አዲስ አበባ፡- የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የአንድነት፣ የሠላም፣ የመቻቻል እንዲሁም የኅብረ-ብሔራዊነት ቀለም መገለጫ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዓሉን አስመልክቶ ትናንት ባስተላለፈው መልዕክት፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ፤ የሕዝቦች ትስስርን በማጠናከር ኅብረ- ብሔራዊ አንድነትን በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ ከማገዙ ባሻገር የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕላቸውንና ማንነታቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ብሏል፡፡
በ1987 የፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚያረጋግጥ፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና የባሕላዊ መግለጫዎችን አስፈላጊነትን አፅንዖት መሆኑንም ጠቅሷል።
በዓሉ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች በታሪክ ለሀገሪቱ የበለፀገ የባሕል ቅርስ አስተዋፅዖ ያበረከቱትን አንድነት አስፈላጊ መሆኑን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት ተግባብተውና ተስማምተው የኖሩ የሕዝቦቿን የዳበሩ ባሕሎች፣ ቋንቋዎችና ትውፊቶችን ይበልጥ እንዲደምቁ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህ ሀገራዊ መግባባትን በእጅጉ እንደሚያጠናክረው ነው የገለጸው፡፡
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ይህን ልዩነት ለማክበር እና የማይናወጥ ብሔራዊ ማንነትን እንዲጎለብት ከማድረጉም ባሻገር በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል አብሮነትን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ነው ያለው፡፡
ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚለው መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ እውነታዎችን ቁልጭ አድርጎ እንደሚገልጽም አንስቷል፡፡
የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ እንዲከበር ማዘጋጀቱ ክልላዊ ብዝኃነትን እና አካታችነትን ለማስተዋወቅ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም አብራርቷል፡፡
“በዓሉ የአንድነት፣ የሠላም፣ የመቻቻል እንዲሁም የኅብረ-ብሔራዊነት ቀለም መገለጫ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን የብዝኃ ባሕል፣ ታሪክ፣ እሴትና የተፈጥሮ መስኅብ መሆናቸውን ለዓለም የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም