አዲስ አበባ፡- በ2016/17 መኸር እርሻ እስካሁን ድረስ 16 ሚሊዮን 449 ሺህ 133 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ግብርና ምክትል ቢሮ ኃላፊና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዓለምይርጋ ወልደሥላሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016/17 መኸር እርሻ 550 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 49 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እስካሁን ድረስም 252 ሺህ 732 ሄክታር መሬት ላይ ያለ ሰብል ተሰብስቧል፡፡ ከዚህም 16 ሚሊዮን 449 ሺህ 133 ኩንታል ምርት ተገኝቷል፡፡
በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ለስብስባ የደረሰ 360 ሺህ ሄክታር መሬት ሰብል ተለይቶ ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ እስካሁን ድረስ 252 ሺህ 732 ሄክታር መሬት ላይ ያለ ሰብል ተሰብስቧል፡፡
በዚህም ውስጥ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ከአዝርዕት ሰብሎች፣ 12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ ከሆርቲካልቸር ልማት በድምሩ 16 ሚሊዮን 449 ሺህ 133 ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩ በተለይ የአዝርዕት ሰብሎችን ሰብስቦ ሳይወቃ የማቆየት ልምድ ስላለው ቁጥሩ ከላይ ከተጠቀሰው ሄክታር መሬት የተገኘውን ሙሉ ምርት የሚያሳይ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ክልል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በሜካናይዝድ የታገዘ የማሳ ዝግጅት፣ የግብዓት አቅርቦት እና የሰብል ተባይ ጥበቃ ሥራዎችን ያጠቃለለ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን አስታውሰው፤ ከዚህም በተጨማሪ የኩታ ገጠም እርሻ ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡
በተጠቀሰው ወቅት በዘር ከተሸፈነው 550 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 170 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በኩታ ገጠም የተዘራ ነው፡፡ አሁን ላይ በአብዛኛው የክልሉ ሞቃታማ አካባቢዎች በመኸር የተሠሩ ሰብሎች ምርት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀሪ ምርቶችም ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲሰበሰቡ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ለምርት አሰባሰቡም የማኅበረሰቡን ጉልበትና ምቹ በሆነባቸው አካባቢዎች ላይ ደግሞ ከ95 በላይ ኮምባይነሮች ገብተው እንዲሰበስቡ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪም ብዙ ባልተለመደው የፀደይ እርሻ በመኸር ተዘርተው ቀድመው የደረሱ በቆሎና ጤፍ ሰብሎችን በማንሳት 35 ሺህ ሄክታር መሬት በሽምብራ ዘር መሸፈን መቻሉን ጠቁመው፤ ይህም የአርሶ አደሩን በዓመት ሁለት ሦስት ጊዜ የማምረት ልምድ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ሽምብራ ብዙም ግብዓት የማይፈልግ፣ በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ምርት መስጠት የሚችል እንዲሁም በራሱ የናይትሮጂን የማብላላት አቅም ስላለው ለመሬት ለምነት መጨመርም ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡
በጥቅሉ ሲታይ የምርት አሰባሰቡ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ አርሶ አደሩ አሁንም በእያንዳንዱ ቀን ማሳ ሆኖ የደረሱ ሰብሎችን በአግባቡ እንዲሰበስብ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም