ዜና ትንታኔ
በርካታ ሀገራት ሀገር በቀል እውቀቶቻቸውን በማዳበርና በማዘመን የእድገትና ሥልጣኔያቸው መነሻ አድርገዋል። ሀገር በቀል እውቀቶችን በሥርዓተ ትምህርታቸው በማካተት ይበልጥ እንዲጎለብቱና ከዘመን ጋር እንዲራመዱም ያደርጋሉ፡፡
በኢንዶኔዥያ ዮጊያካርታ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የሀገር በቀል ዕውቀት እና የሳይንስ ውሕደት ለባሕል ቀጣይነት›› በሚል ርዕስ እኤአ በ2018 በተሠራ ጥናት፤ ሳይንስ ከሀገር በቀል እውቀት የተቀዳ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ እንደ ጥናቱ ገለጻ፤ ሳይንስ ማለት በተፈጥሮ የሚከሰቱ ክስተቶችን መረዳት ማለት ነው፡፡ ይህም አካባቢን በማስተዋል እና በሕይወት ዘመን ልምድ በማዳበር በተፈጥሮ የሚከናወኑ ነገሮችን የማወቅ ውጤት እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ እና የዓለም አቀፍ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ በኪነ ሕንጻ፣ በመድኃኒት፣ በግብርና፣ በአልባሳት እና በሌሎች የዕደ ጥበብ ሥራዎች የራሷ ሀገር በቀል እውቀት አላት። ዳሩ ግን እነዚህ ሀገር በቀል እውቀቶች በዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካተው ሥራ ፈጣሪ እና ማንነትን አስቀጣይ አለመሆናቸው ይነገራል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህር እና የባሕል ተመራማሪ የሆኑት ሰሎሞን ተሾመ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ሀገር በቀል እውቀቶች ማኅበረሰቡ ለዘመናት ያካበታቸው የራሱ ዕውቀቶች ናቸው። የማኅበረሰቡ ሕይወት ናቸው፤ ማንነቱን የሚያስቀጥልባቸውም ናቸው።
‹‹ሥርዓተ ትምህርቱ መጀመሪያውኑም የማኅበረሰቡን ባሕል፣ ሥነ ልቦና እና ዕውቀት የረሳ ነው›› የሚሉት ሰሎሞን (ዶ/ር)፤ ከውጭ የተቀዳ በመሆኑ የኢትዮጵያን እምቅ ሀብት ለመጠቀም የሚያስችል እንዳልሆነ ያብራራሉ። የራስን ማንነትና የፈጠራ ጥበብ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነም ይናገራሉ።
እንደ ሰሎሞን (ዶ/ር) ገለጻ፤ ሀገር በቀል እውቀትን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት ሲባል፤ የውጭውን አለመጠቀም ማለት አይደለም። ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሀገራትን ተሞክሮ መውሰድ ያስፈልጋል፤ ሆኖም ግን የራስን ጥሎ ከሆነ ‹‹ቤት መሥራትን ከመሠረቱ ከመጀመር ይልቅ ከጣሪያ እንደመጀመር ይሆናል›› ይላሉ። ወደ ዓለም መሄድ የሚቻለው መጀመሪያ የራስን አውቆ ነው። በተለይም ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ባለው፤ ተማሪዎች ሀገራቸውን እንዲያውቁ መሠራት አለበት ይላሉ።
‹‹የዕደ ጥበብ ሥራዎችን በትምህርት ቤቶች ማሳየትና ማለማመድ ያስፈልጋል›› የሚሉት ሰሎሞን (ዶ/ር)፤ ተማሪዎች ለትልልቅ ሥራ ፈጠራዎች የሚነሳሱት በአካባቢ የሚሠሩ ነገሮችን በማየት እንደሆነ ይናገራሉ። እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ተማሪዎች የማይሰበር ጀበና መሥራት የሚችሉት፤ መጀመሪያ የሚሰበረውን የሸክላ ጀበና አሠራር ሲያውቁትና ሲያዩት ነው። ሞፈርና ቀንበርን በዘመናዊ መሣሪያ መቀየር ያልተቻለው፤ ተማሪዎቹ መጀመሪያ የእንጨቱን ሞፈርና ቀንበር አሠራር እንዲያዩትና እንዲያውቁት ስላልተደረገ ነው። መማሪያ ክፍል ውስጥ የሞፈርና ቀንበር አሠራር፣ የሸክላ አሠራር ቢማሩ፤ እነዚህን የሚተካ ሌላ ነገር ወደ ማሰብ ይሄዳሉ። ዘመናዊ የልብስ አሠራር ሊፈጥሩ የሚችሉት፤ መጀመሪያ የሽመና ጥበብ ቢማሩ ነበር። የቤት ውስጥ የመገልገያ ዕቃዎችን ከኬሚስትሪና ከፊዚክስ ጋር አያይዞ እንዲማሩ አለመደረጉ ሥራ ፈጣሪ እንዳይሆኑ ያደርጋል ይላሉ።
ሰሎሞን (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ መስጊድ እና ቤተ ክርስቲያን የታነፁባቸው ሀገር በቀል የኪነ ሕንጻ ዕውቀቶች ነበሩ፤ ዳሩ ግን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካተው ወደ ትውልድ ስላልተላለፉ የአሁኑ ትውልድ ሊሠራቸው አልቻለም።
የዩኒቨርሲቲዎችንና የኢንዱስትሪዎችን ትስስር በተመለከተም ሰሎሞን (ዶ/ር) ሲናገሩ፤ ትስስሩ መሆን ያለበት ከውጭ ሀገር የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ጋር ሳይሆን ሽሮ ሜዳ ከሚገኝ የራስ ሀገር ጥበብ ጋር ነው። ይህን ለማድረግ እንዲያስችል ደግሞ ሥርዓተ ትምህርቱ ወጣቶችን የክህሎቱ ባለቤት ማድረግ እንደሚገባው ያሳስባሉ።
ባለፈው ዓመት በአሜሪካ ዋሽንግተን ታኮማ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ሀገር በቀል እውቀትን በትምህርት ውስጥ ማካተት›› በሚል ርዕስ በታተመ ጥናት እንደተገለጸው፤ እውቀት ማለት የሰዎች፣ የተፈጥሮና የባሕል ነፀብራቅ ቢሆንም፤ ይህ ግን በቅኝ ግዛት አጋጣሚዎች ይሸረሸራል። ቅኝ ገዥ ሀገራት በቅኝ ተገዥዎች ላይ በሚያደርሱት የባሕል ለውጥ ሀገር በቀል እውቀቶች በሌላ ሀገር ባሕል ይቀየራሉ። ይህም ለነባሩ ነዋሪ አዲስ እንዲሆንበት ያደርጋል።
ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ሀገር ብትሆንም፤ ሥርዓተ ትምህርቱ የውጭውን መሠረት ያደረገ እና ለሀገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ያልሰጠ መሆኑ በራስ ፈቃድ ቅኝ መገዛት መሆኑን ምሑራን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛችው የራሷ ነባር ባሕልና ማንነት ያላት በመሆኑ እና ቅኝ ገዥዎች በቀላሉ እንደማይበርዙት አጥንተው መሆኑን የታሪክ ተመራማሪው አቶ አበባው አያሌው ተናግረዋል።
የአሜሪካው ጥናት እንደሚለው፤ ሀገራት ሥርዓተ ትምህርት የሚቀርጹት፤ ሀገር በቀል እውቀቶችን መነሻ በማድረግ ነው። ይህ ግን በዘመናት ሂደት እየተሻሻለና እየተወራረሰ ይሄዳል። በተለይ ቅኝ ተገዥ ሀገራት ሥርዓተ ትምህርታቸውን ወደ ሀገር በቀል እውቀቶች ለመመለስ ይቸገራሉ።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ሀገር በቀል ዕውቀት በኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ›› በሚል ርዕስ ተሾመ አበራ በሚባሉ አጥኚ በተሠራ ጥናት፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ሥርዓተ መንግሥታት ውስጥ የነበረው የትምህርት ሥርዓት፤ እውነተኛውን የኢትዮጵያን ባሕል፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ አይደለም። ለዚህም ምክንያቱ ከምዕራባውያን የሚገለበጥ መሆኑ ነው። ከ1900 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ ሥርዓተ ትምህርቱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከውጭ የተገለበጠ ሲሆን፤ የውጭ ባለሙያዎችም ያሉበት ነው።
ጥናቱ በማጠቃለያው እንደሚጠቁመው፤ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ዕውቅና ሊሰጣቸውና ወደ ሥርዓተ ትምህርቱ ሊካተቱ ይገባል። ለሀገር በቀል ዕውቀቶች የሀገር ውስጥ ቋንቋ ወሳኝ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ አሁንም በእንግሊዝኛ መሆኑ የሀገር በቀል እውቀትን እንደሚጎዳ እና የተማሪዎችን አመለካከት ጭምር ወደ ውጭ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የማኅበረሰብ ጉድኝትና ሀገር በቀል እውቀት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ሠላም ዓለሙ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ትምህርት ሚኒስቴር ሀገር በቀል እውቀቶች ማንነትን ለማስቀጠል፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እና ለሥራ ፈጠራ ያላቸውን ፋይዳ አምኖበት ጥናት እየተደረገ ነው።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ በየዘርፉ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን ማኅበረሰቦች እየተጠቀመባቸው መሆኑን፣ በየትኛው አካባቢ ምን አይነት ሀገር በቀል እውቀቶች እንዳሉ እና እንዴት እንደሚጠቀሙበት እየተጠና እና ልየታ እየተደረገበት ነው። የባሕል መድኃኒት ከሆነ፤ ለምን መድኃኒትነት እንደሚጠቀሙበት፣ በምን አይነት አካባቢና መልክዓ ምድር ውስጥ እንደሚገኝ፣ ምን አይነት ሰዎች ናቸው የሚያውቁት የሚለውን በተመራማሪዎች ይታያል ብለዋል። በቃል ደረጃ እየተላለፉ የመጡትን ወደ ሰነድ የማምጣት እና በሳይንሳዊ ሙያ የመለየት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድኃኒት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአልባሳት፣ በማኅበረሰብ ፍልስፍና በመሳሰሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየአካባቢያቸው እንዲያጠኑ አቅጣጫ መሰጠቱን እና እስከ አሁንም 17 ያህል ዘርፎች እንደተለዩ የተናገሩት ወይዘሮ ሠላም፤ ጥናቱ በሂደት ላይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን፣ ሀገር በቀል የፖለቲካ አካሄድን ተግባራዊ እያደረገች እንደመሆኗ ለውጥ እያመጣች እንደሆነ ሁሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን በትምህርት ሥርዓቷ በማካተት በኢኮኖሚው በፈጠራውና በመሰል ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የዘርፉ ምሑራን ይጠቁማሉ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም