በኮሪደር ልማቱ ከ600 በላይ አውቶብሶችና ታክሲዎችን የሚያስተናግዱ ተርሚናሎች ተገንብተዋል

አዲስ አበባ፡- በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በአንድ ጊዜ ከ600 በላይ አውቶብሶችና ታክሲዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ተርሚናሎች መገንባታቸውን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። ከ185 በላይ የታክሲና የአውቶብስ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች መሠራታቸውንም ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግና ለማዘመን የኮሪደር ልማት እያካሄደ ነው። በመጀመሪው ዙር የኮሪደር ልማትም ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን ሲሆን በዚህም ከ600 በላይ አውቶብሶችና ታክሲዎችን የሚያስተናግዱ ተርሚናሎች ተገንብተዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ በልማቱ ለሞተር አልባ ትራንስፖርት በተሰጠው ትኩረት በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የእግረኛ እና ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የብስክሌት መንገድ ተገንብቷል። ይህም የሞተር አልባ ትራንስፖርት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ።

እንደ ከተማ እስካሁን የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት አለመጀመሩን የጠቆሙት አቶ ያብባል፤ ቢሮው የብስክሌት ኦፕሬተሮችን መፍጠር የሚያስችል የአደረጃጀትና የአሠራር መመሪያ አዘጋጅቷል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ አደረጃጀቱና የአሠራር መመሪያው ተግባራዊ ሲሆን በከተማ አስተዳደሩ የብስክሌት መጋራት የትራንስፖርት ሥርዓት ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።

ከሃያት ወደ ሲኤምሲ፤ ከሜክሲኮ ወደ ሣር ቤት፤ ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ ከፍተኛ መኪና ተጠቃሚ ማኅበረሰብ እንደነበር አውስተው፤ በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድ ከተገነባ ወዲህ አጫጭር መንገድ ተጓዦች ታክሲ ከመጠበቅ ይልቅ በእግራቸው መጓዛቸው የዘርፉን አገልግሎት ያሳደገ ስለመሆኑ አቶ ያብባል ገልጸዋል።

በኮሪደር ልማቱ መንገዶች የተሳፋሪዎች የመጫኛና የማውረጃ ቦታ እንዲኖራቸው መደረጉን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው፤ ይህ ትናንት ያልነበረ ዛሬ ላይ የሚታይ እና ዘርፉን ወደ ዘመናዊነትና ተወዳዳሪነት የሚያመጣው መሆኑን አመልክተዋል።

ከተፈቀደ የመጫኛና ማውረጃ ቦታ ውጭ መጫንና ማውረድ አይቻልም። ይህ ተግባራዊ ማድረግ ሲቻልም የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ሠላማዊና የተቀላጠፈ እንደሚሆን አብራርተዋል።

ከ185 በላይ የታክሲና የአውቶብስ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች በመጀመሪያው የኮሪደር ምዕራፍ መገንባታቸውን ያስታወሱት አቶ ያብባል፤ በከተማዋ ከአሁን በፊት የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ተርሚናሎችና በርከት ያሉ ፓርኪንግ እንዳልነበረ ተናግረዋል። አሁን ላይ በለውጡ መንግሥት የመስቀል አደባባይ፤ አንድነት ፓርክ፤ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የመሳሰሉ የመኪና ማቆሚያዎች (ፓርኪንግ) መገንባታቸው አስታውቀዋል።

በመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ብቻ 32 መኪና ማቆሚያዎች (ፓርኪንጎች) መገንባታቸው ያስታወቁት ቢሮ ኃላፊው፤ በሁለተኛው ምዕራፍ ሁለተኛ ቤዝመንትና ከዚያ በላይ መሠረት ባላቸው ሕንጻዎች ጭምር እየተሠሩ ያሉ መኪና ማቆሚያዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ከ58 በላይ ፓርኪንጎች የሚሠሩ ሲሆን ለከተማዋ ዘመናዊነትና ተወዳዳሪነት ብሎም ለተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት እና የትራፊክ ፍሰት መሻሻል ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ነው ያሉት።

በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በአንድ ጊዜ ከ600 በላይ አውቶብሶችና ታክሲዎች ማስተናገድ የሚችሉ ተርሚናሎች መሠራታቸውን የተናገሩት አቶ ያብባል፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮግራም ሰፋፊ የተርሚናል ግንባታ እቅዶች ታቅደው እየተሠሩ መሆኑን አመልክተዋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You