፤ ጥራት ያለው ጥሬ እቃ ከመምረጥ አንስቶ ጨርቃጨርቅና አልባሳት ተመርቶ ለተጠቃሚው እስከሚደርስ በምን መንገድ ጥራትን ማስጠበቅ እንደሚቻልና መሰል ሥልጠናዎች በማዕከሉ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

እንደ ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የኢንዱስትሪው ሌላ ፈተና ከንግድ ምልክትና ስያሜ(ብራንዲንግ) ጋር የተያያዘ ነው። ይህን ሲያብራሩም በብዙ ሀገራት አምራቾች ከጅምሩ የራሳቸውን ብራንድ ይዘው ወደ ገበያው እንደሚገቡ ያስረዳሉ። በዚህም የሀገር ውስጥ ድርሻቸውን አስፍተው በቀጣይ ታዋቂ ብራንድ ሆነው የሚወጡበትን የረዥም ጊዜ እቅድ በመንደፍ ይንቀሳቀሳሉ፡፡

“በሀገራችን ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች ረገድ ያልተሰራበት አንዱ ይሄ የብራንዲንግ ጉዳይ ነው” የሚሉት አቶ አላምረው፤ በሌሎች ሀገራት የታወቀና ስሙን ያስተዋወቀን ብራንድ አስመስሎ በመስራት በአጭር ጊዜ ትርፍ ለማግኘት የማሰብ አዝማሚያ መኖሩን ይናገራሉ። በዚህም የራስን ስም ከመትከል ይልቅ የታወቁ ብራንዶችን አመሳስለው በመስራት ገበያ ላይ የሚታዩ አልባሳት መኖራቸውን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

“ይሄ አካሄድ ኢንዱስትሪውን በዘላቂነት አያሻግርም” የሚሉት አቶ አላምረው፤ ከኢንዱስትሪ ፖሊሲውም ሆነ በተኪ ምርት ስትራቴጂ ከተያዘው የሀገር ውስጥ ምርትን የገበያ ድርሻ ማሳደግ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ አምራቾች የራሳቸው የሆነ ብራንድ በመፍጠር ወደ ገበያው የሚገቡበትና የሚያሸንፉበትን ረዥም ራዕይ ኖሯቸው መስራት እንዳለባቸው ይመክራሉ። ለዚህ በራሳቸውም ብራንድ ምርታቸውን ለገበያ አቅርበው ውጤታማ የሆኑ የሀገር ውስጥ አምራቾችን እንዳሉ ማስተዋል ይገባል ባይ ናቸው።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ መምህር እያሱ ፈረደ እንደሚናገሩት፣ የሀገር ውስጥ አልባሳት የግብዓትና መሰል ችግሮች ጥራት ማጓደላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ሸማቾች ለሀገር

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You