ወጣት መኮንን ብሩ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ነው። ወጣቱ ጥሮ ግሮ ነገውን ብሩህ ለማድረግ ያልሞከረው የሥራ ዘርፍ የለም። በወጣት ክንዱ ሞፈር ጨብጦ አርሷል። አለት ሰንጥቆ ካባ ድንጋይ በማውጣትና በመጫን ላቡን አንጠፍጥፏል። ቀን ሀሩሩ፤ ጠዋትና ማታ ቁሩ ሳይበግረው ድፍን ሁለት ዓመት ጋሪ ላይ ሠርቷል።
ከዛም ፊቱን ወደ ባጃጅ ሥራ ያዞራል። የተለያዩ አስቸጋሪ ባሕሪ ያላቸው ተሳፋሪዎች ታግሶ፤ ሌሊት ወንበዴዎች “ለገንዘብ” ሲሉ ሕይወቱን እንዳይነጥቁት እየሰጋ ቀንና ሌሊት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ባጃጅ ይሠራ ነበር።
ሆኖም በዚህ ሁሉ ልፋትና ውጣ ውረድ የወጣቱ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ሊሻገር አልቻለም። በልፋቱና ድካሙ ልክ ሕይወቱ አልተቀየረም። በኋላ ግን በባጃጅ ሥራ ላይ በነበረበት ወቅት፤ ባጃጅ ተራ ከሚሠሩ ጓደኞቹ ጋር ከዕለት ገቢያቸው መቆጠብ ይጀምራሉ። እንደዋዛ ባጃጅ ተራ የተጀመረው ገንዘብ ቁጠባ ወደ ማኅበርነት ያድጋል።
ወጣት መኮንንም ከጉሮሮው እየቀነሰ ከዕለት ከሚያገኘው ገቢው በማኅበሩ መቆጠቡን አጠናክሮ ይቀጥላል። በቆጠበው ልክ ደግሞ ከገንዘብ ቁጠባ ማኅበሩ ብድር እየወሰደ ይሠራ ጀመር። የተበደረውን ብድር በአግባቡ መልሶ፤ ሌላ ጠቀም ያለ ብድር ደግሞ ይወስድና ይሠራል። እንዲህ እየቆጠበና በቆጠበው ልክ እየተበደረ እየሠራ ዛሬ ላይ የሚሊየነሮችን ተርታ መቀላቀሉን ወጣት መኮንን ይናገራል።
በአብዲ ጉዲና የፋይናንስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን አባልና የብድር ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት መኮንን፤ በዩኒየኑ ቆጥቦ በሚያገኘው ብድር እየሠራ አዳማ ከተማ ቦታ ገዝቶ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት መሥራቱን ይናገራል። አሁን ደግሞ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት በተለምዶ ሲኖ ትራክ የሚባለው ገልባጭ ተሽከርካሪ ባለቤትም እንደሆነ ያስረዳል። ወጣቱ በቀጣይም ጠቀም ያለ ብድር ወስዶ የተለያዩ ግልጋሎት የሚሰጥ ሕንፃ ለመገንባት እቅድ እንዳለው ይናገራል።
“የስኬቴ ምስጢር በኅብረት ሥራ ቆጥቤ ያገኘሁት ብድር ነው” የሚለው ወጣቱ፤ ዩኒየኑ ተበድሮ ሠርቶ ለመለወጥ ዓላማ ላላቸው ወጣቶች ለማበደር በሩ ክፍት ነው። በተለይ ወጣቱ ማኅበረሰብ ብድር አግኝቶ ሠርቶ እንዲለወጥ የሚያደርገው ትብብር ልዩ ነው ሲል ይገልጻል።
በተደጋጋሚ ብድር ከዩኒየኑ ወስዶ ሠርቶ መለወጡን የሚናገረው ወጣቱ፤ አንድ ሰው ዋስ … ወዘተ በሚሉ ቢሮክራሲዎች ሳይጉላላ በቆጠበው ልክ ከዩኒየኑ ብድር ወስዶ መሥራት ከቀኝ ኪስ አውጥቶ ወደ ግራ ኪስ እንደማስገባት የቀለለ እንደሆነ ይናገራል።
ልክ እንደ ወጣት መኮንን ሁሉ በዩኒየኑ የብድር ተጠቃሚ የሆነችው ወይዘሮ ገነት ከፈኔ፤ ኑሮ አልሞላ ብሏት ሠርታ ልጆቿን ለማሳደግ ባሕር አቋርጣ ወደ ዓረብ ሀገር ለሥራ ተሰዳ ነበር። በባዕድ ሀገር ሠርታ ያገኘቻትን ጥቂት ገንዘብ ይዛ ወደ ሀገር ቤት ተመልሳ ፀጉር ቤት ከፍታ ሥራ ትጀምራለች። የፀጉር ቤት ሥራው ከንግድ ቤት ኪራዩ አልፎ የቤቷን ቀዳዳ ሊሸፍን ባለመቻሉ ሥራውን ታቆማለች።
ነገር ግን ወይዘሮ ገነት እጇን አጣጥፋ ቁጭ ብላ የድህነት ምርኮኛ ለመሆን ሕሊናዋ አልፈቀደላትም። በመሆኑም በአንድ ግሮሠሪ በረንዳ ላይ ተከራይታ ቡና ጠጡ ሥራ ጀመረች። ከቡና ጠጡ ከምታገኘው ገቢ በቀን 200 ብር በኅብረት ሥራ ማኅበር ትቆጥብ ጀመር። በኋላም ከማኅበሩ ብድር ወስዳ ሁለት፣ ሦስት ቦታ ላይ የቡና ጠጡ ሥራዋን አስፋፍታ ከራሷ በተጨማሪ ሰው ቀጥራ ማሠራት ጀመረች። ባገኘችው ብድርም ሠርታ ገቢዋ በማደጉ የዘመመ ቤቷን እንደአዲስ አድሳ ዛሬ ላይ በአማረ ቤት ደስተኛ ሕይወት እየኖረች እንደሆነ ትናገራለች።
ቀደም ሲል የወሰደችውን ብድር መልሳ አሁን ደግሞ 400 ሺህ ብር እንደአዲስ ብድር ወስዳ የራሷን ካፍቴሪያ ከፍታ ከራሷ አልፎ ለሌሎች አራት ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረችው ወይዘሮ ገነት፤ ባገኘችው ብድር ዛሬ ላይ የካፌ ባለቤት ሆና የተሻለ ሕይወት እየመራች እንደምትገኝና ከስኬቷ በስተጀርባ ያለው ምስጢር አብዲ ጉዲና ኅብረት ሥራ ዩኒየን እንደሆነ ታስረዳለች።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው ማኅበራት ልምድና ተሞክሯቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ባመቻቸው የመስክ ምልከታ፤ የጋዜጠኞች ቡድን የአብዲ ጉዲና የፋይናንስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየንን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተናል።
በጉብኝቱ ወቅት የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወጋአየሁ ፅጌ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ዩኒየኑ የዛሬ 18 ዓመት በ1999 ዓ.ም ሲቋቋም 12 መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ሁለት ሺህ 040 አባላት አቅፎ በ875 ብር ካፒታል ነው የተቋቋመው። አሁን ላይ 58 መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ከ20 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፤ 450 ሚሊዮን ሀብት፣ 108 ሚሊዮን ኢንቨስትመንት እና 72 ሚሊዮን ካፒታል አፍርቷል ብለዋል።
ዩኒየኑ እንደ አብዛኞቹ የኅብረት ሥራ ፋይናንስ ተቋማት ለኪሳራና ለመክሰም ሳይዳረግ በ18 ዓመት ስኬታማ ጉዞው 142 ሚሊዮን ብር አትርፎ፤ 110 ሚሊዮን ብር ለአባላቱ የትርፍ ክፍፍል ማድረጉን አቶ ወጋአየሁ ይገልጻሉ።
አቶ ወጋአየሁ፤ ዩኒየኑ በሚሰጠው የብድር አገልግሎት ከጉልት ተነስተው ወደ ኢንቨስትመንት የገቡ ብዙ አባላትን ማፍራቱን ጠቁመው፤ ከማኅበሩ አባላት ውስጥ 50 በመቶዎቹ እንዲሁም ከ50 በመቶ በላይ የብድር ተጠቃሚዎች ሴቶች ናቸው። ብዙ ሴቶች ባገኙት ብድር ሠርተው ከመሬት ተነስተው ዛሬ ላይ የናጠጠ ቱጃር ለመሆን በቅተዋል ሲሉ ገልፀዋል።
ዩኒየኑ በኅብረት ሥራ ከዚህ ቀደም ያልተጀመሩ አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበርና የፋይናንስ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝድ በማድረግ አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ለአብነት ብድርን መሠረት ያደረገ ለ10 ሺህ አባላት የመድን ሽፋን ይሰጣል። ከዚህ ውስጥ 21 ሰዎች ያለባቸውን ብድር ሳይከፍሉ ሕይወታቸው በማለፉ ንብረት ተሽጦ ቤተሰቦቻቸው ጎዳና ላይ እንዳይወድቁ 20 ሚሊዮን ብር የመድን ሽፋን መስጠቱን አውስተዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም