ሀገሬ እልፍ የምርቃትና የዝየራ ጥበብ ባለቤት ናት። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት አንዱ ነው:: የሀገር በጎ ውርስ ከሚባሉትም መጪን በፈገግታ መቀበል፤ ሂያጂን በምርቃት መሸኘት ይጠቀሳሉ:: በኅዳር መጨረሻ የሚከበረው የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀንም በፍቅር ሀገር አርባ ምንጭ ላይ በአባቶች ምርቃትና በኢትዮጵያዊነት ወግ ቄጠማ ጎዝጉዘን ተቀብለነዋል::
በዓሉ የሁላችን ኢትዮጵያውያን በዓል ነው:: በኢትዮጵያዊነት ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት የሚያበቃ የነፃነት፣ የእኩልነት እና አንድነታችን ውብ ቀለማችን መድመቂያ ነው:: በርካታ በልዩነት ውስጥ ያበቡ፣ በውበት ውስጥ የደመቁ የተለያዩ ባሕሎችና ወጎች በአንድ መድረክ የሚጎሉበትም ነው::
ስለኢትዮጵያ በአንድነት ለአንድነት መሰባሰብ በእውነትም ልዩ ስሜት የሚፈጥር ትዕይንት ነው:: ይሄ የውሕደትና የአንድነት በዓል በልዩነት ውስጥ ስላለው ውበትና በውበታችን ውስጥ ስላለ አንድነትና አብሮነት ለዓለም የምናሳይበት፤ ነገዎቻችንን በወንድማማችነት ብሩህ የምናደርግበት ነው::
ብዙኃነት በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትም በብዙኃነት ውስጥ ያለውን ክብርና ከፍታ ላለፉት በርካታ ዓመታት ተመልክተናል:: እንደአልቦና አሸንክታብ የሀገር ውበት፣ የሕዝብ ደምግባት በመሆን ለበጎ ስም ስንቅ ሆነዋል:: በአንድ መድረክ ላይ ባማረ አለባበስና በተዋበ ዘዬ ስለኢትዮጵያዊነት መመስከር በብዙ ስሜትን፣ መንፈስን እና አዕምሮ የሚያድስ ነው::
ያለፉትን አስራ ስምንት ዓመታት በአንድነት ተቃቅፈን፣ እየተዋወቅን እና እየተደማመጥን በዓሉን በማክበር እነሆ አስራ ዘጠነኛው ላይ ደርሰናል:: ዘንድሮም የፍቅርና አንድነት ተምሳሌት በሆነችው አርባምንጭ በበጎ ምኞትና በቅን ልብ ተሰባስበን ደምቀናል:: በምስጋና ተጀምረው በምርቃት የሚያበቁ እንዲህ ያሉ በዓላት ዋጋቸው ከፍ ያለ ነው:: ሀገር ከማሻገር፣ ትውልድ ከማነጽና፣ አብሮነትን ከማስቀጠል አኳያ ያላቸው ሚናም የላቀ ነው።
በርግጥ ትናንትም ከራሳችን አልፈን ለሌሎች መትረፍ የቻልን ትልቅ ነበርን:: ብዙ ጥበብን፣ ታሪክን፣ ጀግንነትን አጣምረን የያዝን:: ልዩነታችን ውስጥ ብዙ የአንድነት መንፈስ፣ ብዙ የኅብረ ብሔራዊነት ጌጦች አሉን:: ልዩነታችን ውስጥ ሀገር የሚያሻግር፣ ትውልድ የሚቀርጽ የታሪክና የሥርዓት እሴቶች አሉን::
ብዙኃነታችን ውስጥ እኛነትን የሚያወሳ፣ ግለኝነትን የሚኮንን የሥርዓትና የጨዋነት ልማድ አለን:: ሌሎችን ባቀናና ባነቃ ባሕልና ሥርዓት እሴትና ልማድ ውስጥ ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነን:: በልዩነታችን ስናጌጥ፣ በብዙኃነታችን ጸንተን ስንቆም እና ኅብረ ብሔራዊነታችንን ስናጸና የትናንት ገናና ታሪካችን ይመለሳል፤ በዚያም በብዙ እንደምቃለን::
በርግጥ ተስፋ የአንድነት ቀለም ነው:: የኢትዮጵያ ተስፋ የእኛ አንድነት ነው:: ለልጆቻችን ልናወርስ የምንችለው ትልቁ ውርስ በብዙኃነት ውስጥ አብሮነትን የማስቀጠል ጥበብን ነው:: ፍቅርን ተካፍለን፣ አብሮነትን አስበልጠን ነገዎቻችንን ብሩህ ማድረግ የየዕለት ሥራችን ነው ::
በዓሉ እልፍ የጋራና የአብሮነት ትስስርን የምናጸናበትም ነው:: ከምስራቅ፤ ከምዕራብ፣ ከደቡብ እና ከሰሜኑ ከመጣው ጋር ስለሀገሩ እና ማንነቱ፤ ስለ የነገ ዕጣ ፈንታው እያወጋ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጸናበት ነውና:: ኢትዮጵያውያን በአለባበሳቸው አምረው፣ በቋንቋና ባሕላቸው ደምቀው የሚታዩበት፤ አንዱ ሌላው ላይ የሚፈጥረው የወዳጅነት ስሜት ገዝፎ የሚታይበትም ነው ::
ፍቅር የምንወራረስበት፣ አብሮነትን የምንቋደስበት በብዙኃነት ኢትዮጵያዊነትን የምናስጠብቅበት የፍቅርና አንድነት ቀን ነው:: በእጃችን እቅፍ አበባ፣ አንደበቶቻችን ምስጋናና ምርቃትን ይዘን በዓሉን ትላንትን በምርቃት እንደሸኘን፤ ዘንድሮን በውዳሴ እየተቀበልነው ለሚመጣው ዓመት ለተሻለ ድምቀት እንጠብቀዋለን:: እንኳን ከትናንት በተሻለ በብዙኃነት ለሚያስተሳስረን፤ ኅብረ ብሔራዊነታችንን ለማጽናት ትልቅ ፋይዳ ላለው የሁላችን ኢትዮጵያውያን በዓል በሠላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም