ደንበኛ ሞኝ ነው?

ንጉሥ ነበር ደንበኛ፣ ድሮ ነው አሉ።

ድሮ ስል መች ነው ግን? የጊዜው አሯሯጥ የ’ድሮ’ን ርቀት መለኪያ የሆነውን መስፈርት ያጠፋው ይመስላል። እርግጥ ነው፣ ድሮ ሲባል የቀደሙ ወላጆቻችንን ዘመን እየጠቀስን ይመስላል። አሁን ላይ ግን ድሮ የሚለው ‘ነገር’ በክፍለ ዘመን አቆጣጠር መሆኑ ከቀረ ሰነባብቷል።

ለምሳሌ “በአምስት ብር ሂሳብ ተሳፋሪ ጭኖ ከተጠቀሰ አንድ ስፍራ የሚያደርስ ታክሲ ነበር።” ሲባል፥ ይህ ጉዳይ የዛሬ ሀምሳና አርባ ዓመት የሆነ የሚመስለው ተሳስቷል። ይህ የዛሬ አምስትና ስድስት ወር አካባቢ ታሪክ ነው። እንጀራ 15 ብር ይሸጥ ነበር ሲባልም እንደዛው፣ የጥንት ታሪክ ሊመስል ተቃርቧል።

በድምሩ፥ ይህን ሁሉ መዘብዘቤ፣ ድሮ የሚለው ‘ጽንሰ ሐሳብ’ ትላንት ወደሚለው የጊዜ መጠቆሚያ እየቀረበ ነው ለማለት ነው። ድሮ ታድያ ምን ነበር፥ ደንበኛ ንጉሥ ነበር።

ደንበኛ ንጉሥ ነበር፥ ቃሉ ይደመጣል፣ ቅሬታው ይስተናገዳል፣ መከፋቱ ጆሮ ይሰጠዋል፣ ቢሳሳትም እንኳ አይሳሳትም ትክክል ነው፣ ሳያጠፋ ይቅርታ ይጠየቃል፣ ሳይጠይቅ መልስ ይሰጠዋል፣ ምርጥ እቃ ሁሉ ይቀመጥለታል፣ ልዩ ቅናሽ ይደረግለታል ወዘተረፈ።

አሁን አንድ ሰው “ደንበኛዬ ጋር ሄጄ አንድ እቃ ልገዛ ነው” ሲል ምን ማለቱ ነው? አንደኛ በዋጋ አንጻር ቅናሽ እንደሚያገኝ ይተማመናል፣ ሁለተኛ የሚያገኘው ምርት ጥራት ያለው እንደሚሆንና የማይሆን እቃ ነጋዴው እንደማያቀርብለት እርግጠኛ ነው፣ ሦስተኛ አስር ቦታ እየገባ ‘ይሄ ስንት ነው፣ ዋጋ ቀንሱልኝ ተወደደ፣ ብዛቱ ይጨመርልኝ አነሰ፣ መርቅ እመርቅሃለሁ’ እየተባባለ ከመድከም ይተርፋል።

ይህ ሁሉ ነገር ታዲያ አሁንስ ከድሮው በምን መልኩ ተቀየረ? በብዙ መልኩ ተቀይሯል። የደንበኝነት ጥቅማ ጥቅሞች ብዬ የማስባቸው ጉዳዮች በሙሉ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደመከተል እንደሆኑ እንዲሰማኝ ያደረገ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። ጉድ!

ገጠመኙን ልንገራችሁ።

ከቤተሰብ ጋር ሆነን ሞባይል ለመግዛት ረዘም ላለ ጊዜ ደንበኛችን ወደምንላት ባለሱቅ አቀናን። ለሞባይል መግዣ የያዝነው ገንዘብ በዕቁብም፣ በብድርም፣ በውለታም የተገኘ ነውና ግዢውን በጥንቃቄ ለማድረግ ሲባል በርከት ብለን ነበር የሄድነው።

እኔ ነበርኩ፥ ከደንበኛዬ ውጭ ሌላ የትም አንሄድም ብዬ አብረውኝ ስልክ ለመግዛት የተሰማሩ አጃቢዎቼን ያሳመንኩት። “አምናታለሁ፣ በዛ ላይ ሱቋ በብዙ አማራጮች የተሞላ ነው። በዛ ላይ አውቃታለሁ፣ ታውቀኛለች፥ ልትሸውደኝ አትሞክርም።” ብዬ ኡ ኡ አልኩኝ። ከመካከላችን አንዱ ወንድሜ ብቻ ነጠል ብሎ፥ “እናንተ እዚህ እስክታዩ ድረስ እኔ ዞር ዞር ብዬ ገበያውን ልመልከት፣ ዋጋውንም ልይ” ብሎን ሄደ።

ደንበኛዬ ጋር ገባን፥ እንደተለመደው በፈገግታ አስተናገደችን። ከዚህ ቀደም ስለገዛነው ምርት፣ ስለመጥፋታችን፣ ስለምርቶች መወደድ፣ ባለፈው አብረን ሞባይል ልናጋዛው መጥተን ስለነበረው ጓደኛችን… ብዙ አወጋን። ከዛ ልንገዛ የመጣነውን እቃ ስንነግራት ዋጋ ነገረችን። ትንሽ ወደድ ማለቱን፣ የኑሮውን መቀያየር፣ እነሱ ራሱ ዋጋውን መጥራት እንዴት እንደሚከብዳቸው አያይዘንም ለልጆች ስልክ መስጠት እንደማይገባ፣ ስልክን ከሌባ፣ ከውሃና እና መሬት ላይ ከመውደቅ ምን ያህል መጠበቅ እንዳለብን መከረችን፣ ብዙ ተወያየን።

ሞባይሉ ተመረጠ፣ ዋጋ ስትነግረንም “ትንሽ ቀንሽ እንጂ” ስትል አብራኝ ገበያ የወጣች ጓደኛዬ፣ እኔ በአንጻሩ “የለም! ለእኔ ሁሌ ነው የምትቀንስልኝ፣ አትጫኗት” ብዬ በምልክትም፣ በሹክሹታም ተከራከርኩ።

ልንገዛ ተስማምተን የመጨረሻው ውሳኔ ላይ ልንደርስ ስንል፥ ሌላውን ገበያ ሲያይ የቆየው ወንድሜ ከተፍ አለ። ልንገዛ ያለውን ሞባይልና ዋጋውን ስንነግረው ፊቱ ተቀየረ። “ሻይም ጠጥተን፣ ገንዘቡንም በጥሬ አውጥተን ተመልሰን እንመጣለን፣ ሞባይል ባንኪንግ አንጠቀምም. . .” የመሳሰለውን ቀበጣጥሮ እንድንወጣ አደረገን።

አኳኋናችን መኪና ሊገዛ አማራጩን በደንብ ማየት እንደፈለገ ባለሀብት እንጂ መካከለኛ ደሞዝ እንዳለውና ሙሉ የአንድ ወር ደሞዙን ወጪ አድርጎ ሞባይል ለመግዛት እንደተሰማራ ሰው አይመስልም። ግርርርርር ብለን ከሱቁ ወጣን።

ግራ ገባኝ።

ይሄኔ ነው “ሆ ሆይ! ደንበኛ ንጉሥ ነው ያለው ማን ነው? ደንበኛ ሞኝ ሆኗል!” ያለን።

“እንዴት?” ጠያቂ እኔ ነኝ።

“እንዴ! ደንበኛኮ አሁን ሞኝ ተብሏል። ደንበኛ ስላችሁ ያው መደበኛ ተጠቃሚ የሚባለው ማለቴ ነው” አለ፥ ሊያስረዳ።

“እኮ እንዴት?” አልኩኝ፥ መቼም ጊዜ የማያመጣው የለ!

“ደንበኛ ስለሆንሽ ሌላ ቦታ እንደማትጠይቂ ያውቃሉ፣ ዋጋ እንደማታወዳድሪ፣ በጥራቱ ጥርጥር እንደሌለሽም እንደዛው። የጠሩልሽን በጠሩልሽ ዋጋ እንደምትገዢ አይጠራጠሩም። ስለዚህ፥ እንደውም ሞቅ ያለ ዋጋ የሚጭኑት ደንበኛቸው ላይ ሆኗል። አዲስ ደንበኛ ግን ተከራክሮ፣ ተጨቃጭቆ፣ ገበያ አነጻጽሮ ነው የሚገዛው።” አለ፥ ያለማንገራገር የተሻለ ዋጋ አለበት ወዳለው ሱቅ እየመራን።

“የምርህን ነው?”

“እውነቴን ነው። አንዷ ደንበኛዬ ናት አምልጧት ከዚህ በፊት የነገረችኝ። ተጨማሪ ትርፍ የሚያገኙት እንደውም ከደንበኞቻቸው ነው።”

ማመን ከበደኝ። ደንበኛቸው ነኝ ብዬ ያሰብኳቸውን ባለሱቆች ሁሉ አሰብኩ። ግፍ ሲፈጸምብኝ የኖረ መሰለኝ።

“የምርህን ነው?” ደግሜ ጥያቄ አነሳሁ። “እና አንድ ቋሚ ደንበኛ መያዝ ነዋ ሞኝነት?” አልኩኝ።

“በይ ደግሞ ይህንንም ጻፊውና ያነበበው ሁሉ መጠራጠር ይጀምር! ሁሉንም ማለት አይደለም…” አለኝ ሳቅ እያለ። እኔ ግን ነገሩን ማሰላሰል ማቆም አልተቻለኝም። ደንበኛ ሞኝ ነው? እንጃ! ብቻ ደንበኛዬ ያልኳት ባለሱቅ ያሳየችኝን ሞባይል ራሱን፥ እርሷ ከጠራችው ዋጋ በቀነሰ መጠን ከሌላ ሱቅ ገዝተን ወጣን። ይኸው ለእናንተም ነገርኳችሁ!

ሂላሪያ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You