የፀረ ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ ፦ ጥቃቶችን የማስቆምና የመከላከል ሥራና ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታገኘሁ አሰፋ አስታወቁ፡፡

ወይዘሮ እታገኘሁ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደስታወቁት፤ እንደ ሀገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት መከላከል የሚያስችል “ፀረ- ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ዘመቻ” በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በተለያየ መልኩ ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ዓለም አቀፉ የፀረ- ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ዘመቻ በኢትዮጵያም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን አካላዊ፤ ስነልቦናዊ፣ ወሲባዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቃት በመቃወም ለዓመታት ሲካሄድ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

እነዚህን ቀናት በኅብረት በማሰብ በሴቶች ላይ ችግር እያደረሰ ያለውን ጾታዊ ጥቃት ለመግታት ሀገራዊ አጀንዳ ማድረግ በማስፈለጉ ፣ የፀረ- ጾታዊ ጥቃት የንቅናቄ ዘመቻ በኢትዮጵያ መጀመሩንም አስታውሰዋል፡፡

ከ2006 ዓ.ም ጀምሮም 18 የተለያየ አደረጃጀት ያላቸው አባላት በማሰባሰብ ጥቃቱን እየተቃወመ በሚገኘው በኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ስር ባለው “ዘመቻ በጾታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ ቡድን” አማካኝነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥቃቱን ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን በጋራ ሲካሄድ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን መረጃዎች ማሳየታቸውን የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ ዘንድሮም 16ቱ ብርቱካናማ ቀናት “ስለ ሴቶች ጥቃት ዝም አንልም” በሚል መሪ ቃል እንደ ሀገር በተለይም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ለይቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት ባሻገር የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሀ ግብሮች ሲካሄድ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ስር ባለው “ዘመቻ በጾታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ ቡድን” እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች የግፊት ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ የምክክርና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፤ጥቃቱ የደረሰባቸውን ወገኖች ለማሰብ የሚረዱ የሻማ ማብራት ስነስርዓቶች በማካሄድና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ጥቃትን በመቀነስና በማስቆም ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጣ ሁኔታ ሲከበር መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

“ጾታዊ ጥቃትን ለማስቀረት ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ ነው” ያሉት ኃላፊዋ፤ በጋራ መስራቱ እርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ፤ እንዲሁም ዕለቱን አስመልከቶ በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች የተገኙ ሀሳቦችን በማደራጀት የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶቹ ለደረሰባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡት ማድረግ ያስችላልም ብለዋል፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የበኩሉን መወጣት እንዳለበት፤ በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት አስመልክተው ተከታታይነት ያላቸው ስራዎች መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ጥቃቱን ለመቃወምና ለመከላከል ሲካሄድ የነበረው የ16ቱ ቀናት የንቅናቄ ዘመቻ ቢጠናቀቅም፤ጥቃት የማስቆም ስራና የተቃውሞ ትግሉ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከህዳር 16 / 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄድ የቆየው የፀረ ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ዘመቻ ትናንት ተጠናቋል።16ቱ የፀረ- ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ቀን በወቅቱ ትሩጅሎ ተብሎ የሚጠራውን አምባ ገነናዊ ስርዓት ለመቃወም ሲፋለሙ በግፍ ለተገደሉ ለሦስት እህትማማቾች መታሰቢያነት እ.ኤ.አ በኖቨምበር 25 ቀን 1981 በላቲን አሜሪካዊቷ ኢንኩዊንትሮ መጀመሩ ይታወሳል።

ሰላማዊት ውቤ

 አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም

Recommended For You