– ባለሥልጣኑ የተመሠረተበት 80ኛ ዓመት በዓል እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፦ የአቪዬሽን ዘርፉን በማሳደግ አዳዲስ እድሎችን መክፈት፣ ሥራ መፍጠር እና የአፍሪካን ኢኮኖሚ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተመሰረተበትና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማቋቋሚያ ስምምነት የተፈረመበት 80ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ሁነቶች በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ከትናንት ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ትራንስፖርት የኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ መሪ እንደሆነ ይገነዘባል። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንም ለአየር መንገዱ ማስፋፊያ አስፈላጊውን የቁጥጥር ድጋፍ በማድረግ የዕድገት መሰረት ሆኖ ቆይቷል።
ባለሥልጣኑ ከ112 ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የአየር አገልግሎት ስምምነቶችን (BASA) ተፈራርሟል። እንዲሁም የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የሚደግፍ ወሳኝ የቁጥጥር ማሕቀፍ አዘጋጅቷል ያሉት ዓለሙ (ዶ/ር)፤ ይህ ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህም አፍሪካ ከዓለም አቀፉ የአቪዬሽን መረብ ጋር እንድትቀላቀል አስተዋፅኦ ያደርጋል። የአቪዬሽን ዘርፉንም በማሳደግ አዳዲስ እድሎችን መክፈት፣ ሥራ መፍጠር እና የአፍሪካን ኢኮኖሚ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ የአየር ትራንስፖርትን ለማስተዋወቅ ከአጋር አካላት ጋር በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ ነች ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ለማሸነፍ ዓለም አቀፍ ትብብር ቁልፍ ነው ብለን እናምናለን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን መስራች አባል መሆኗን ገልጸው፤ በአፍሪካና ከዚያም ባሻገር ትስስርን በማጎልበት በአቪዬሽን ዘርፍ አህጉራዊ ውህደትንና ትብብርን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የአቪዬሽን ስነ-ምህዳር እድገትን በመደገፍ ቁልፍ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተመሰረተበትና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማቋቋሚያ ስምምነት የተፈረመበት 80ኛ ዓመት በዓል ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ በበዓሉ አከባበርም የፓናል ውይይት፣ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም