ሀገር በሰው፤ ሰውም በሀገር ይመሰላል:: አንዱ በአንዱ ውስጥ ይገለጣል:: ይህንን በጋራ የመጽናታቸውን ምስጢር ከምናይባቸው ኩነቶች መካከል ሕዳር 29 የምናከብረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አንዱ ነው:: ዕለቱ ሲሰየም የተለያዩ ትርጓሜዎች ተሰጥተውት ነው:: ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተረጋግጦ ጥቅማቸውን እንዲያሳኩ ያለመ ነው:: ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታቸው ከወቅቱ የፖለቲካ ሥሪት፤ ከዘመኑ የኢኮኖሚ እድገትና ማህበራዊ ትስስር አንጻር ተመጣጥኖ እንዲሄድ ለማስቻል ነው::
ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት ብሔር ብሔረሰቦች ከአብሮነት ይልቅ ልዩነት፤ ከመተባበር ይልቅ መነጣጠል፤ ከሚያሰባስቡ ትርክትና እሴቶች ይልቅ በሚከፋፍሉ አጀንዳዎች ላይ እንዲጠመዱ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራ ነበር:: የወል ማንነትም የሚባል አይታሰብም:: ከዚያ ይልቅ ተናጠላዊ ማንነት ገዝፎ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እስኪረሱ ድረስ በዓሉ የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ሆኖ ቆይቷል::
ከ2010ዓ.ም መንግሥታዊ ለውጥ ወዲህ ግን መጥፎ አስተሳሰቦች በመልካም ትብብርና በሕብር መጓዝን እንዲያነግቡ ሆነዋል፤ መፈናቀልና አለመረጋጋቶች፣ እልፍ ሲልም ጦርነቶች እዚህም እዚያም መታየታቸውን ከማስቀረት አንጻርም አሉታዊ አስተዋጽኦዎች እንዲበራከቱ አድርጓል:: ሕዝቦች የብዝኃነታቸውን ዓርማ አድምቀው እንዲያሳዩ፣ የውል ሰነዳቸውን እንዲገልጡ፣ ኢትዮጵያዊ መልካቸውን እንዲያሳዩ፣ የትናንት አብሮነታቸው በጽኑ መሠረት ላይ እንዲያኖሩ፣ የዛሬ እውነታቸውን እንዲገልጡና የነገ ሕልምና ተስፋቸውን እንዲያለመልሙ እድል ሰጥቷቸዋል::
ለውጡ ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ በሁለቱም መልክ እንድትገለጥም ያስቻለ ነው:: ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ብዙ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ሆነዋል:: ቀደም ሲል እንደ ሀገር ተከታታይ የሚባል ልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ቢመጣም እድገቱ የኅብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል፣ የዜጎችን የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያና የእርስ በእርስ ትስስርን ከማጠናከር አንጻር እንብዛም የታየ አልነበረም:: ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ተረጋግጧል ለማለት ያስቸግራል:: አብዛኞቹ ልማቶችም በውጪ ዜጎች የሚደረጉ እንጂ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ሲያበረታታ አልታየም:: የብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን መብት ጠብቋል፤ የመልማት መብታቸውን አረጋግጧል፤ ተጠቃሚነታቸውንም አስፍቷል ለማለት እንዲሁ አስቸጋሪ ነው:: ከለውጡ በኋላ ግን ይህንን ችግር ፈተዋል የተባሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል::
የለውጡ ሥራ ለሕዝብ እውቅና ከመስጠትም የጀመረ ነው:: በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፤ ትናንት በሕዝባችን የለውጥ ፍላጎት እና ተራማጅ የለውጥ እሳቤን ባነገቡ ብርቱ መሪዎቻችን ጥረት ታግዘን የጀመርነው የለውጥ ጉዞ ብልፅግና ፓርቲን ወልዷል:: በተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን የዓለም ፈርጥ ምድራዊት ኮከብ ሊያደርጉ የሚችሉ መሠረቶችን ጥሏል ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል::
አክለውም እንዳሉት፤ ለውጥ በመምጣቱ እንደ ሀገር ያልታዩ እምቅ ሀብቶችን እንዲታዩ፣ በአቧራ የተሸፈኑ እልፍ ውበቶች እንዲገለጡና አይደፈሬ የሚመስሉ ተግዳሮቶችን በመጋፈጥ ሀገርን ከብተና ማዳን ተችሏል:: በዚህም በሁላችን ከሁላችን ለሁላችን የሆነች ህብረ-ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን መገንባት ችለናል::
ይህንን እውነት የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት አረጋግጠዋል:: እርሳቸው እንዳሉት፤ ብልፅግና እንዲፈጠር ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በሀገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ባለፉት ሥርዓታት በአግባቡ ባለመመለሳቸው ነው:: ኅብረ ብሔራዊ የሆነ ሀገር ለመመሥረት አልተቻለም:: ሀገረ መንግሥቱና ብሔረ መንግሥቱ የነበሩት እጅግ በጣም ፈተና ውስጥ ነው:: የዜጎች መሠረታዊ ጥያቄዎችና መብቶች የእኩልነት፣ የነፃነትና የፍትህ ጥያቄዎች ያልተመለሱበት ጊዜም ነበር:: ሆኖም ሕዝቡ በአደባባይ ወጥቶ ለውጥ ፈላጊነቱን በማሳየቱ ብልፅግና ተወልዶ የእኩልነትን፣ የነፃነትን የሁሉም፣ በሁሉም ከሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻልበት ላይ እንዲሰራ ሆኗል::
በኅብር የደመቀውን አብሮነት፤ ትክክለኛውን ኅብረ-ብሔራዊ ዴሞክራሲ በተግባር መግለጥ እንዲቻልም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም አድርጎታል:: ይህ በመሆኑ ሕዝቡ ከተናጠል ይልቅ በጋራ መቆም ያለውን የላቀ አቅም እንዲያሳይ አድርጓል:: እንደ ሕዝብ ከነጣጣይ ትርክቶች ይልቅ ለአሰባሳቢ ሀገራዊ አብይ ትርክቶች ቦታ እንዲሰጥ፤ እውነተኛ የኅብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ቅኝቱ ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን ከፍ እንዲያደርግ መደላደልንም ፈጥሯል:: የትናንት ስህተትን ማረም ላይ ብቻ ከመታጠር ተወጥቶ የዛሬን ተጨባጭ ሃቅና እውነት መግለ ጥ ተጀምሯል::
ከትናንት ይልቅ ዛሬ የተሻለ ስለመሆኑ፤ ከዛሬም ደግሞ ነገ በእጅጉ የተሻለ እንደሚሆን በተግባር ወደማሳየቱም ተገብቷል:: ለዚህም አብነት የሚሆኑንን ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ማንሳት ይቻላል:: የሕዝብ መብት ተከበረ የሚባለው በፍጥነት የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሲያገኙ በመሆኑ፤ የለውጡ መንግሥት ከጅምሩ ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ፤ መስሪያና መለወጫ እንደሆነች ያሳየበት ተግባር አንዱ እውነቱን ከገለጡት ሥራዎች መካከል ነው:: ለውጡ ሲመጣ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና በትግል ስልታቸው ምክንያት ከሀገር የተሰደዱት ሀገራቸው ላይ መጥተው የፈለጉትን እንዲያደርጉ እድል ሰጥቷቸዋል::
ከዚህ በተጓዳኝ አሳሪና ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘኑ የሕግ ማሕቀፎች እንዲሻሻሉ፣ በአዳዲስ ሕጎች እንዲተኩና አዲስ የሆኑ ሕጎችም እንዲወጡም አስችሏል:: ይህ ደግሞ ከፖለቲካው አንጻር ስናየው አጋር እየተባሉ ይጠሩ የነበሩ ድርጅቶች ሳይቀሩ መፍትሄ እንዲያገኙና የክልላቸውን ብቻ ሳይሆን የሀገር ውሳኔ ላይ ጭምር እኩል መብት እንዳላቸው እንዲያሳዩ እድል ሰጥቷል:: ስለ ሕዝባቸው ጉዳይም ዝም እንዳይሉ አድርጓቸዋል::
ከለውጡ በኋላ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኃይልና አቅም አግኝተው ለሕዝቡ ጥቅምና ደህንነት እንዲሟገቱ እድል አግኝተዋል:: በነጻነት ተቀላቅለው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ እንዲሆኑም ተደርገዋል::
በፖለቲካው ዘርፍ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ከሆነባቸው ተግባራት መካከል ሌላው የክልልነት ጥያቄዎች መልስ ማግኘታቸው ነው:: በሞግዚት ይተዳደሩ የነበሩ ክልሎች የራሳቸው መብት ተሰጥቷቸው የራሳቸውን አስተዳዳሪ መርጠው እንዲተዳደሩ ሆነዋል:: የራሳቸውን ሕዝብ ራሳቸው እንዲያስተዳድሩት እድል አግኝተዋል:: በራሳቸው ቋንቋ፤ በራሳቸው ባህልና ወግ እየተመሩም ነው:: በተለይም ከበጀት አንጻር የሚያነሷቸው ጥያቄዎች መፍትሄ ያገኙ ይመስላል:: እንደውም ከዚያም አልፈው በጀት አመንጪ እንዲሆኑም መደላደል ተፈጥሮላቸዋል:: ምክንያቱም በተሰሩ ሪፎርሞች በራሳቸው ሀብት ራሳቸው የሚያዙበትን እድል ተጎናጽፈዋል::
ሌላው ከለውጡ በኋላ ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት መከበር የተሰራው ስራ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ማረጋገጥ ነው:: እንደ ሕዝብ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው አርሶ አደሩ ነው:: ከዚህ አንጻር የሀገር የኢኮኖሚ ምህዋር የሚዘውረው ግብርናው እንደሆነ እንረዳለን:: የአርሶ አደሩ የመልማት መብትን ከማረጋገጠ አንጻር የግብርና ሜካናይዜሽን ላይ የተሰራው ተግባር በቂ ማሳያ ይመስላል:: በክላስተር እንዲያለሙ ሲያደራጃቸው ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን ቆጥበው ምርታማነታቸውን የሚጨምሩበት መሳሪያ ጭምር በማመቻቸት ነው:: ይህ በመሆኑ ሕዝቡ ከሸማችነት ወጥቶ ወደ ሁሉን አቀፍ አምራችነት ተሸጋግሯል:: ኢትዮጵያ ታምርት ተብሎ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች በስፋት እንዲያመርቱ ሆነዋል:: በምግብ ራስን እንቻል በሚልም ግብርናው ትርፍ አምራችነትን ተጎናጽፏልም::
በሌማት ትሩፋትና በአረንጓዴ አሻራውም እንዲሁ የተሰሩ ተግባራት ከሀገር አልፈው ዓለምን ያስደመሙ በመሆናቸው በአህጉር ደረጃም ልምድ ተቀስሞባቸዋል:: ይህ ብቻም አይደለም ከገበታ ለሸገር እስከ ገበታ ለትውልድ የዘለቁ፤ አሁን ደግሞ መነሻውን አዲስ አበባ አድርጎ እስከ ገጠር ቀበሌዎች የደረሱ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም ሀገር እየለማች እንድትቀጥልና ከአደጉት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ የሚያስችሉ የሕዝብን ጥያቄ የሚመልሱ የለውጡ የኢኮኖሚ ትሩፋቶች ናቸው::
በማህበራዊ ዘርፍም የሕዝቦችን መብት ያረጋገጡ በርካታ ተግባራት ከለውጡ በኋላ ተከናውነዋል:: ይህ ደግሞ ተግባራቱ የዜጋውን ማኅበራዊ ስሪት፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ሥነልቦናዊ ማንነትና ልዕልና የሚያጎናጽፉ ስለመሆናቸው ራሳችን ምስክርነት የምንሰጥባቸው ናቸው:: የጤና እና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ መሠረተ ልማቶች በብዛትም በጥራትም መከናወናቸው ጤናማ ዜጋንና የተማረ ማህበረሰብን ከመፍጠር አንጻር የማይተካ ሚና ይኖረዋል:: ይህንን ደግሞ ከለውጡ በኋላ የተመለከትነው እንደሆነ ‹‹ትውልድ ለሀገር›› የትምህርት ቤት ግንባታዎችን ብቻ በመጥቀስ መናገር ይቻላል::
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት መረጋገጥ በማህበራዊ ዘርፉ ያለው ጠቀሜታ ከሌላም አቅጣጫ የሚታይ ነው:: ይህም በዓላቱን ከማክበርና እንዲታሰብ ከማድረግ አንጻር ያለው ጥቅም ሲሆን፤ በበዓሉ መከበር አማካኝነት የሀገር እሳቤ እንዲያቆጠቁጥ ይሆናል፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የትናንት የበዛ የጋራ ታሪክ፣ መንገድና ገድላቸው እንዲተዋወቁም እድል ይፈጥራል:: በተመሳሳይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚናና ድርሻ ተገንዝበው እንዲሰሩ ያደርጋል:: ኢትዮጵያዊያን እንደ ሀገር የወደፊትን ተልሞ እና ተባብሮ የመሥራት አቅም ያላቸው መሆናቸውንም እንዲያረጋግጡ መደላደልን የሚፈጥር ነው::
ይሄ ደግሞ ነገ ለልጆቻችን የተሻለ እድል ይፈጥራል:: ከትናንት ቁርሾና ንትርክ ነጻ የመውጣትን እድል ያጎናጽፋል፤ ከመነጠል ይልቅ በኅብር የመቆማችንን ኃያልነት ያሳያል:: ከሁሉም በላይ ዛሬን መሥራት፤ ዛሬን ዋጋ መክፈል፤ ዛሬን በንጹህ ልብ ሆኖ ቁጭ ብሎ መነጋገርን፤ ዛሬን ስለ ትናንት ሳይሆን ስለ መጪው እያሰላሰልን የተሻለ ነገርን የመተለም ልዕልናን ከእኛ ጋር ያደርጋል::
ስለሆነም ይህንን እድል የመጠቀሙ ሁኔታ የሁሉም ዜጋ ነውና ማንነታችንን ይዘን ኢትዮጵያዊነታችንን ከፍ ማድረግ፤ አንድነታችንን አጠንክረን ኅብረ- ብሔራዊነታችንን መግለጥ፤ ታሪካችንን ከተዛባ መስመሩ አውጥተን በትክክለኛና እውነተኛው ትርክት ማነጽና የጋራችን የሆነውን ሃቅ ማኖር ይጠበቅብናል በማለጥ ሃሳቤን ቋጨሁ:: ሰላም!!
ክብረ መንግስት
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም