የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የአካል ጉዳተኞች አካቶ ትግበራ

ዜና ሐተታ

የአካል ጉዳተኞችና ዓይነስውራንን ቁጥር በተመለከተ በኢትዮጵያ የተሰራ የቅርብ ጥናት ባይኖርም፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ እንደሚኖሩ ይጠቁማሉ። ይህ ቁጥር ከበርካታ ሀገራት አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር የበለጠ ነው። ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን ቁጥር ያህል በበርካታ ጉዳዮች በቂ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ማለት አይቻልም።

በሁሉም ዘርፍ አካታች ስራዎች በበቂ ሁኔታ እንዳልተሰሩ የአካል ጉዳተኛ ማህበራትና በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚሰሩ የተለያዩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በብዙ አጋጣሚዎች ቅሬታ ያቀርባሉ። እነዚህን ቅሬታዎች ሙሉ በሙሉ የሚቀርፉ ባይሆኑም የአካል ጉዳተኞችን ጥያቄ ለመመለስ እንደሀገር የተሰሩና እየተሰሩ የሚገኙ ጥረቶችም ጥቂት አይደሉም።

አዲስ አበባን ጨምሮ በአብዛኞች የኢትዮጵያ ከተሞች በሚገነቡ ህንጻዎች፣ መንገዶች፣ አሳንሰሮች፣ ትራንስፖርትና ሆስፒታሎች ውስጥ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሰረተ ልማቶችን ከመስራት አኳያ ጥሩ ጅምሮች ቢኖሩም ብዙ ይቀራል። የአዲስ ህይወት ዓይነስውራን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አጸባዩሽ አበበ፣ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው የሚሰሩት የመሰረተ ልማት ስራዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ጥሩ ቢሆኑም በሁሉም ቦታ ወጥ እንዳልሆኑ፤ ለዚህም አብዛኞቹ መሰረተ ልማቶች በሚገነቡበት ወቅት በአሳንሰሮች፣ ሆስፒታሎችና መንገዶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹና አስፈላጊው መስፈርት አለመሟላታቸውን እንደማሳያ ያነሳሉ ።

ችግሩን በምሳሌ ሲያብራሩም፣ በህንፃ መግቢያዎች፣ አሳንሰሮችና ሌሎች መወጣጫዎች ሁሉንም የአካል ጉዳት ያማከሉ ምልክቶች አለመኖራቸውን ይጠቁማሉ። በዚህም ምክንያት በቅርቡ ከሰባተኛ ወለል ላይ ወድቆ ህይወቱ ያለፈ ዓይነስውር መኖሩን ያስታውሳሉ።

በከተሞች አካባቢ በዋና መንገዶች ዙሪያ ጭምር ለተለያየ ግንባታና መሰረተ ልማት ስራዎች ተቆፍረው በአግባቡ ያልተደፈኑ በርካታ ጉድጓዶች መኖራቸውን የሚጠቁሙት ሥራ አስኪያጇ፣ ይህ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየቀነሰ እንደሚገኝ፤ ችግሩ ግን አሁንም ለዓይነስውራን ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ።

የሰርቫይቫልስ፣ ሪከቨሪና ሪሃብሊቴሽን ኦርጋናይዜሽን መስራችና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በቀለ ጎንፋ በበኩላቸው፤ የአካል ጉዳተኞችን እንቅስቃሴዎች ምቹ ለማድረግ እንደሀገር አዋጆች መኖራቸውንና ኢትዮጵያም ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞችን ኮንቬንሽኖችን መፈረሟን በማስታወስ፣ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች አማካኝነት አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ በየጊዜው ደንቦችና መመሪያዎች እንደሚወጡ ያብራራሉ፡፡

እነዚህ ደንቦችና መመሪያዎች የሚገነቡ ህንጻዎች፣ መንገዶችና ድልድዮች አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ እንዲያደርጉ የሚያስገድዱ ናቸው። ይሁን እንጂ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሚደረገው ጥረት በቂ ነው የሚል እምነት የላቸውም። እንደ አቶ በቀለ ገለፃ፣ አሁን ላይ ከሚሰሩት መሰረተ ልማቶች ጋር ተያይዞ ከአካል ጉዳተኝነት አንፃር ብዙ ፈተናዎች አሉ። በከተሞች በሚካሄዱ በርካታ የህንጻ ግንባታ ስራዎች የአካል ጉዳተኞች መወጣጫዎች (ራምፖች) በአግባቡ እየተሰሩ አይደሉም። የሚሰሩትም ቢሆኑ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ወይም ለይስሙላ የሚሰሩ ናቸው።

መንግሥት በዚህ ረገድ ለህንጻዎች የአገልግሎት ፍቃድ በሚሰጥበት ወቅት እንዲህ አይነት ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚስተካከሉበት መንገድ መፍጠር አለበት። እነዚህን ችግሮች ለማቃለልም በቀጣይ አካል ጉዳተኞችን በተገቢውና ትክክለኛ መንገድ የሚያካትት ስራ ሊከናወን ይገባል ሲሉም ይናገራሉ።

አካል ጉዳተኞች ምቹ ባልሆኑ መሰረተ ልማቶች የሚደርስባቸውን ጉዳትና ጫና ለመቀነስ እንዲሁም ከተደራሽነት አኳያ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣ ህንጻዎችና ትራንስፖርት ላይ ማህበራቸው ጥናቶች እንደሚሰራ ወይዘሮ አጸባዩሽ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም አካል ጉዳተኞችና ዓይነስውራን በሚሰሩባቸውና በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ከትራንስፖርት፣ ከመንገድ፣ ከሚሰሩበት ቦታ ጋር አመቺ አለመሆን ጋር ብዙ ፈተናዎችን እንደሚጋፈጡ ከጥናቶቹ ግኝቶች መገንዘብ እንደሚቻል ያመለክታሉ።

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ኅብረተሰቡ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የነበረው የተዛባ ግንዛቤ እየተቀየረ መምጣቱን ፣ በኢኮኖሚ ረገድ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ግን አሁንም ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩት ይናገራሉ፡፡ የአካል ጉዳተኞችን አካቶ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም ማህበረሰብና መገናኛ ብዙኃን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ በቀለ አስተያየት፣ በየትኛውም መንገድ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የወጡ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ኮንቬንሽኖችን ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ከመሰረተ ልማት አኳያ ደረጃዎችና አሳንሰሮች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ በሆነ መልኩ እንዲሰሩ ለመሐንዲሶችና ህንጻ ተቋራጮች ግንዛቤ ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ቅጣው፣ ቢሮው በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተሳታፊነትና አካታችነት ላይ እንደሚሰራ ይናገራሉ። በዚህም ሁሉንም የከተማ አስተዳደር ቢሮዎችን ከአካታችነት አንጻር ጠያቂ፣ ድጋፍ ሰጪና የተሰጣቸውን ኃላፊነት የማይፈጽሙትን ተጠያቂ የማድረግ ስራ እንደሚያከናውን ያብራራሉ። በተጨማሪም በከተማው የሚገነቡት መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ከከተማው ፕላን እና ዲዛይን ቢሮ ጋር እየሰራ ድጋፍ፣ ክትትልና እርማት እንዲደረግ በጥናቶች ላይ ተመስርቶ ምክረ ሃሳብ ይሰጣል።

እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅት በከተማው በሚገነቡት ህንጻዎች ራምፖችና አሳንሰሮችን እንዲያካትቱ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች የሚያስፈልጉትን መሰረታዊ ነገሮች የማያሟሉት ላይም በተቀመጠው የአሰራር ደንብና መመሪያ መሰረት ተጠያቂ ይደረጋሉ። አሁን በከተማዋ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ቢሮዎች ለአካል ጉዳተኞች የተሻለ አካታችና ምቹ መሆናቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት፣ ከዚህ በፊት የተገነቡት ህንጻዎች ጭምር ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማድረግ ስራዎች እየተከናወነ ነው።፡ አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሙያና ስልጠና ማዕከላት ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡም የሚያስችሉ ስራዎች አሉ።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You