‹‹አምቦ ሰላሟን እያስጠበቀች፤ ልማቷን እያስቀጠለች ያለች ከተማ ናት›› -አቶ ተስፋዬ ደገፋ የአምቦ ከተማ ምክትል ከንቲባ

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውክልና ያላት ሀገር እንደመሆኗ በጉያዋ ያቀፈቻቸውን ልጆቿን ያማከለ መልክ እንዲኖራት የተለያዩ ተጋድሎዎች ተደርገዋል፡፡ ከተለያዩ የትግል ምዕራፎች ውስጥም ስመ ጥር ከሆኑ የሀገሪቱ ከተሞች መካከልም አምቦ ከተማ ተጠቃሽ ነች፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ገዢና ጨቋኝ ናቸው የሚላቸውን ሥርዓቶች ከጫንቃው ላይ ለመጣል ባደረገው ተጋድሎ ፋና-ወጊ ከነበሩት እንዲሁም የለውጥ እርሾ ከሚጣልባቸው እና የትግል ማዕከል ከሆኑ የክልሉ ከተሞች ውስጥ አምቦ ግንባር ቀደም ከተማ ነች፡፡

አምቦና አካባቢዋ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ጭቆና የሚሞግቱ ጉምቱ ፖለቲከኞች የሚወጡባት፣ ስለነጻነት የሚያቀነቅኑ ስመጥር ድምጻውያን የሚፈልቁባትም ነች፡፡ ከዚህ ከተማ የሚነሳው የነጻነት እና የእኩልነት ድምጽ ምቾት የሚነሳቸው የየሥርዓቱ ገዢዎችም ከተማዋ በልማት እንድታድግ ከማገዝ ይልቅ መቀጣጫ እንድትሆን በሚመስል መልኩ የልማት ተጠቃሚ እንዳትሆን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አምቦ ዛሬ በተለይም ከስድስት ዓመት ወዲህ ካቀረቀረችበት ቀና ብላ ፊቷን ወደ ልማት አዙራለች፤ በዚህም መሻሻሎችን አሳይታለች፡፡ 19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በክልል ደረጃ እንድታስተደናግድም ታጭታለች፡፡ እኛም በዛሬው የእንግዳ አምድ ዝግጅታችን አምቦ ከተማን ልንቃኝ ወደናል፡፡ ከተማዋ በሰላምና ጸጥታ፣ በከተማ ግብርና ፣ በኮሪደር ልማት፣ በሥራ እድል ፈጠራ እና በሌሎችም ጉዳዮች እያደረገች ያለችውን የሥራ እንቅስቃሴና ያስመዘገበችውን ለውጥ በተመለከተ ከከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ደገፋ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የአምቦ ከተማ እና አካባቢው በኦሮሞ ሕዝብ የትግል ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ የመሆኑን ያህል በተለይም ባለፉት ሥርዓቶች በልማት ተጠቃሚ አልነበረም ይባላል፤ ለምንድን ነው?

አቶ ተስፋዬ ደገፋ፡– አመሰግናለሁ! ሁላችሁም እንደምታውቁት የአምቦ ከተማና የአካባቢው ማህበረሰብ ጫንቃው ላይ የተጫነውን ጨቋኝ ሥርዓት ከስሩ ነቅሎ ለመጣል ለረዥም ዓመታት በትግል ላይ ያሳለፈ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ዋና ትኩረቱ የነበረው የጭቆና ሥርዓትን ገርስሶ እኩልነት ፣ ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን ስለነበር እምብዛም ወደ ልማት ሥራዎች የገባበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከሌሎች የኦሮሞ ማህበረሰቦች እንዲሁም ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመተባበር ከፍተኛ ትግል አድርጎ ጨቋኝ ሥርዓትን በመጣል፤ አሁን የታየው ለውጥ እንዲመጣ የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የተጠመደ ነበር፡፡

በዚሁ መሰረት ከአምስት እና ስድስት ዓመታት በፊት የመጣው ለውጥ ለአምቦ ከተማም ይሁን ለመላው ኢትዮጵያ መልካም እድል ይዞ እንደመጣ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም እንደሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ መላው የምዕራብ ሸዋም ይሁኑ የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ለውጡ ያመጣላቸውን መልካም አጋጣሚዎች ተጠቅመው ፊታቸውን ወደ ልማት አዙረዋል፡፡ የአምቦ ከተማም በአሁኑ ሰዓት የተገኘውን ለውጥ እንደጥሩ አጋጣሚ ተጠቅማ በልማት ሥራዎች ላይ ተጠምዳለች፡፡ በዚህም የአካባቢውንና የከተማውን ገጽታ የቀየሩ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛል፡፡

የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥትም ለከተማዋ ልማትና እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከተማ አስተዳደሩም በበኩሉ ትልቅ በጀት በመበጀትና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የሚሰራቸው ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች አሉ፤ አምቦ ከተማ ከነበሩባት የመሰረተ ልማት ችግሮች አንዱ መንገድ ነበር፤ አሁን የመንገድ ጥያቄዋን ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ለምሳሌ የፌዴራል መንግሥትን ብንመለከት በአምቦ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ እየሠራ ይገኛል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም እንዲሁ ከአሥራ ስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገድ በማሠራት ላይ ይገኛል፡፡ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል ከሚያሠሩት የመንገድ ግንባታ በተጨማሪ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ትልቅ በጀት በመመደብና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከተማዋን በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለማስተሳሰር በስፋት እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህ የሥራ ሂደት በርካታ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተሠርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ አሁንም በግንባታ ላይ ያሉ አሉ፡፡

እንደሚታወቀው ከአዲስ አበባ ከተማ ተነስቶ አምቦ ከተማን በማቋረጥ ወደ ወለጋ የሚዘልቀው መንገድ ቀደም ሲል አንድ ብቻ ነበር፤ በዚህም ላይ ጠባብ ነበር፡፡ አሁን ከአንድ በላይ የሆኑ የመንገድ አማራጮችን ገንብቶ ጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል፡፡

በአጠቃላይ የአምቦ ከተማ የፌዴራል መንግሥት፣ የክልሉ መንግሥት፣ ከተማ አስተዳደሩና ሕዝቡ በሚያደርጉት ርብርብ የመንገድ መሰረት ልማት ጥያቄዋ እየተመለሰ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ ከንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ ከመብራትና ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት አንጻር ምን ትመስላለች?

አቶ ተስፋዬ ፡- የከተማዋ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በሚፈለገው ደረጃ ማሟላት ተችሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት እንደ ከተማ የሚነሱ የውሃ አቅርቦት ጥያቄዎች የሉም፡፡ የመብራት ፍላጎት ጥያቄዎችም በተመሳሳይ መንገድ ተመልሰዋል፤ ሌላው ቀርቶ የቴሌኮም ኔትወርክ ችግር አይስተዋልም፡፡ በከተማው የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግር ግን አለ፤ በአሁኑ ሰዓት የቁጠባ ቤቶችን በመገንባት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የቀበሌ ቤቶችንም በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል አሰራር ዘርግተን ችግሩን ለመፍታት እየጣርን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ምን ያህል አቅም አለ? በተያዘው በጀት ዓመትስ ለምን ያህል ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታስቧል?

አቶ ተስፋዬ፡– ከተማ አስተዳደሩ በሚፈጥራቸው ምቹ ሁኔታዎች ህብረተሰቡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ይፈለጋል። ከዚህ አንጻር የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል። እንደሚታወቀው አምቦ ከተማ በስተምዕራብ ፊንፊኔ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝና ወደ ወለጋ፣ ወሊሶና ሌሎችም ከተሞች መግቢያና መውጫ ኮሪደር ያላት በመሆኑ ለንግድ፣ ለሥራ ፍለጋ፣ ለተመቻቸ ኑሮና ለተለያዩ ጉዳዮች ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ በርካታ ሰዎች ይኖሩባታል። በዚህም ምክንያት የሕዝብ ብዛቷ በየጊዜው ያድጋል፤ የሥራ ፈላጊው ቁጥርም በዚያው ልክ ይጨምራል።

በመሆኑም ያለው ሥራ ፈላጊዎች ቁጥር እና ያለው የሥራ እድል አሁንም በሚፈለገው ልክ ተጣጥሟል ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ባለሀብቶችን በማሳተፍ ጭምር የከተማው አቅም በሚፈቅደው ልክ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ትልልቅ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው የሥራ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረውና ለእድገታችንም ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ የሚታመነው ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየሠራ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባለሀብቶች ወደ አምቦ ከተማ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ ይቅርና የነበሩት ራሱ ከተማውን ትተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚሄዱ ነበሩ፡፡ ከተማቸውን እንዳያለሙ ያደረጋቸው አንዱ ምክንያት የሰላም ጉዳይ ነበር፡፡

አሁን አምቦ ሰላሟን እያስጠበቀች፤ ልማቷን እያስቀጠለች ያለች ከተማ ሆናለች፤ በዚህ የተነሳ ኢንቨስተሮች ወደ ከተማዋ እየተሳቡ መጥተዋል። በርካታ ባለሀብቶች በልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ በመሆኑም የሥራ እድል እየተፈጠረ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ቢያንስ ከ195 በላይ ኢንቨስተሮች መሬት ወስደው በሥራ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛዎቹም ከ70 በመቶ በላይ ቅድመ ዝግጅትና የግንባታ ሥራዎችን ሠርተው በአጭር ጊዜ ወደ ሙሉ ሥራቸው የሚገቡ እንደሆነ ይጠበቃል። እነዚህ ወደ Cራ ሲገቡ ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ይሆናሉ፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ በተያዘው ዓመት ብቻ በከተማዋ 20ሺ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ ተይዟል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራውን በተለያዩ የሥራ መስኮች ተግባራዊ ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎችም በየጊዜው እየተገመገሙ ይገኛል፡፡ እቅዱ ግቡን እንዲመታም የባለሀብቱ ተሳትፎና የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ጉዳይ በመሆናቸው ሀብትን፣ ገንዘብን እና ጉልበትን በማቀናጀት የሥራ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፡- የልማት መሠረቱ ሰላም ነው፤ የአምቦ ከተማ የሰላም ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ተስፋዬ ፡– ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት አሁን የታየው ለውጥ በሕዝቡ መስዋዕትነት የተገኘ እንደመሆኑ ለውጡን ሕዝቡ ራሱ እየጠበቀው ይገኛል፡፡ ህብረተሰቡ ለውጡን የማስጠበቅ ወይም የማስቀጠል ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበትም ያምናል። ሥርዓቱን ያመጣው ራሱ በመሆኑም ይጠብቀዋል፤ እየጠበቀውም ይገኛል፡፡ ሕዝቡ ሰላሙን የመጠበቅ ከፍተኛ ፍላጎትም አለው፡፡ ይህ የሕዝቡ የሰላም ፍላጎት ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ደግሞ በእኛ በኩል መሥራት የሚጠበቅብንን እንሠራለን። ሰዎች የሚያቀርቧቸው የሰላም ጥያቄያቸው ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ በዚሁ መሰረት ከሰፈር ጀምሮ እስከ ከተማ መዋቅር ድረስ ህብረተሰቡን እና የጸጥታ አካሉን የማቀናጀት፣ ድጋፍና ክትትል የማድረግ ሥራዎች በአመራሩ በኩል ይሠራሉ፡፡

የማህበረሰብ ፖሊስ፣ የከተማ ሚሊሻ፣ የሥርዓቱ ጋሻዎች የሚባሉት የየአካባቢው ሥርዓት አስጠባቂዎች (ሲርና ጋቸና)፣ የአምቦ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ ፌዴራል ተቋማት የተመደቡ የፌዴራል ፖሊሶች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የየአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች የከተማውን ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር የየራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሁሉም የጸጥታ አካላት የተውጣጣ አደረጃጀት በመፍጠር ሁሌም በከተማውና በአካባቢው ሰላም ጉዳይ ምክክሮችና ውይይቶች ይደረጋሉ፤ በመድረኩ አሠራሮች ይገመገማሉ፤ በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ መሠራት ስላለባቸው ነገሮች የጋራ አቅጣጫዎችም  ይቀመጣሉ፡፡

በተለይም የሥርዓቱ ጋሻ (ሲርና ጋቸና) የሚባሉት ከማህበረሰቡ የወጡት ወጣቶች ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ወይም የየቀበሌዎችን ሰላምና ጸጥታ የማስከበር ሥራ ይሠራሉ፡፡ ህብረተሰቡም ያግዛቸዋል፤ አካባቢውን እንዲጠብቅ ተልዕኮ ይሠጠዋል። ፀጉረ ልውጥ ሰዎችን ሲመለከት ዝም ብሎ ማለፍ እንደማይገባው፤ በየሰፈሩ ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎች ማንነትን የማወቅ፣ በአካባቢው የሚስተዋሉ እውቅና የሌላቸው አደራጃጀቶችና እንቅስቃሴዎች ካሉ የመፈተሽ፣ አስፈላጊ ከሆነም ለሚመለከተው አካል መረጃ የመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ህብረተሰቡ የተሰጠውን ተልዕኮ በተግባር እንዲገልጽም በየጊዜው የማንቃትና የማስታወስ ሥራ ይሠራል። እንዲህ አይነት ጠንካራ አደረጃጀቶች ስለተፈጠሩ ከተማዋ ፀጥታዋ ተከብሮ ነው ያለችው፡፡ እኛም በከተማው ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ጠንካራ አቋም ይዘን፤ እቅድ አውጥተን ህብረተሰቡን እያንቀሳቀስንና እያቀናጀን የአምቦ ከተማ ሰላም እንዲጠበቅ፣ ልማቷም ጠዋትና ማታ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል እያደረግን እንገኛለን። በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት አምቦ ሰዎች ሰላም አጣን ብለው የሚፈናቀሉባት ሳትሆን ሰላም ፈልገው የሚመጡባት ከተማ ሆናለች፡፡ ይህ ሰላም የተገኘውም በጸጥታ ኃይሉ፣ በሥርዓቱ ጋሻዎች (ወጣቶች) በህብረተሰቡ ትብብር እና በተሠራው አደረጃጀት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የመቻል እቅድ ይዛ በግብርናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች ነው፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ የከተማ ግብርና ነው፤ በአምቦ ከተማ ፣ ከከተማ ግብርና እና ከሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብሮች አንጻር ምን የተሠሩ ሥራዎች አሉ?

አቶ ተስፋዬ፡– ከሌማት ቱሩፋት አንጻር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ለምሳሌ ህብረተሰቡ በግቢው ውስጥ ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲተክል ማድረግ ተችሏል፤ እያንዳንዱ አባ እና እማ ወራ ከ20 እስከ 30 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንዲኖሩት ከተቻለም አንድ የወተት ላም እንዲኖረው በማድረግ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በተጨማሪም እንደ ዩኒቨርሲቲ፣ የእምነት ተቋማትና ሌሎችም የሚሰሯቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በወተት ላሞች እርባታ፣ በከብት ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ ፣ በአሳማ እርባት፣ ወጣቶች በማህበር እየተደራጁ እንዲሠሩ በማድረግ እንደ ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብሩ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ እየተሠራ ነው፡፡ እስከ አሁንም አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል፡፡

ለህብረተሰቡም የሌማት ትሩፋት ምንድን ነው? ምን አይነት ጥቅም ያስገኛል? በሚለው ላይ በደንብ የማስገንዘብና የማነቃነቅ ሥራ ተሠርቷል። ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ዓመት በከተማው አቅራቢያ በሚገኝ ወንዝ ላይ ዓሳ የማርባት ሥራ ለመሥራት ከባለሀብቶች ጋር በመነጋገር ጅምር ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዓሳ የሚመረትባት ከተማ ትሆናለች፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኮሪደር ልማትን በተመለከተ በከተማዋ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ተስፋዬ፡– የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በፊንፊኔ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በክልሎችም እንዲስፋፋ በስልጠና የተደገፈ የሥራ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ይህ እንደ ሀገርም ይሁን እንደ ኦሮሚያ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት የአምቦ ከተማን የሚመጥን የኮሪደር ልማት እየተሠራ ነው፡፡ በመጀመሪያው ተግባራችን፤ ቤቶች ከመንገድ እንዲርቁ በተቀመጠው የርቀት መጠን ወይም ስታንዳርድ መሰረት ከማፍረሳችን አስቀድመን ሕዝቡ ልማቱ የእኔ ነው ብሎ አምኖ እንዲቀበል የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። የሚያምረው ከተማዬ ነው ብሎ እንዲቀበልና፤ አምኖበትም ለተግባራዊነቱ እንዲተባበር ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ራሱ ህብረተሰቡ የሚፈርሱ ቤቶችን ወሰን በማካለል እና ድንበር በማስከበር ሥራዎች ላይ ተሳትፏል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ወሰኑ ተከብሮ መንገድ የማስፋፋት ሥራው በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በመንገዶች ዳርና ዳር የሚገኙ ግለሰቦችም በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ሽግሽግ ማድረጋቸውን ተከትሎ የፈረሱ አጥሮችንና ቤቶችን የማስተካከል ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ለከተማዋ ውበትና እድገት ነዋሪው ሁሉ እየተረባረበ ነው፡፡

ከተማዋን በሚመጥን መልኩ ለዓይን ማረፊያና ለሰዎች መዝናኛ የሚሆኑ ሁለት ቦታዎችን በመምረጥም ከተማ አስተዳደሩ ራሱ ለመገንባት በያዘው አቅጣጫ መሰረት ወደ 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት በጀት ተይዞላቸው ወደ ሥራ በመግባት ላይ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይም ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች በኮሪደርና በሌሎችም የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ተችሏል፡፡ አምቦ ከተማን አቋርጦ የሚያልፈውን ወንዝ የማልማት ሥራ ለመሥራትም ጥናት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከተማዋን ማራኪ ውብና ለኑሮ ተስማሚ በማድረግ የቱሪስት ማዕከል እንድትሆንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷ እንዲጨምር ታስቦ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንደ ክልል በአምቦ ከተማ መከበሩ ለከተማዋ ምን ጥቅም አለው? አምቦ ተመራጭ የሆነችውስ በምን ምክንያት ነው? ምንስ ትርፍ አስገኘላት?

አቶ ተስፋዬ፡– አምቦ ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ከታገሉ አካባቢዎች አንዷ እንደሆነች ቀደም ሲል አንስተናል፡፡ በዘንድሮው ዓመት በክልል ደረጃ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በአምቦ ከተማ እንዲከበር ተደርጓል፡፡ እውነት ለመናገር ይህ በዓል በአምቦ ከተማ መደረጉ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። ይህንን እድል የሰጠንን የክልሉን መንግሥት እናመሰግናለን። የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠው በትግል ነው፤ እውነተኛውን ፌዴራሊዝም እውን ለማድረግ የዚህ አካባቢ ሕዝቦች ከሌሎች ጋር በመሆን ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የመጡ እንግዶች የትግል ማዕከል በሆነችው በአምቦ ከተማ መጥተው ይህን በዓል ማክበራቸው የሚያስደስት ነው፡፡ ትርጉሙም ከፍ ያለ ነው፤ የሕዝቡን የእርስ በእርስ ግንኙነትና አንድነትም የሚያጠናክር ነው፡፡

በዓሉ በከተማዋ እንዲከበር ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የዝግጅት ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በዓሉን በማስመልከት በምእራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ እና አምቦ ከተማ በገጠርና በከተማ የተሠሩ የግብርና እና የልማት ሥራዎች የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራማን በተገኙበት ተጎብኝተዋል፡፡ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ የደም ልገሳ እና ለሳምንት የቆየ የባዛር እና ኤግዚቢሽን ሥነሥርዓት ተከናውኗል፡፡ በባዛሩ ላይ ከተለያዩ የክልሉ ዞኖችና ከተሞች ማለትም ከአዳማ፣ ከጉጂ፣ ከፊንፊኔ ፣ ከጂማና ከመሳሰሉት የመጡ ቢያንስ ቆጥራቸው 118 የሚደርስ ኢንተር ፕራይዞች እንዲሁም ከ100 የማያንሱ ነጋዴዎች እና ከተለያዩ ኮሌጆችና ከግል ዘርፍ የመጡ 35 የፈጠራ ሥራዎች በባዛሩ ላይ ቀርበዋል፡፡ ምርታቸውን የማስተዋወቅ፣ ግብይት የመፈጸም እና ልምድ የመለዋወጥ ሂደቶችን አከናውነዋል። በኤግዚቢሽኑ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የኦሮሞ ሕዝቦችን ባህል የሚገልጹ አልባሳትና ቁሳቁስም ለእይታም ለሽያጭም እንዲሆኑ ተደርገው ቀርበዋል፤ በዓሉ በፓናል ውይይት፣ በድጋፍ ሰልፍና በሩጫ ውድድርም የታጀበ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ሰዓት ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለማካሄድ አጀንዳ የማሰባሰቡ ሂደት እየተጠናቀቀ ነው፤ ሕዝቡ ከሀገራዊ ምክክሩ የሚያገኘውን ትርፍ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ተስፋዬ ፡- እስከ አሁን ድረስ በአንዳንድ የሀገራችን ጉዳዮች በሃሳብ ሳንግባባ ማዶና ማዶ ሆነን የቆየንባቸው ሁኔታዎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ አሁን ይህን ችግር ሊፈታ ይችላል ተብሎ የታመነበት ሀገራዊ የምክክር መድረክ ነው። እስከ አሁን ያለው ሂደት በጣም ጥሩ ነው፡፡ ህብረተሰቡም፣ በየደረጃው ያለው አመራርም፣ ይህን እድል ተጠቅሞ ለሀገሪቱም ይሁን ለሕዝቡ ጥሩ ነገር ያመጣል ብለን እናምናለን። ከዚህ አንጻር እኛም የሚጠበቅብንን እየሠራን ነው። ሀገራዊ ምክክሩ የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ እንደሀገር ያልተግባባንባቸውን ትልልቅ ጉዳዮች ተነጋግረን እልባት በመስጠት ወደ አንድ የመግባቢያ ሃሳብ ላይ እንድንደርስ ያስችለናል፡፡ የእኔ ይበልጣል፤ የእኔ ይሻላል የሚሉት የተራራቁ ሃሳቦች ወደ መሀከል እንዲመጡ በማድረግ ልዩነታችንን የምናስታርቅበት ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክር ሃሳብና ሃሳብ ብቻ የሚንጸባረቁበት፤ ምክክርና ውይይት በማድረግ መግባባትና ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚረዳ መድረክ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ ከተማ አሉን የምንላቸውን ሃሳቦች ይዘን በእያንዳንዱ ሂደት የመሳተፍ ዝግጁነት አለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከሰላምና ልማት አንጻር ለዞኑ እና ለከተማው ነዋሪዎች ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?

አቶ ተስፋዬ፡- ለከተማው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያም ይሁን ለኦሮሞ ሕዝብ የማስተላልፈው መልዕክት፤ ይህ አሁን ያገኘነው ለውጥ ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም። ትልቅ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው፡፡ ይህንን ለውጥ ለማምጣት ብዙዎች የህይወት ዋጋ ከፍለዋል፤ ደምተዋል፤ ቆስለዋል፤ ስቃይና መከራ ተቀብለዋል። ይህን በጋራ ትግል ያመጣነውን ለውጥ አንድ ሆነን ተማክረንና ተረዳድተን መጠበቅና ወደ ፊት ማሻገር ይኖርብናል፡፡ ይህ ሲሆን ብልጽግናችንን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

ልማትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የመጀመሪያው መሠረታዊ ነገር ሰላም ነው፡፡ የሰላም ዋጋ በምንም የሚለካ አይደለም፡፡ ሰላም ሲኖር የብልፅግና ጉዟችን እውን እንደሚሆን ተስፋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለያየ መንገድ ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ወደ ሰላም መጥተው በዚህ ታሪካዊ የብልፅግና ጉዞ የድርሻቸውን እንዲወጡም እመክራለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቃለ ምልልስ ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነው ውድ ጊዜዎን ስለሰጡን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ ተስፋዬ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You