‹‹በሀገር አቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄ የተገኙ ስኬቶችን ቀጣይ ለማድረግ እንሰራለን››- ክልሎች

አዲስ አበባ፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ ‹‹ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ›› በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የብክለት መግቻ ንቅናቄ የተገኙ ስኬቶችን ቀጣይ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች አስታወቁ፡፡

የኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ዘርፍ የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ በፈቃዱ እንደሚገልጹት፤ ሀገር አቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄው ዋነኛ ዓላማ የዜጎችን በጤናማ አካባቢ የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብት ማስከበር፣ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ነው። እንዲሁም ኅብረተሰቡ ስለ አካባቢ ጥበቃ፣ ብክለትና ብክነት ምንነት፣ የመከላከያና የማስወገጃ መንገዶች ላይ ግንዛቤውን እንዲያጎለብት ማድረግ ነው።

በንቅናቄው በየወሩ የፕላስቲክ፣ የአየር፣ የውሃ፣ የአፈርና የድምፅ ብክለት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ያመላከቱት አቶ ስንታየሁ፤ በኦሮሚያ ክልል ማኅበረሰቡን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትንና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በሁሉም ዞኖች ከተሞች እስከ ታችኛው አስተዳደር እርከን ድረስ በተናበበ ሁኔታ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ ንቅናቄ መድረኮች በማዘጋጀት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መድረስ መቻሉንና ተቋማት የአካባቢ ሕግን ተከትለው እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ በተከናወኑ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በተለይ ደረጃን ያላሟሉ ተቋማት ላይ ከመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ እስከ እገዳ የደረሱ የሕግ ማስከበር እርምጃዎች መወሰዳቸውን አብራርተዋል፡፡

በክልል ደረጃ በተከናወኑ የብክለት መግቻ እንቅስቃሴዎች በሁሉ ረገድ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን መመልከት መቻሉን ያስገነዘቡት አቶ ስንታየሁ፤ የክልሉ ሕዝብ ስለ አካባቢ ጥበቃ ብሎም ብክለት አወጋገድ ከወትሮው በተሻለ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና መብቱን የሚጠይቅ ማህበረሰብ መፍጠር ተችላል። ‹‹የአካባቢ ብክለት ሲከሰትም ‹‹ብክለትን ፈጥኖ ሪፖርት የማድረግ ልምዶች ተፈጥረዋል››ብለዋል፡፡

ከሕዝብ ባሻገር የዘርፉ ተዋናዮች ላይም ከፍተኛ ለውጥ መታየት መጀመሩን ያስገነዘቡት አቶ ስንታየሁ፤ ለአብነትም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ ለአካባቢ ደህንነትና ጥበቃ ልዩ ትኩረት መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ይህ ማለት ግን ብክለትን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በሚፈለገው ልክ ይደርሳል ማለት አይደለም፤ አካባቢ ብክለት በአንድ ሰሞንና ጊዜ ተግባር ብቻ የሚስተካከል አይደለም። ቀጣይነት ያለውን ሥራ፣ ቁርጠኝነትና ተሳትፎን የግድ ይላል። ስለዚህም የስድስት ወሩ ንቅናቄ በዚሁ ከፍታው ልክ በዚህም ዓመት እንዲቀጥል እየሠራን ነው›› ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ በልስቲ ፈጠነ በበኩላቸው፤ ‹‹በሀገር ሀገር ብክለት መግቻ ንቅናቄ ትግበራና ውጤት ብዙ ተምረንበታል፤ በተለይም ከተሠራ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አይተንበታል›› ብለዋል፡፡ የክልሉም በብክለት መግቻ ንቅናቄው የታየው ሁለንተናዊ ተነሳሽነትና ውጤት ይበልጥ መቀጠል አለበት የሚል አቋም መያዙንና ንቅናቄው በዚህ ዓመትም ይበልጥ ቀጣይ እንዲሆን እቅድ ወጥቶለት ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስተባባሪነትን ‹‹ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ›› በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄ መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You