አዲስ አበባ፦ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብሩ ለቱሪዝም ዘርፉ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና በኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ትንሳዔ ላይ እንዳለች የአዲስ አበባ ከተማ የባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሣው (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተለይ የኮሪደር ልማቱ ትሩፋቶች የሆኑት የዓድዋ ሙዚየም፤ ልዩ ልዩ የመስሕብ ቦታዎች፣ ማራኪ እይታዎች እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች አዲስ አበባ ከተማን ለዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ ስብሰባዎች እንድትመረጥ አድርጓታል፡፡ በዚህም አዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ትንሳዔዋ ሆኗል ብለዋል፡፡
እንደ ሂሩት (ዶ/ር) ገለጻ፣ የኮሪደር ልማቱ ከቱሪዝም ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ነው። የኮሪደር ልማቱ ቅርሶችን አጉልቶ በማውጣት፣ የበለጠ በመጠበቅ፣ በማደስና በመጠገን ፊት ለፊት መጥተው እንዲታዩ አድርጓል፡፡ ይህም አንድ የቱሪስት ከተማ ማሟላት ያለባትን መስፈርት እንድታሟላ አስችሏታል።
የኮሪደር ልማቱ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን የቱሪስቶችን ደኅንነት መጠበቅ የሚያስችሉ የደኅንነት ካሜራዎችን፣ የመንገድ መብራቶችና አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ያሟላ መሆኑም ከተማዋ ለቱሪስት ምቹ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ከ2011 ዓ.ም ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ለማስፋፋት በርካታ ተግባራት መከናወናቸው ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ የባሕል፤ ኪነጥበባት እና የቱሪዝም ማዕከላት ከተማዋ በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ ጎብኚዎች ተፈላጊ እንድትሆን አድርገዋታል ብለዋል ።
የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሐፍታይ ገብረ እግዚአብሔር እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ከለውጡ ወዲህ የከተማዋን የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ለማስፋት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ከእነዚህም መካከል አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እና በከተማዋ የተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ተጠቃሽ ናቸው ።
የልማት ሥራዎች የቱሪዝም ሀብቶች እንዲገለጡና ይበልጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማስቻላቸውን ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ የተሠሩት የልማት ሥራዎችም ለከተማዋ አዲስ ገጽታን በማላበስ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠራቸውን አቶ ሐፍታይ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማዋ አሁን ላይ በርካታ የዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ ስብሰባዎችን ለማከናወን ቀዳሚ ተመራጭ እየሆነች መምጣቷንም ገልጸዋል። በቅርብ ጊዜያት የተከናወኑ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ፣ ዓለም አቀፍ የፈጠራ ውድድሮች፣ የካፍ ጉባዔን ጨምሮ የከተሞች ፎርምን ለአብነት ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባን ወደ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ከተማነት የማሸጋገር ዕቅድ ተይዞ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ያሉት አቶ ሐፍታይ፣ በዚህም የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ተግባራት መዲናዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ ከተማ እንድትሆን አስችለዋታል ብለዋል፡፡
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም