ከተሜነትና ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃም እየሰፋ ይገኛል:: በከተሞች ያሉ መሠረተ ልማቶችንና አገልግሎቶችን ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትም እየተበራከተ ነው:: ከተሜነት የማይቀር ክስተት ስለመሆኑና ይህን ፍልሰት ለማስተናገድ ከወዲሁ ዝግጁ ሆኖ መገኘት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ::
በሀገሪቱ የከተሞች ብዛትም፤ ስፋትም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ስለመሆኑ መንግሥትና የዘርፉ ባለሙያዎችም አስረግጠው ይገልጻሉ:: ለማይቀረው ከተሜነትና ክተማ በከተማ ልማት ሥራ በትኩረት መንቀሳቀስ በእጅጉ አስፈላጊ ስለመሆኑም ያሳስባሉ::
በሀገሪቱ እስከ አሁን የታየው ግን የተገላቢጦሽ ስለመሆኑ ባለሙያዎች ይጠቀሳል:: ከተሞች እየቀደሙ እኛ እየተከተለን ነው ያለነው ሲሉ አንድ የዘርፉ ባለሙያ የተናገሩትም ይህንን ያመለክታል:: በትላልቅ ከተሞች አቅራቢያዎች የሚታየው ፕላን ላይ ያልተመሠረተ የከተማ መስፋፋት ይህንኑ ያስገነዝባል::
በከተሞች የሚታየው ሕገወጥ ግንባታ፣ ከፍተኛ የፕላን ጥሰት መስተዋሉ ከተማን ለመምራትም ሆነ ከተሜነትን ለማስተናገድ በአጠቃላይ ከተሞች ስር የሰደደ ችግር ውስጥ እንዲገቡ እያደረጉ ናቸው:: አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ የሀገሪቱ ከተሞች አሁን ለገቡበት የኮሪደር ልማት አንዱ ምክንያት ፕላን መሠረት ተደርጎ አለመገንባታቸው ወይም የፕላን ጥሰት መሆኑ ይገለጻል::
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በከተማ አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ላይ ለሚሠሩ አመራሮች በመሬትና ካዳስተር፣ በከተሞች ፕላን፣ በአገልግሎት ማዘመን፣ በከተሞች ገቢና በምግብ ዋስትና ሥራዎች ላይ ባዘጋጀው ችግር ፈቺ ሥልጠና ላይም እነዚህ ችግሮችና ችግሮቹን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠቁመዋል::
በአዳማ ከተማ በተካሄደውና የሚኒስቴሩ፣ የክልል የከተማና መሠረተ ልማት እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ አመራሮች በተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል:: በዛሬው የመሠረተ ልማት ዓምዳችን በመድረኩ ከተነሱት መካከል በተለይ በከተማ ፕላንና መሬት ላይ የተነሱትን ሀሳቦች ይዘናል::
መድረኩን በንግግር የከፈቱት በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፋንታ ደጀን በሀገሪቱ ሰፊ የክትመት ምጣኔ እንደሚታይ ጠቅሰው፤ ‹‹ይህን የሚመጥን ሥራ መሥራት ከእኛ ይጠበቃል›› ሲሉ ያመለክታሉ:: የሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት እየጨመረ እንዲሁም ሕዝቡ ወደ ከተሞች እየተሰበሰበ ነው፤ የከተሞቹ ብዛትም ከ2 ሺ 500 በላይ መድረሱንም ይጠቁማሉ::
ከተሞቹ በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችና ጥቂት ባለሀብቶች የሚኖሩባቸው መሆናቸውንም አመልክተው፣ ‹‹እነዚህን ከተሞች በተቻለ መጠን ለሰው ልጅ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግና ለዚህም ከእኛ ብዙ ይጠበቃል›› ይላሉ:: በበጀት ዓመቱ በሚኒስቴሩ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሠራባቸው መካከል ፕላን አንዱ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ከተሞች በፕላን መመራት እንዳለባቸው ይናገራሉ:: በሀገሪቱ አሁንም ፕላን የሌላቸው ከተሞች ስለመኖራቸውም ጠቁመው፣ የገጠር የቀበሌ ማዕከላት ጭምር ስኬች ፕላን ሊኖራቸው እንደሚገባ ያስገነዝባሉ::
በ2017 በጀት ዓመት ሌላው በትኩረት መሠራት ያለበት መሬት ነው:: መሬት በሚፈለገው ልክ እየተመዘገበ አለመሆኑ በመድረኩ የተነሳ ሲሆን፣ የመሬት መመዝገብ ከተሞችን ከተለያዩ ያልተገቡ ፍላጎቶች እንደሚያወጡ ተመላክቷል:: በመድረኩ በሀገሪቱ ከተሞች እየተካሄደ ያለውን የኮሪደር ልማት እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባም ተጠቁሟል::
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማት በከተሞች ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል መገንዘብ ይቻላል:: በኮሪደር ልማቱ ለመጪው ትውልድ ትልቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል:: በከተሞች የሚታየውን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት አንድ ቦታ ላይ ዋጋ መክፈል የግድ ይሆናል፤ አሁን ያለው ትውልድ በከተማ መልሶ ልማቱ ዋጋ እየከፈለ ነው:: ለትውልድ ዕዳ እያወረሱ መሄድ አይገባም፤ የሀገሪቱ ከተሞች ከተማ መምሰል አለባቸው:: አዲስ አበባ በፕላኗ መሠረት ለምታ ቢሆን ኖሮ አሁን የሚታየው ችግር ባልታየ ነበር::
አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ሌላው ከተሞች በትኩረት ሊሠሩበት የሚገባ ጉዳይ ነው:: በዚህ ዘመን ሰው ቤቱ ሆኖ ጉዳዩን መፈጸም መቻል እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበው፣ በእዚህ ልኩ ካልተሠራ በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል እርካታ ማምጣት እንደማይቻል ያመለክታሉ::
ስምንት ከተሞች አገልግሎት ማዘመን መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ ሌሎች ይህንኑ መንገድ እየተከተሉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ:: አገልግሎት ማዘመን ሰው የተማረረበትን የሥነ ምግባር ችግር ለመፍታት አንድ መሣሪያ በመሆኑ ዲጂታላይዜሽን ላይ በስፋት መሠራት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት::
‹‹ችግር ፈቺ ሥልጠና በመሬትና ካዳስተር እንዲሁም በከተሞች ፕላን ሥራዎች›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የከተማ ፕላንና አከታተም መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ገነት ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፤ የሀገሪቱ ከተሞች የክትመት ምጣኔ 5 ነጥብ 4 በመቶ አየጨመረ መሆኑን ይጠቅሳሉ:: ይህም ፈጣን የሚባል ምጣኔ መሆኑን አመልክተው፤ ይህን እድገት የሚመጥን ሥራ መሠራት እንዳለበትም ያስገነዝባሉ::
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ በአከታተም ሥርዓት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል:: የከተሞች እድገት ተመጣጣኝ አይደለም፤ አዲስ አበባ በሀገሪቱ ሁለተኛ ከተማ ተብለው ከሚታወቁት በአስር እጥፍ ትበልጣለች:: የሀገሪቱ ከተሞች የአከታተም ሥርዓት ሲታይም ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው፤ የአከታተም ሥርዓቱ የገጠር ትናንሽ ከተሞችን ለማፍራትም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል:: የገጠር ቀበሌ ማዕከላት ላይ እየተሠራ ያለውም ለዚህ ነው:: በዚህ ዓይነት ሁኔታ ብዙ ከተሞችን መፍጠር ይቻላል:: የእስከ አሁኑ አካሄድ የተወሰኑ ከተሞች ላይ ያተኮረ ነው:: ይሄ ደግሞ ሃገሪቱ ከምትከተለው ሥርዓት ጋርም አይጣጣምም፤ በመሆኑም በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ ላይ መሠራት ያስፈልጋል::
‹‹ይህም በመሠረታዊነት ወደ ከተማ ፕላን ይወስደናል›› ያሉት ወይዘሮ ገነት፣ ከተሞች ወደ ጎን መስፋት እንደሌለባቸው ለእዚህም ያደጉ ከተሞችን ተሞክሮ መመልከት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ:: ሕንጻ መሥራት ብቻውን ከተማን ከተማ አያደርገውም፤ ከከተማው መሬት 40 በመቶ ለሕንጻ፣ 30 በመቶው ለአረንጓዴ ስፍራና 30 በመቶው ለመሠረተ ልማት መዋል አለበት ሲሉም ይናገራሉ::
የከተሞች በፕላን አለመሠራት ሀገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ ስለመሆኑ እሳቸውም ያመለክታሉ:: ‹‹ፕላኖች መሬት ላይ ወርደው ተሠርቶባቸው ቢሆን አሁን የምናየውን ፈተና ባላየን ነበር›› ይላሉ:: ሚኒስቴሩ ብሔራዊ ፕላን አለው፤ ለዘጠኝ ክልሎች ሠርቶ ሰጥቷል፤ ሦስት ክልሎች ይቀሩታል፤ ለየክልሉ ከተሞች የተሠሩ ፕላኖች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ:: ለየክልሎቹ የተዘጋጁ ፕላኖች በተቀናጀ አግባብ መሬት ላይ ከወረዱ የምንፈልጋቸውን ከተሞች እውን ማድረግ እንችላለን ሲሉም ነው የተናገሩት::
ሥራ አስፈጻሚዋ እንዳሉት፤ በሀገሪቱ ከሁለት ሺ 500 በላይ ከተሞች አሉ:: ከእነዚህ ውስጥ 90 በመቶው በፕላን የሚመሩ ሲሆኑ፣ የተቀሩት በፕላን መመራት ላይ ችግር ይታይባቸዋል:: ፕላናቸውም ያልተከለሰ ከተሞችም ይገኛሉ:: ከተሞች ባደጉ ቁጥር በፕላን ካልተመሩ ለማስተዳደርም ያስቸግራሉ፤ ከተሞችን በፕላን ላይ ተመሥርቶ ካልሠራን አሁን የሚገነባው ከተሞች ራሳቸው ነገ የሚፈርሱ ሊሆኑ ይችላሉ:: የገጠር ቀበሌዎችንና ማዕከላትንም በፕላን መምራት ያስፈልጋል:: ፕላናቸው ሲሠራ ነገ ከተማ እንደሚሆኑ ታሳቢ ተደርጎ መሆን ይኖርበታል:: ከተሞች የችግር ምንጭ እንዳይሆኑ፣ አሁን በከተሞች የሚታዩ ችግሮች እንዳይደገሙ ለማድረግ በፕላን ላይ ተመሥርተው እንዲለሙ ማድረግ ይጠበቃል::
በከተሞች ከፕላንና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ችግር ለመፍታት በአዲስ አበባ ተጀምሮ ወደ ክልል የተስፋፋውን የኮሪደር ልማት እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባም ሥራ አስፈጻሚዋ ያመለክታሉ:: በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን የኮሪደር ልማት ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ 30 ከተሞችም እንዲስፋፋ መደረጉ በመድረኩ ይጠቁማሉ:: እነዚህ ከተሞች ወደ ኮሪደር ልማቱ ገብተው እንዲሠሩ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው:: ከተሞቹ እያከናወኑ ያሉትን ሥራ በተመለከተ ሪፖርት በማድረግ ላይ ግን ክፍተት ይስተዋላል፤ 14 ከተሞች ብቻ ናቸው ሪፖርት እያደረጉ ያሉት ይላሉ::
የኮሪደር ልማቱ እየተካሄደባቸው ከሚገኙ ከተሞች መካከል ሀዋሳ፣ ዲላ፣ ይርጋለም፣ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ ሻሸመኔ፣ ሮቤ፣ ሸገር ሲቲ ከተሞች፣ ባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረብርሃን፣ ድሬዳዋ በኛ ይታወቃሉ ሲሉ ወይዘሮ ገነት ይጠቅሳሉ:: በዚህ ሥራ ፕላን፣ ከተማ መሠረተ ልማት፣ የመሠረተ ልማት ቅንጅት ይከናወናሉ፤ እነዚህ በጋራ መመራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ጠቅሰው ልማቱ በአንድ ሚኒስትር ዴዔታ እንዲመራ መደረጉንም ይናገራሉ::
የኮሪደር ልማት መንገድ የማስፋት ሥራ ብቻ አይደለም:: ከመንገድ ጋር ብቻ አያይዞ ማየት የሚለው መታረም ይኖርበታል:: መንገድ ከማስፋት በላይ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል:: ይህ ልማት በፕላን መመራት እንዳለበት ገልጸው፣ አንዳንድ ከተሞች ወደ ልማቱ ለመግባት እየፈሩ ናቸው፤ ሥራው በምዕራፍ በምዕራፍ ሊካሄድ የሚችል ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ:: አንዳንዶቹ ደግሞ ከፍተኛ በጀት የመደቡበት ሁኔታ እንደሚታይም ያስረዳሉ::
የኮሪደር ልማቱን አስመልክቶ ያነጋግርናቸው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ፋንታ ደጀን የኮሪደር ልማት ከተሞች ፕላናቸውን ጠብቀው ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚሠራ መሆኑን ይገልፃሉ:: የትራፊክ ፍሰታቸው የተሻለ ኢንዲሆን፣ መንገዶቻቸው ውበታቸውን የጠበቁና የተስተካከሉ እንዲሆኑ በተለይ ለተተኪው ትውልድ ጥሩ ከተማ ማስተላለፍን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሰፋ ተደርገው የሚሠሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ::
እርሳቸው እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ የተጀመረውን ልማት ወደ ሀገሪቱ 30 ከተሞች በማስፋት እየተሠራ ነው:: ከተሞቹም ልማቱን ለማካሄድ ቁርጠኝነቱ አላቸው፤ ልማቱ የተወሰነ ካፒታል የሚጠይቅ መሆኑ ከተሞቹ ሁሉንም ሥራ በአንዴ መሥራት ባይችሉም በአቅማቸው ልክ ለመሥራት የተወሰነውን ለመሥራት ጀምረዋል:: ለእዚህም የአዲስ አበባን ተሞክሮ ቀምረዋል::
ልማቱን ከሚያካሂዱት መካከል ሪፖርት እያደረጉ ያሉት 14 ብቻ ናቸው ተብሏልና ይህ ለምን ሆነ? የትደረሳችሁ አይባልም ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ‹‹ሪፖርት ማድረግ አንድ ነገር ነው፤ መሥራት ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው፤ ሁሉም እየሠሩ ናቸው፤ ሪፖርት የማያደርጉ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሪፖርት እንዲያደርጉ ሄደን መደገፍ ይኖርብናል›› ሲሉ ይናገራሉ:: በሁሉም ከተሞች ሥራው ተጀምሮ እየተካሄደ መሆኑንም ይገልፃሉ::
ልማቱን የሚያካሂዱበት የፋይናንስ ምንጭ የራሳቸው የውስጥ ገቢ መሆኑንም ጠቅሰው፣ መንግሥት የሚደግፍበት ሁኔታም እንዳለም ይናገራሉ:: አንዳንድ ክልሎች ላይ የክልል መንግሥታት እየደገፉ ያለበት ሁኔታም እንዳለ፤ ዋናው ግን በራሳቸው የውስጥ ገቢ፣ ኅብረተሰቡን በማስተባበር የሚሸፉኑት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት::
እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ የኮሪደር ልማቱ እየሰፋ እንዲሄድ ይደረጋል፤ እኛ 30 ከተሞች እኛ የምንከታተላቸው ሆነው እንጂ ሁሉም ከተሞች ልማቱን መተግበር ጀምረዋል:: የጀመሩ፣ በእቅድ ላይ ያሉ ሲሆን አቅም የሌላቸው የትናንሽ ከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች ይህን መሥራት ሊያቅታቸው ይቻላል:: እንደ ችግኝ ተከላ ያሉትን ግን እየሠሩ ናቸው፤ የሀገሪቱ መንግሥት ይህን የኮሪደር ልማት ሥራ ወጪ ሊሸፍን አይችልም፤ ኅብረተሰቡ በየአቅራቢያው ያለውን አካባቢን የማፅዳት ሥራ ቢሠራ በራሱ ትልቅ ነገር ነው::
ከተሞችን ከፕላን ወጪ ያደረጋቸው ችግር ፕላን ያለመኖር ወይስ በፕላን ያለመሥራት ችግር ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ‹‹የችግሩ ምንጭ የፕላን ጥሰት መሆኑን ያመለክታሉ:: ሁሉም ከተሞች ፕላን ቢኖራቸውም ትልቁ ችግር የፕላን ጥሰት ነው:: ከተሞች ሲመሠረቱ ቶሎ በፕላን እንዲመሩ ያለማድረግ ሁኔታም ይታያል:: በተለይ በገጠር ማዕከላት አካባቢ ይሄ ችግር በስፋት ይስተዋላል:: በቀጣይ ከተሞች ሲቆረቆሩ በፕላን እንዲመሩ ማድረግ ላይ በትኩረት ይሠራል::
በመድረኩ በሥልጠና ትኩረት የተሰጠባቸውን ዘርፎች የተመለከቱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ቀርበው በሚመለከታቸው አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል:: ከከተማ ፕላን ዝግጅትና ትግበራ አኳያም ባሉ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦች ተንሸራሽሯል:: የከተማ ፕላን የከተማ እድገትና ልማት የሚያፋጥን የልማት እቅድ መሆኑን በመረዳት ኅብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በሚገባ በማሳተፍ አቅምን ያገነዘበ የከተማ ፕላን በጥራት እንዲዘጋጅና እንዲተገበር ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፤፤
መድረኩ ከተሰጡ አቅጣጫዎች መካከልም የከተሞችን ፕላን ከክልላዊ ልማት ስፓሻል ፕላን ጋር አናቦ መዋቅራዊ ፕላን በማዘጋጀት መተግበር እንደሚገባ፣ የገጠር ቀበሌ ማዕከላትን የቀጣይ ከተሞች መሠረት ስለሚሆኑ ስኬች ፕላን በማዘጋጀት መተግበር ሽፋንን ማሳደግ፣ የከተማ ፕላን መረጃዎችን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ተደራጅተው እንዲቀመጡና ለተጠቃሚ ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻል፤ የኮሪደር ልማትን በፕላን እንዲመራ ማድረግና የፕላን ማስፈጸሚያነት መጠቀም የሚሉት ይገኙበታል::
ኃይሉ ሣሕለድንግል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም