– በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሠለጠናቸውን 450 ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ብቁ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን እያፈራ መሆኑን የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ካሴ ይማም ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሠለጠናቸውን 450 ተማሪዎች ትናንት አስመርቋል።
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ካሤ ይማም በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ብቃት ያለው የሰው ኃይልን በብዛት ለማፍራት እየሠራ ይገኛል፡፡ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ እና ለዓለም ሀገራት አየር መንገዶች በተለያዩ የሙያ መስኮች ብቁ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን እያፈራ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ተማሪዎችን በመቀበል እያሠለጠነ መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡም 300 የሚደርሱ ሠልጣኞችን ከጋቦን ተቀብሎ እያሠለጠነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያን አየር መንገድ ፈጣን እድገት እና የመሪነት ሚና ለማስቀጠል የሚያስፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተያዘው በጀት ዓመት ከሁለት ሺህ በላይ ሠልጣኞችን በተለያዩ የሙያ መስኮች ለማስመረቅ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ በሁለት ዙር ማስመረቅ የተቻለ ሲሆን፤ በአሁኑ ዙር የተመረቁት በተለያዩ የሙያ መስኮች የሠለጠኑ 450 ተማሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የተመረቁት ተማሪዎች 115 በአብራሪነት፣ 84 በአውሮፕላን ቴክኒሺያንነት፣ 123 በበረራ መስተንግዶ ባለሙያነት፣ 128 በፋይናንስ ዘርፍ የሠለጠኑ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ተመራቂ ተመሪዎቹ ከኢትዮጵያ እና ከ12 የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ መሆናቸው ተናግረዋል።
ከመሠረታዊ የአቪዬሽን ሙያዎች በተጨማሪም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በሌሎች ዘርፎች በዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ እና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ከ20 ሺህ በላይ ሠልጣኞችን ማስመረቁን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመዳረሻ እና በአውሮፕላን ብዛት፣ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስመጣት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑን የሚታወቅ ነው፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም