ክልሎችን ከክልሎች የሚያገናኙ የአውሮፕላን መዳረሻዎች እየተስፋፉ ነው

አዲስ አበባ፡– ክልሎችን ከክልሎች በቀጥታ የሚያገናኙ የአነስተኛ አውሮፕላን መዳረሻዎች እየተስፋፉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ። በአሁን ጊዜ አነስተኛ አውሮፕላኖች የሚያርፉባቸው 23 መዳረሻዎች ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንዳለ አሰፋ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በሀገር ውስጥ በረራዎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ አዲስ አበባ ከዋናው አውሮፕላን ማረፊያ መምጣት የግድ ነበር። አሁን ጊዜ አነስተኛ አውሮፕላኖች የሚያርፉባቸው 23 መዳረሻዎች ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። መዳረሻዎቹን ቁጥር ከዚህ በላይ ለማሳደግና ሁሉንም የሀገር ውስጥ አካባቢዎችን ለማገናኘት ተጨማሪ መዳረሻዎች እየተገነቡ ነው፤ የዲዛይን ጥናት እየተደረገባቸው የሚገኙ እንዳሉም ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ፤ መዳረሻዎቹ በጥናት የተሠሩ እና ለአነስተኛ አውሮፕላኖች ማረፊያ የሚያገለግሉ ቢሆኑም፤ በቀጣይ ግን ተርሚናል ተሠርቶላቸው ወደ ኤርፖርትነት የሚያድጉ ናቸው። ይህም መዳረሻዎቹን በተለይም ለኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው ያስችላል።

በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመንገድ ችግር ምክንያት አርሶ አደሩ ምርቱን በርካሽ ዋጋ በመሸጥ የልፋቱ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ገልጸው፤ የአነስተኛ አውሮፕላኖች መዳረሻ መስፋፋት ለእነዚህ አርሶ አደሮችና ለሀገሪቱም ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

‹‹ኤርፖርቶች እንዳሉ ሆኖ፤ ትኩረት እያደረግን ያለነው ኤርስትሪፕ (መዳረሻ) ላይ ነው›› ያሉት አቶ እንዳለ፤ ዋና ዓላማው ገጠራማ ሆነው የአውሮፕላን ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጥናት አድርጎ ፈቃድ ከሰጠ በኋላ በክልሎች ወይም በግል ዘርፎች ወይም በኤርፖርቶች ድርጅት ሊገነባ ይችላል። መዳረሻዎቹ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ለመሄድ ወደ አዲስ አበባ ይደረግ የነበረውን በረራ ከማስቀረታቸውም ባሻገር፤ ከአንድ የቱሪዝም መዳረሻ ወደ ሌላ የቱሪዝም መዳረሻ በቀጥታ በመሄድ የቱሪዝም ዘርፉን ያጠናክራሉ ብለዋል።

እንደ ኬንያ ባሉ ጐረቤት ሀገራት እስከ 200 የሚደርሱ መዳረሻዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ እንዳለ፤ የሀገር ውስጥ የአነስተኛ አውሮፕላኖች መዳረሻ (ኤርስትሪፕ) ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሁሉንም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የአውሮፕላን መዳረሻዎቹ መስፋፋት ለአርሶ አደሩ የግብርና ምርቶችን በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ተብሏል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You