የስፖርት ፌዴሬሽኖች ፈተናና ያልተመለሰው የመሠረተ ልማት ጥያቄ

የኢትዮጵያ ስፖርት በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ የስፖርት መሠረተ ልማቶች እጥረት መሆኑ ይገለጻል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በየአካባቢው አነስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን እየገነባ

ይገኛል:: ይሁን እንጂ ካለው ሰፊ ፍላጎት አንፃር ብዙ ይቀራል:: ይህ እንደ ማኅበረሰብ አቀፍ ስፖርት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በበርካታ የስፖርት አይነቶች በፕሮፌሽናል ወይም በኢሊት ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ስፖርተኞችና ፌዴሬሽኖች ውድድርም ሆነ ልምምድ የሚሠሩባቸውን ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶች ማግኘት አሁንም አስቸጋሪ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ::

በዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት ባልቻሉና ግንባታቸው ባልተጠናቀቀ ስታዲየሞች ምክንያት ብሔራዊ የስፖርት ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች ዛሬም ከፍ ያሉ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ተቸግረዋል:: ለዚህ ሁነኛው ማሳያም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወንዶች ቡድን ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎቹን በሌሎች ሀገራት ለማካሄድ መገደዱ ሁሉም የሚያውቀው ነው:: ይህም ጉዳቱ ከስፖርታዊ ውጤት መጥፋት አንዱ ምክንያት ከመሆን የዘለለ ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋናው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን በውጭ ሀገራት ለማጫወት በመገደዱ ብቻ ባለፉት አራት ዓመታት አስቸጋሪ ሁኔታ እያሳለፈ ይገኛል:: የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሙዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረማርያም እንደሚያስረዱት፣ ፌዴሬሽኑ በካፍና ፊፋ ግብረመልሶች መሠረት እድሳት ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ስታዲየሞች አስፈላጊውን ደረጃ እንዲያሟሉ ለሚመለከተው አካል ለባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር አሳውቀዋል::

በተለያዩ ጊዜያት ከፊፋ እውቅና ያላቸው ባለሙያዎችን እንዲሁም የካፍ ገምጋሚ ቡድኖችን በመጋበዝም በተለይም የአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ማስተካከያዎችን እንዲደረጉ ፌዴሬሽኑ ሲደግፍ ቆይቷል:: ያም ሆኖ ችግሩ አልተቀረፈም:: በዚህ ምክንያት ፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቡድኑ በውጭ ሀገር ለሚያደርገው ለአንድ ደርሶ መልስ ጨዋታ ከ8 እስከ 10 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደርጋል:: ፌዴሬሽኑ በእነዚህ አራት ዓመታት በሀገር ውስጥ ማድረግ ያለበትን ጨዋታ በውጭ ሀገራት በማድረጉ ለዋናው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ብቻ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥቶ ኪሳራ እንደደረሰበት የፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች መናገራቸው ይታወሳል::

ከስፖርት መሠረተ ልማት ችግር ጋር ተያይዞ ከባድ ፈተና ውስጥ እንደሚገኙ የሚጠቁሙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፣ አሁን ላይ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሁም ለውድድር የሚሆኑ መም (ትራክ) ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ::

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለፃ፣ ለበርካታ ዓመታት የሀገር ውስጥ ውድድርን ጨምሮ አትሌቶች ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጅት ሲያደርጉበት የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም በእድሳት ምክንያት ከሦስት ዓመታት በላይ ዝግ ሆኖ ይገኛል:: የአንጋፋውን ስታዲየም ወደ እድሳት ሲገባ እሱን በጊዜያዊነት የሚተካ አማራጭ መዘጋጀት ነበረበት፣ ይህ ካልሆነም እድሳቱ በጊዜ መጠናቀቅ ነበረበት:: የስታዲየሙ እድሳት በቅርቡ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ ቢኖርም አሁንም ድረስ አትሌቲክሱ የሚፈልገው የመሮጫ መም ሥራ አልተጀመረም:: የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳው ሣር ጉዳይ እልባት ካልተገኘለት ደግሞ መሙ እንደማይሠራ እድሳቱን በማከናወን ላይ ከሚገኘው የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ለፌዴሬሽኑ አሳውቋል:: ይህም የመጫወቻ ሜዳው ሣር ሳይነጠፍ የመሮጫ መም ጥገናውን ማከናወን ለብልሽት ሊዳርገው ይችላል በሚል ምክንያት ነው:: በዚህም የተነሳ የአትሌቲክሱ አንገብጋቢ ችግር መፍትሔ ሳያገኝ ቀጥሏል::

ለትልልቅ ሀገር አቀፍ ውድድሮች እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ የሆኑ መሠረተ ልማቶች አለመኖራቸው ትኩረት ከሚሰጣቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተጨማሪ ተፅዕኖው በሌሎችም ላይ አርፏል:: ከነዚህ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ነው:: አካዳሚው የአዲስ አበባ ስታዲየም ወደ እድሳት ከገባ ወዲህ በሚችለው አቅም የተለያዩ ውድድሮችና ልምምዶች እየተደረጉበት ነው:: ይህ ደግሞ በአካዳሚው መደበኛ የወጣቶች ሥልጠና ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳደሩን በአካዳሚው የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አላምረው ማሞ ይናገራሉ::

እንደ አቶ አላምረው ማብራሪያ፣ አካዳሚው የማዘውተሪያ ስፍራን በተመለከተ እንደ ሀገር ያለውን ችግር ተረድቶ ለማገዝ የተቻለውን አድርጓል:: ይሁን እንጂ በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች በሳምንት ስድስት ቀን ጠዋትና ማታ ሠልጣኞቹን ልምምድ የሚያሠራ ከመሆኑ አንጻር መደበኛ የወጣቶች ሥልጠናውን ለማከናወን ተቸግሯል:: ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የመሮጫ መም በአትሌቲክስ ሠልጣኞቹ ብቃት ላይ ጫና እያሳደረ በመምጣቱም እድሳት የሚፈልግበት ደረጃ ላይ ይገኛል:: ይህንን በገንዘብ ለመተመን የገበያ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም ከዚህ ቀደም ከወጣው ወጪ በመነሳት ግን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያስፈልግ ይችላል:: ይህንን በተመለከተ አካዳሚውን በበላይነት ለሚያስተዳድረው የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጥያቄ ቀርቦም ምላሽ እየተጠበቀ ነው::

የአካዳሚው የመሮጫ መም በመጎዳቱ የአካዳሚውን ወጣት አትሌቶች ጨምሮ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጅት የሚያደርጉ ብርቅዬ አትሌቶቻችንንም ለጉዳት እየዳረጋቸው መሆኑን በመግለፅ፣ መሙ ከተዘጋጀበት ዓላማ አንጻር በዚህ ደረጃ መገኘቱ መጪው ጊዜም አሳሳቢ እንደሚሆን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ሌላ ስጋት አላቸው::

በስፖርት መሠረተ ልማት እጥረት እየተፈተኑ የሚገኙ የስፖርት ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች ይህ ችግራቸው ባለመቀረፉ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። በራሳቸው ተነሳሽነት መፍትሔ ያሉትን ሁሉ ሲሞክሩ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከችግሩ ስፋት አንጻር የአዲስ አበባ ስታዲየም የመም እድሳት በሀገር ውስጥ ኮንትራክተር የማይሠራ እንደመሆኑ ክፍያ የሚፈጸምበትን የውጪ ምንዛሪ በተመጣጣኝ ክፍያ አቅርቦ ሥራው በፍጥነት እንዲጀመር ለማድረግ ለኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሀሳብ አቅርቧል። በዚህም መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ 16 ሚሊዮን ብር ገደማ ወደ ፌዴሬሽኑ የባንክ ሂሳብ አስገብቶ የውጪ ምንዛሪውን ለማዘጋጀት በሂደት ላይ እያለ ከተለያዩ የአሠራር ችግሮችና በእግር ኳስ ሜዳው ሳር ንጣፍ መዘግየት ምክንያት መጓተት እንዳጋጠመው አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል::

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በየጊዜው በተለይም የአዲስ አበባ ስታዲየም አስፈላጊውን መስፈርት እንዲያሟላ እንዲሁም የእግር ኳስ ሜዳ ሣር ንጣፉ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲገነባ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ችግሩ በአጭር ጊዜ እንዲቀረፍ ጥረት ሲያደርጎ ቆይቷል:: ይሁን እንጂ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ቀድሞ ከነበረው አንጻር ግብረመልስን በመቀበልና አብሮ በመሥራት ረገድ አሁን ላይ ለውጥ ቢኖርም ውጤት ግን እየታየ እንደማይገኝ ነው አቶ አብርሃም የሚያስረዱት::

ለአንገብጋቢው የማዘውተሪያ ስፍራ ችግር የራሱን የመፍትሔ ሃሳብ ይዞ ወደ ርምጃ መግባት የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ በርካታ ክለቦች በስሩ እንደመገኘታቸው ለውድድሮችና የታዳጊዎችን ሥልጠና ለማካሄድ የመሠረተ ልማት ችግር አለበት። በዚህ ምክንያት የባለድርሻ አካላትን ሰብስቦ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በማዘጋጀት በጃንሜዳ የውድድርና ልምምድ የሚሆን የአሸዋ መም ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል::

በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ሁሉም ፌዴሬሽኖችና የስፖርት ማኅበራት ደረጃቸውን በጠበቁ የመሠረተ ልማት ችግሮች ሲፈተኑ ኖረዋል:: ዛሬም በዚሁ ፈተና ውስጥ ይገኛሉ:: ሰፊ እንቅስቃሴና ትልቅ ትኩረት የሚሰጣቸው የእግር ኳስና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ግን ይበልጥ እየተፈተኑ የሚገኙት ለዓመታት ሲጠቀሙበት የቆየው አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ወደ እድሳት ከገባ ወዲህ ባሉት ያለፉት አራት ዓመታት ነው::

የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ሲጀመር በአጭር ጊዜ ምናልባትም በአንድ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር:: ይሁን እንጂ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳው ሣር አስፈላጊውን መስፈርት ይዞ ለማጠናቀቅ በየጊዜው ችግር ሲገጥመው ታይቷል:: የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳትና የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታን የሚመራው የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በተለይም የአዲስ አበባ ስታዲየምን እድሳት በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ጠቁሟል:: ይሁን እንጂ የስታዲየሙ እድሳት በዚህ ጊዜ ይጠናቀቃል የሚል ቁርጥ ያለ ነገር አላስቀመጠም:: ይህም ፌዴሬሽኖቹ ያለፉት ዓመታት የመሠረተ ልማት ጥያቄያቸው በአጭር ጊዜ ላይመለስ ይችላል የሚል ስጋታቸው እንዲቀጥል አድርጎታል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You