አዲስ አበባ፡-በሀገራዊ ለውጡ የተመዘገቡ ድሎችንና የብልፅግና ጉዞን ለማስቀጠል ብሔራዊ ትርክት ግንባታን ማጠናከር እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር 19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልክቶ በአርባ ምንጭ ከተማ ትናንት ሲምፖዚየም ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የዘንድሮው በዓል ልዩ የሚያደርገው በሁሉም መስኮች እመርታዎች የተመዘገቡበት መሆኑ ነው። በሀገራዊ ለውጡ የተመዘገቡ ድሎችን ለማስቀጠል ብሔራዊ ትርክት ግንባታን ማጠናከር ይገባል፡፡
በዓሉ የሕዝቦች ባሕላዊ እሴቶች፣ ማንነትን ያከበረ ኅብረ ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር እንዲሁም ሀገራዊ መግባባት እንዲጎለብት ያግዛል ብለዋል።
ቀኑ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ሲከበር አንድነት እንዲጎለብት፣ ሕገ-መንግሥቱና በፌደራል ሥርዓት ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ 19ኛው በዓልም ”ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከኅዳር አንድ ቀን ጀምሮ ሲዘከር መቆየቱን አመልክተው፤ በዓሉ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ መግባባት እንዲጎለብት የማይተካ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ስኬታማነት ደግሞ ሀገራዊ መግባባት ላይ አበክሮ መሥራት ይገባል ጠቁመው፤ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ከራስ አስተዳደር ባሻገር የበይነ መንግሥታት ግንኙነትም ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፤ ይህ ደግሞ መተባበር፣ መተሳሰብ፣ አብሮነት፣ ፍትሐዊነትና እኩልነት እንዲጠናከር ያግዛል ነው ያሉት።
ሀገራዊ ሠላምን በማረጋገጥና ፍትሐዊነትን በማስፈን ኢኮኖሚያዊ የጋራ ተጠቃሚነት ማሳደግ ለሀገራዊ መንግሥት ግንባታ አይተኬ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፀሐይ ወራሳ በበኩላቸው በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የማንነት ዕውቅና የሰጠና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ ለማስቀጠል ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን ብዝኃነትንና የአንድነትን መሠረት ያደረጉ እንዲሁም በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በባሕል የተሳሰርን ወንድማማች ሕዝቦች ነን ብለዋል።
በዓሉም የአብሮነትና የመከባበር እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር በእኩልነት የምንኖርበት ሀገር ለመገንባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በሀገራዊ ለውጡ የተመዘገቡ ድሎችንና የብልፅግና ጉዞን ለማስቀጠል ብሔራዊ ትርክት ግንባታን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ብዝኃነት የሀገራችን ውበት ጥንካሬ ምንጭ በመሆኑ አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጎልበት ሀገርን ወደ አዲስ የብልፅግና ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባም ተናግረዋል።
በዓሉም ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበትና ባሕልና እሴቶች በአደባባይ የምናሳይበት እንዲሁም የውበት ማድመቂያና የቱሪዝም መሠረት የሚሆን ነው ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም