መንገደኛው ትዝታ

የትዝታ አባት፣ መንገደኛው ትዝታ እያዘገመ ወደ አንድ አቅጣጫ ይመለከታል፡፡ በስሙኒ የሕይወት ፌስታል ከሸከፋት በቀር ሁሉንም ሰጥቶ ለራሱ የሚያጓዝዘው የለውም፡፡ ያለው ነገር ከወደኋላው ያለው የትዝታ ዥረት ብቻ ነው፡፡ ተሻግሯት በሃሳብ ግን ከሷው ጋር ሰጠመ፡፡ ደግ ነውና ደግ ደጉን እያሰበ ለመራቅ መወሰኑ ግን አልቀረም፡፡ የትዝታ ሁሉ ንጉሥ ነበር አሁን ራሱም ትዝታ ሊሆን ቆርጦ ተነስቷል፡፡

“ማህሙድ ጋር ጠብቂኝ” የትዝታ ወንዝና ወዝ ናት፡፡ ለብዙዎች የስሜት መናገሻ፣ የፍቅር ጥንቅሽ መልቀሚያ ናት፡፡ እልፎች ተቃጥረው የፍቅርን እሸት በልተውባታል፡፡ በሙዚቃ የስሜት ጣዕም ረክተውባታል፡፡ በደስታ ተራጭተውባታል። ከ1970ዎቹ ጀምሮ “ማህሙድ ጋር እንገናኝ” የዚያን ዘመን ምርጡ የአራዳ ትዝታ ነው፡፡ ትዝታ ግን ተንጣላ እንደ ጣና ሀይቅ አትቆምም፡፡ እንደ ዓባይ ግሳግሱን ተሸክማ መሄድ፣ መሮጥ ነው አመሏ፡፡ ሮጣም የማትገባበትና የማትደርስበት የለምና መንገደኛው ጉዞውን ሲጀምር ከኋላ እንዲህ ነበር፡፡

ያደረች አራዳ፣ ለፒያሳ መገን ምሽት ያለ አይመስልም። ጀንበር ብቅ ከማለቷ በጠዋቱ ሹኩሹክታ ፈገግ ብላ በቀኑ ግርግር የምትስቅ ትመስላለች፡፡ ተረኛዋ ጨረቃ ማታ በጨዋታው ከሰው ጋር ሞቅ ብላ፣ ከሚሰማት ሙዚቃ ጋር ማንጎራጎር ሳይቃጣትም አትቀርም፡፡ ይሄ መንገደኛ፣ ያ ትንሹ ልጅ ማህሙድም የፒያሳ አድባር ገና በጠዋቱ እየተጣራች ትቀሰቅሰዋለች፡፡ ማልዶ ተነስቶ ከሊስትሮ ሳጥኑ ጋር ወደዚያው ይገሰግሳል፡፡ ደርሶ “እንደምን አደርሽ ፒያሳ?” ለማለት በመርካቶ፣ እሪ በከንቱ ይሮጣል፡፡ በውቤ በረሃ ያቋርጣል፡፡

ትንሹ ማህሙድ ታላቁን ማህሙድን ለመገናኘት ወደፊት ሲከንፍ ያልገባበት አልነበረም፡፡ አሁን በተራው ትልቁ ማህሙድ ትንሹን ማህሙድ ፍለጋ በትዝታ ወደኋላ ገስግሶ “አዬ ጊዜ!” ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ፡፡ ትንሹ ማህሙድ የሊስትሮ ሳጥኑን ተደግፎ በሃሳብ ጭልጥ አለ፡፡ አዲስ አበባ መሃል ተቀምጦ ትዝታው ግን ሰባት ቤት ጉራጌ ነጎደ፡፡ ያቺን የተወለደባትን ቀን “መቼ ነበር? እንዴት ይረሳል፤ እንዴት ይረሳል፤ ተረሳሽ ወይ?” ሲል ራሱን ጠየቀ፡፡ አዎን ግንቦት 8 ቀን 1933ዓ.ም እንዴት ይረሳል…

አሁንም ትክዝ እንዳለ የልጅነት ፈተናዎቹ ፊቱ ድቅን አሉበት፡፡ በትውልድ ቀዬው ጣፋጭ የልጅነት ጊዜውን ሳያሳልፍ ትንሽ ልጅ ሆኖ ከቤተሰቡ ጋር አዲስ አበባ ገብቷል። እንደ እኩዮቹ ትምህርት ቤት ቢገባም ግን ለርሱ አልሆንህ አለው፡፡ የሚታየው ሁሉ የቤተሰቡ ችግርና የኑሮ ሰቀቀን ነበር፡ ፡ ገና ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ ከእናቱ ጋር ጉሊት ወጥቶ እንጀራ ሽጧል፡፡ ወደ ጫካ እየወረደ ጭራሮ ለቅሟል፡፡ ብዙ መከራ፣ ብዙ ውጣውረድ አላልፍ አላልቅ ቢለው ደግሞ የሊስትሮ ሳጥኑን አንጠልጥሎ ወጣ፡፡

ገና ጉልበቱ ያልጠነከረ የ12 ዓመት ድንቡሽቡሽ፣ የደስ ደስ ያለው፣ ሲያዩት አንጀት የሚበላ፣ ትሁትና ታዛዥ፡፡ በቀጭን ሰውነቱ ላይ ቱታውን በካናቴራ ደርቦ ከእግር ስር ቁጭ እንዳለ ጨርቁን ከሳሙና፣ ብሩሹን ከቀለም እያደረገ የቤተሰቡን ኑሮ ለማሸነፍ ከጫማ ጋር ይታገላል፡፡ ሰከን ያለ የልጅ አዋቂ ቢሆንም ሥራውን አንዴ ከጀመረ በፍጥነቱ የእዝርት ያህል ይሾራል፡፡ ከስር አቀርቅሮ ካላንጎራጎረ ቀኑም ሥራውም ይጣሉታል፡፡ የአራዶች ውቃቤ፣ የፒያሳ አድባር ያኮርፉታል፡፡ ከላይ ሽቅርቅር ብሎ እንደተቀመጠ ከታች እግሩን ለማህሙድ የሰጠው ጅንኑም ከጫማው መጽዳት ይልቅ በትንሹ ልጅ ዜማ የልቡ ፍንትው ማለት ያስደስተው ይሆናል፡፡

ትንሹ ማህሙድም ደንበኞቹ እስኪመጡ ያንጎራጉራል። መጥተው ቁጭ ሲሉም ያንጎራጉራል፡፡ በሸክላ ተጠፍጥፈው እየተሽከረከሩ በመጫወት ላይ ካሉት የሙዚቃ ድምጾች ሁሉ የዚያ ትንሽ ልጅ እንጉርጉሮ ጆሮና ቀልብ የሚስብ ይመስላል፡፡

ትንሹ ማህሙድ በሌላ ጊዜ ደግሞ በአንድ ክለብ ውስጥ በሳንድዊች አቅራቢነት ተቀጠረ፡፡ የገባበት ቤት በጊዜው የትላልቅ ድምጻውያን መገኛ ነበር፡፡ በጣም የሚወደድና ምርጦቹ ሙዚቃዎቻቸውን የሚያቀርቡበትም ነበር፡፡ ልቡ በሙዚቃ ፍቅር የተነደፈው ትንሽ ልጅ ከሚያቀርበው ሳንድዊቹ የዘፋኞቹ ድምጽ እየጠራው ቀልቡን ጥፍት አድርጎታል፡፡ የሙዚቃ ባንዶቹ ለልምምድ ሲመጡ ሙዚቀኞቹን ያያቸዋል፡፡

በተለይ ጥላሁን ገሠሠን በዓይኖቹ ብቻም ሳይሆን በልቡም ይመለከተዋል፡፡ ታዲያ ከዕለታት በአንደኛው ቀን ድምጻውያኑ በሌላ ሥራ ወደ ድሬዳዋ አቅንተው፤ ሙዚቀኞቹ በመሣሪያ ብቻ ሲለማመዱ አገኛቸው፡፡ ጠጋ ብሎም “መዝፈን እችላለሁና እኔ ልዝፈንላችሁ” አላቸው፡፡ ባያምኑበትም ሊከለክሉት አልፈለጉምና እስቲ በል አሉት፡፡ “አልጠላሽም ከቶ” አለ፡፡ የዚህን ትንሽ ልጅ ድምጽ የሰማን የቤቱን ባለቤት አጃኢብ! አስባለው፡፡ ሙሉ ሱፍ ለብሶ ከአስተናጋጅነት ወደ ዘፋኝነት ለወጠው፡፡

ጥላሁንና ጓዶቹ ከድሬዳዋ መልስ የተመለከቱት አስደነቃቸው፡፡ በማህሙድ ብቃት የተደሰተው ጥላሁንም የግጥም ደብተር ሰጠው፡፡ እሱም ከጥላሁን ስር የማይጠፋ ሆነ። በክብር ዘበኛ የመቀጠር አጋጣሚውን አገኘናም በቅድሚያ በሕዝብ ፊት ዘፍነህ ማለፍ ይኖርብሃል ተባለ፡፡ በአንደኛው ቀን በተሰናዳ ዝግጅት ላይም የመድረክ አስተዋዋቂው ወጥቶ “አንድ አዲስ ልጅ ዛሬ እናቀርብላችኋለን፡፡

ልጁ ምናልባትም የጥላሁን ገሠሠ ደቀመዝሙር ይሆናል ብለን እንገምታለን፡፡ ይሁን ካላችሁ ይቀጥላል” ሲል ለታዳሚው ገለጸ፡፡ ማህሙድ በተራው ተከትሎ መድረክ ከወጣና ከዘፈነ በኋላ ሊወርድ ሲል የታዳሚው ምላሽ “ይደገም! ይደገም!” የሚል ጩኸትና ፉጨት ነበር፡፡

ለ11 ዓመታት ያህል በክብር ዘበኛ ቤት ሲቆይ ከአፍ አከፋፈት እስከ ድምጽ ድረስ በጥላሁን ገሠሠ ተገርቷል፡፡ ጥላሁን ማህሙድ ላይ ያሳረፈው ዐሻራ ትልቅ ነበርና ዛሬም ድረስ በየአጋጣሚው ሁሉ የሕይወት ዘመን መምህሩ ስለመሆኑ የሚናገርለት፡፡ “ወንድሜ” እያለ ነው የሚጠራውም። ቀጥሎም በ1966ዓ.ም ወደ አይቤክስ ባንድ የመቀላቀል ዕድሉን አገኘ። የራሱንም ሆነ የቤተሰቦቹን የኑሮ ሸክም ማራገፍ የጀመረው ከዚህ በኋላ ነበር፡፡

ለዛሬው መሠረት የሆኑትን ድንቅ ሙዚቃዎችን መሥራት የጀመረው እዚህ ጋር ነው፡፡ በ1970ዎቹ አጋማሽም ፒያሳና ማህሙድ ሙዚቃ ቤት ተገናኙ፡፡ በዚያ ሙዚቃ ቤት ሳቢያ መንደሩ ለስሙ መጠሪያ እስኪሆን ድረስ ዝነኛና ተወዳጅ ሆነ።

ታላቁ የሙዚቃ ፍኖት፣ የክብር ዶክተር ማህሙድ አህመድ መንገዱን ቀጠለና ከሀገር ድንበር ተሻግሮ በአፍሪካ ሀገራት፣ አልፎ ሄዶም በአውሮፓና አሜሪካ ተገኘ፡፡ በሄደበት መንገድ በረገጠው ሥፍራ ሁሉ የስሙን ዐሻራ በዱካው ማህተብ ማሳረፍ ጀመረ፡፡

በሙዚቃ ሕይወቱ ማህሙድን ከብዙዎች ለየት የሚያደርገው ነገር ምንድነው ካሉ ይኸው በውጭ ያለው ስሙ ነው፡፡ በተለያዩ ሀገራት መድረኮች ላይ በክብር ቆሞ ትዝታውን አንጎራጉሯል፡፡ ብዙዎች ምራቅ የሚወጡበትን መድረክ እንደቀልድ ሰተት ብሎ ገብቷል፡፡ በ1999ዓ.ም ከአፍሪካ ዓለም አቀፍ ተሸላሚ ለመሆንም በቅቷል፡፡ ከኢትዮጵያ በማይተናነስ መልኩ በውጭ ሀገራት አድናቂና አድማጭ አለው፡፡

ከባህር ማዶ የነበረውን ታላቅነቱን ስናነሳ የማንዘነጋው ሌላ አንድ ሰው ከመንገዱ ላይ አለ፡፡ ፈረንሳዊው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ባለሙያ ልቡ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ፍቅር የሚቃጠል ሰው ነበር፡፡ ከሙያው ባሻገር በተያዩ ቋንቋዎችና ስልቶች የተሠሩ፣ በተለይም ቆየት ባሉ ሙዚቃዎች ጥናትና ምርምር የሚያደርግ ምሁርም ጭምር ነው፡፡ ታዲያ አንድ ጊዜ ላይ “ኧረ መላ መላ” እያለ ትዝታና ፍቅርን በሬዲዮ የሚያንቆረቁረውን የማህሙድን ድምጽ ሰምቶ ተማረከበት፡፡ ፈልጎ አስፈልጎ አገኘውናም አብረን እንሥራ ሲል የጥያቄ ግብዣ ለማህሙድ አቀረበለት፡፡ ማህሙድ ፈራተባ እያለም ምላሹ የእሽታ ቢሆንም በመጀመሪያ ግን ተጠራጠረው፡፡ ምን አስቦ ነው ሲል አሰበ፡፡

በጊዜው ፍራንሲስ ፋልሴቶ “ኢትዮጲክስ” የተሰኘውን ኢትዮጵያዊ ሙዚቃዎችን ብቻ ያካተትና ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚናገር ግዙፍ ዝግጅት በማሳናዳት ላይ ነበር። በ1960ዓ.ም ሁለቱም አብረው ለመሥራት በመነጋገር ላይ ሳሉ ንግግራቸውን ሳይጨርሱም በመሃል ማህሙድ ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር ተያይዞ የሙዚቃ ሥራ ለማቅረብ ወደ ፋልሴቶ ሀገር ፈረንሳይ አቀና፡፡ ቢሄድም ተመልሶ ከመጣ በኋላ ከፋልሴቶ ጋር የጀመሩትን ሥራ ቀጠሉ፡፡

ከፋልሴቶ መንገድ ላይ አሻግረው ሲመለከቱ የነበሩ ሁሉ ማህሙድን አለማድነቅ አልተቻላቸውም፡፡ በእርሱ ተመርጦ አብሮ በመሥራቱ ብዙ ዕድሎችን ተገናኘ፡፡ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ አፍቃሪያን ልብ ውስጥ እንዲቀር ሆነ፡፡ ከአዛዚያም ስልቱ ጀምሮ ሁሉንም ነገሮቹን እንዲወዱለት ሆኗል፡፡

ሙዚቃዊ ርምጃው ሁሉ ኢትዮጵያዊ በሆነ ስልት ነው፡፡ ባህላዊውን ቅኝት ሳይለቅ ከዘመናዊው ጋር በሚገባ አጣጥሞ ሞዝቆታል፡፡ የርሱ መገለጫና ንግሥናው በትዝታ ቢሆንም በጃዝና ፋንክም ደህና አድርጎ ተጫውቶባቸዋል። ወደር የሌለው ድምጻዊ ብቻ አይደለም፤ ግጥምና ዜማ በመድረስም የታወቀ ሙዚቀኛ ነው፡፡ ሙዚቃዎቹ ግን እጅግ በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ እንደዋዛ ለመቁጠር የሚቻሉ አይመስሉም፡፡

በአልበም ደረጃ “ኧረ መላ መላ” በ1975ዓ.ም፣ “ትዝታ 1 እና “ትዝታ 2” በ1975ዓ.ም፣ “ሶል ኦፍ አዲስ” በ1977ዓ.ም፣ “ተው ተው ጊዜ” በ1978 ዓ.ም፣ “አልማዝ” በ1986ዓ.ም፣ “ገዳዎ” በ1995ዓ.ም፣ “ትዝታ” በ2001ዓ.ም፣ “ይትባረክ” በ2008 ዓ.ም የመንገደኛው ስንቆች ናቸው፡፡ መቼም ከልብ የማይጠፉት የጉራጊኛና ሌሎች ቋንቋዎች ሙዚቃዎቹ ሙት ጆሮን የሚቀሰቅሱ ናቸው፡፡

ማህሙድ ከአንድ የግል ኮንሰርትም ይሁን የጋራ ዝግጅት ላይ ከመድረክ በስተጀርባ የሚታየው ወደ አዳራሹ አጨንቁሮ የታዳሚውን ድባብና ስሜት ሲከታተል ነው፡፡ በቆይታቸው ፈልገው የመጡትን እንዳያጡ አብዝቶ ይጨነቃል፡፡ የልብ ትርታቸውን ስለሚረዳም እርሱ መድረክ ላይ ወጥቶ ማይክራፎኑን በጨበጠ ጊዜ ሙዚቃው እንደ ብሔራዊ መዝሙር ነው፡፡ ሁሉም በእኩል አብሮት ያዜማል፡፡ እንዲያ ሆነው ተመልክቷቸው እንኳን አይረካም፡፡

በስተመጨረሻም የነበራቸውን አቀባበል ለማወቅ ሌላውን ይጠይቃል፡፡ “ሕዝቡ መደሰቱን እያየሁ እንኳን በድጋሚ ጠይቃለሁ፡፡ ምክንያቱም የመጣው ታዳሚ ከእኔ የሚጠብቀውንና ከዝግጅቱ የሚፈልገውን ነገር ማግኘት አለበት ብዬ ስለማምን ነው” ይሄ ለሙዚቃ አፍቃሪውና ደጁን ለረገጠ ሁሉ ያለው ክብር ነው፡፡

ታዲያ ማህሙድ ያ ሁሉ አክብሮቱ ሚወዱትና አድናቂዎቹ ለሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ የልቡ ቅንነትና ትልቅ ሆኖ ከትንሹም ጋር እኩል መታየቱን ስንመለከት ውስጥ የተገነባበት ከህብሪት ነጻ ሕይወቱ የሚያስቀና ነው፡፡ “ትንሹንም እንደትንሽነቱ፣ ትልቁንም እንደትልቅነቱ ማክበር ነው፡፡ ለኔ ሁሉም እኩል ናቸው” በማለት ይናገራል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ አጢኖ ለተመከተው የትኛውም ዓይነት የተከበረ፣ የቱንም ያህል ተራ ሰው ቢሆን ሰላምታው ሁሌም ሁለቱንም እጆቹን ሰዶ፣ በዝቅታ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን ትህትና ሲያሳይ የነበረው እኮ ያኔ ገና ሊስትሮው ሥፍራ ሳለ ነበር፡፡ ግን አገኘሁ ብሎ ደረት ሳይነፋ፣ በዝና ናኘሁ ብሎ ሳይኩራራ፣ ምርጡ ድምጻዊ ነኝ ብሎ ሳይታበይ፣ ትልቅ ነኝ ብሎ ሳይኮፈስ ይሄው እንዳለ አለ፡፡

አሁን ሲያልፉ ያገኙት ሰው፣ ሲመለሱ ሰውነቱ እንደ ጤዛ ረግፎ እንደ መንፈስ በሚለዋወጥበት ጊዜ፤ ማህሙድ ግን ከ60 ዓመታት በፊት የነበረ ማንነቱ ዛሬም ድረስ አልተለየውም። እንዲለየውም ለአፍታ ዕድሉን አይሰጠውም፡፡ ሁሌም በሄደበት ሁሉ እንዴት ከሰው ጋር መኖር እንዳለበት ያስባል። ለዚህም ይመስላል በሙዚቃ “ተይ ልኑርበት” ሲል ከሰው እንዳታነካካው የሚማጸናት፡፡

እራሴን ዝቅ አድርጌ

ከሰው ጋር እንድስማማበት

አግዢኝ ባሳብ ደግፊኝ

አንቺ ሰው ተይ ልኑርበት

ማህሙድ የክብር ብቻ ሳይሆን የፍቅር ሰውም ጭምር ነው፡፡ በትዳር ተጣምሮ ለብዙ ዓመታት አብራው ለኖረችው ባለቤቱ እጅጋየሁ ሳይሰለች አዚሞላታል፡፡ በማያልቅ የፍቅር ቃል አስውቧታል፡፡ ግን “የተዋደደ ሁሉ አብሮ አይኖርም” የሚለው አንዳንዴም እውነት አለው፡፡

በትዳር ቆይታቸው ሁለት ልጆችን ቢያፈሩም መጨረሻው ግን ሞት የሆነው መለያየት እጣፈንታቸው ሆኗል። ቢለያዩም ዛሬም ድረስ ልባቸው በመተሳሰብ የሞቀ ነው፡፡ ስለ እርሱ ክፉ ስትናገር አትደመጥም፡፡ ስለ እርሷ እንዲህ ናት ሲል አይሰማም። አንዱ ስለሌላው መልካም መልካሙን ብቻ ከማውራት አይቦዝኑም፡፡

የማህሙድ ጎዳና ትውልድን ከትውልድ፣ ባህልን ከዘመናዊነት ጋር ያገናኘ ትልቅ አደባባይ ነው፡፡ በሙዚቃው ጭኖ የሚጓዘው የራሱን ብቻ ሳይሆን የሙሉ ትውልዱንም ትዝታ ነው፡፡

በርሱ ውስጥ የምንመለከታቸው ሰዎች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ያላንጎራጎረው፣ በመረዋ ድምጹ ያላስረቀረውና ያልተስረቀረቀ ምንም የለም፡፡ ትዝታን አዝለው ያልሄዱበት የእርሱ የትዝታ መንገድ አይገኝም፡፡ ሁሉን ይዞ፣ ሁሉንም የሰጠ፣ ሙዚቃ እስትንፋሱ ደግነት ከነብሱ የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡ አንዱን ትዝታ ሺህ አድርጎ በየፈርጁ ሲሰጠን አዲስ እየሆነብን ሰምተን በድግግሞሽ እንኳን ልንረካ አልቻልንም፡፡

ከወራት በፊት አንዱ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “ከብዙ የትዝታ ሙዚቃዎችህ ውስጥ የሁሉንም በአንድ ይገልጽልኛል ብለህ የምታስበው ግጥም የትኛው ነው?” የሚል ነበር፡፡ ማህሙድም ጥቂት አሰብ አደረገና እንዲህ አለ፤ “ከበራፍ አንስቶ እስከ ምሰሶው፤ አጎንብሶ ይሄዳል ያፈቀረ ሰው…ዓመት አምስት ዓመት ይቀመጣል ጠጅ፤ መናፈቁ አይቀርም የራቀ ወዳጅ” ብሎ አዜመ፡፡

የትዝታው መንገደኛ በሙዚቃ ጋራ ሸንተረር፣ በዳገትና ቁልቁለቱ ወጥቷል፡፡ ወርዷል፡፡ ረዥም ተጉዞ በእድሜ ማምሻውን ድክምክም ብሏል፡፡ ከልጅነት እስከ ሽበት ከ60 ዓመታት በላይ ከደከመለት ሙዚቃ ላይ ሁሉንም ሰጥቶ ሲያበቃ ለራሱ የቀረው ቀሪ ዘመኑ ብቻ ነው፡፡ ይህ ግን ማንም በምንም ሊነካበት የማይገባውና የርሱ የብቻው የሆነ ሕይወት ነው፡፡ ለዛለው ጉልበቱ መበርቻ፣ ላለፈበት የትዝታ መንገድ እረፍትና ለቀጣይ ሕይወቱ ማሰላሰያ ጊዜ ደርሷል፡፡

በስተመጨረሻም የሚወዱት ሁሉ ተሰባስበው ማይኩን ሲሰቅል በክብር ለመሸኘት ጥር ሶስትን ትን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ በሚመጣው ጥር ሶስት ቀን 2017ዓ.ም የታሰበለትን ሲሰማ “ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ፡፡ ስላከበራችሁኝ አከብራችኋለሁ፡፡ ለኔ የተደረገው ሁሉ ለሌሎቹም እንደተደረገ ነው የምቆጥረው” አለ፡፡

ከመድረኩ ላይ በክብር ተሰናብቶ፣ እሱ ትዝታውን ብቻ ይዞ ይወርዳል፡፡ ሕይወት ግን እስከ አንድ ጀንበር መጥለቂያ ድረስ ሁሌም የጉዞ መንገድ ናትና ትዝታውን እንዳንጠለጠለ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ የሙዚቃ ትዝታና ናፍቆት ከጀርባው ሆኖ ቢጣራውም “ተው ልመድ ገላዬ፤ ገላዬ…” እያለ መሄድ ብቻ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You