“ለኢትዮጵያ እድገትና ብልፅግና በጋራ መቆም ክብር ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- ከግልና ከአንድ አካባቢ መሻትና ፍላጎት ይልቅ ለኢትዮጵያ ብልፅግና እና እድገት በጋራ መቆም ክብር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ትናንት ሲከበር እንደገለጹት፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ ስንቆም ውብና ጠንካራ እንሆናለን፡፡ ከግልና ከአንድ አካባቢ መሻትና ፍላጎት ይልቅ ለኢትዮጵያ ብልፅግና እና እድገት በጋራ መቆም ክብር ነው፡፡

አብሮነታችንን በምንም ሁኔታ የማንሸረሽር ሕዝቦች እንሁን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በመደመር እሳቤ በኅብረ ብሔራዊ ትርክት በጋራ ለመቆም ሁሉም ዜጋ እንዲወስንም ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያን አውቀን አልጨረስናትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ባሕል፣ የጋራ ውርስ እና የጋራ መስዋዕትነት መኖሩንም ገልጸዋል፡፡

ገዢ ትርክትን በማጎልበት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፤ ኅብረ ብሔራዊነት ኢትዮጵያን ለመገንባት እና ለማጽናትም የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መከበር ሚናው የጎላ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ትልቅ መጽሐፍ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በውስጧ በርካታ ባሕሎች፣ እሴቶች፣ እውቀቶችና ጥበቦች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

አንድ መጽሐፍ ብቻውን ሙሉ እንደማይሆን ሁሉ የኢትዮጵያ ብሔሮችም አብሮነትን በማጎልበት ጉድለቶችን መሙላት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ተቀድታ የማታልቅ ባሕር በመሆኗ በቁንጽል እውቀት ከመበየን ይልቅ በቅርበት ሆኖ ማጥናት፣ መመራመርና ማወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ልባችን ወደ ሠላም በመመለስ ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማበልፀግ በጋራ እና በትብብር እንሥራ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በፈጣሪ ቸርነት እና በዜጎቿ ትጋት የጀመረችውን የብልፅግና ግስጋሴ ከግብ እንደምታደርስም አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሴራ፣ የፀብ፣ የውጊያ እና የጥላቻ ትጥቅን ፈትቶ ለኢትዮጵያ ሠላም እና ዕድገት በጋራ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች ከጦርነት ሠላም ይሻላል ብለው ወደ ሠላም መምጣታቸውን አስታውሰው÷ ይህን መልካም ጅማሮ በኦሮሚያ፣ አማራ እና በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ታጣቂ ወንድሞች እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ትናንት በስኬት የተከበረ ሲሆን መጪው ዓመት የ20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አዘጋጅ ክልል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሆኑ ታውቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You