እንደመነሻ …
ትንሹን ልጅ አጥብቃ የያዘችው የኩፍኝ ሕመም እንደዋዛ ጨክናበት ከርማለች:: እሱን ጨምሮ የእህቶቹ ፊትና ገላ በሽፍታ ተውርሷል:: በእነሱ ግን ክንዷ አልበረታም:: እንደነገሩ ከራርማ ተሸልማ ሄዳለች:: ሕመሙ ሁሌም በልጆች ላይ ተለምዷልና ማንም ነገሬ ያለው የለም::
ወጋየሁ በኩፍኝ ጉዳይ እንደተቸገረ ነው:: የገላው ምልክት ውሎ አድሮ ቢከስምም ሕመሙ አልተወውም:: ችግሩ በዚህ ብቻ አልበቃም:: ከቀናት በኋላ ዓይኖቹ ሙሉ ለሙሉ ከብርሃን መጋረዳቸው ታወቀ:: ትንሹ ልጅ እንደልቡ ማየትና መራመድ ተሳነው::
ኩፍኝ ማለት ለአካባቢው ብርቅ ሆኖ አያውቅም:: ሁሌም ልጆች ታመው ይድኑበታል:: እስከዛሬም እንደወግ ባሕሉ የተለመደው ተደርጎ ኩፍኝዋ በስንብት ትሸኝ ነበር:: በወጋየሁ የሆነው ግን አዲስና ያልተለመደ ነው:: ከገላው ለቃ በዓይኖቹ ላይ መዋሏ ሁኔታውን አስደንጋጭ አድርጎታል:: አጋጣሚው ቤተሰቡን ሲያሳስብ ሲያስጨንቅ ከረመ:: የዛኔ በአካባቢው የረባ ሕክምና አልነበረም:: የሐረሯ አንጫር ወረዳ ‹‹በዴ›› ከተማም ሕክምናውን ችላ የምታሸንፈው አል ሆነም::
ጥያቄው …
ውሎ አድሮ ወጋየሁ ዓይኑን የጋረደው ነጭ ነገር ጥቂት የገፈፈ መሰለ:: ይህኔ ትንሹ ልጅ በግምት መራመድና ሰው መለየት ጀመረ:: በአቅሙም የቻለውን ለማድረግ እየሞከረ ቆየ:: እንዲህ መሆኑ ግን እይታውን አልመለሰም:: እኩዮቹ ትምህርት ቤት ሲገቡ እሱ ከዕድሉ ታቅቦ ከቤት ሊውል ግድ አለው:: ይህ አጋጣሚ ለወጋየሁ ቀላል አልሆነም::
የእሱ ከቤት መቅረት ሆድ ያስባሰው ብላቴና ለምን ሲል አባቱን ደጋግሞ ጠየቀ:: ምላሹ አጭርና ግልጽ ነበር:: ወጋየሁ ዓይኖቹ ከእይታ ተጋርደዋል:: ከእኩዮቹ እኩል ተቀምጦ ቀለምና ቁጥር መለየት አይቻለውም:: ብቸኛው አባወራ ባለቤታቸውን በሞት አጥተዋል:: ከእሱ በላይ ብዙ የሕይወት ጥያቄዎች ይጠብቋቸዋል::
አባት በብዙ ምክንያት ልጃቸውን ወደ ተሻለ ሕክምና ለመወሰድ አልፈጠኑም:: የቤተሰቡ ሙሉ ኃላፊነት በእሳቸው ትከሻ ወድቋልና ተቸግረዋል:: እንዲያም ሆኖ ወጋየሁ ዝም አላለም:: አባቱ እንዲያሳክሙት ይወተውታል:: እሳቸው ስለእሱ ተስፋ ቆርጠዋል:: ዓይኑ ታክሞ እንደማይድን እየነገሩት ነው:: የአካባቢው ግንዛቤና የአቅሙ ጉዳይ ደግሞ ማንንም የሚያስወቅስ አልነበረም ::
በጊዜው ኩፍኝ ይሏት ሕመም የበዛ ችግር አላት ብሎ የሚያምን የለም:: ጊዜው እየገፋ፣ ቀኑ እየነጎደ ነው:: የወጋየሁ ባልንጀሮች ከትምህርት ውለው ይገባሉ:: የትንሹ ልጅ ጥያቄ አላቆመም:: የትምህርት ጉጉቱ ደጋግሞ ለምን ሲል ጥያቄውን እንዲገፋበት አስገድዷል::
በሐኪሞች ፊት…
ወጋየሁ ዓይኖቹ ክፉኛ መታመማቸው ሲገባው በአባቱ ላይ ጫና ማሳደር ያዘ:: ሁሌም መታከም እንዳለበት እየጨቀጨቀ አስጨነቃቸው:: አሁን አባት ጥያቄውን ችላ ብለው ዝም አላሉም:: ከሐረር ወጣ ብላ ወደምትገኝ መተሐራ ከተማ ወሰዱት:: ከስፍራው ደርሶ ምርመራው ተካሄደ:: ጉዳዩ በሆስፒታሉ አቅም የሚቻል አልሆነም:: ወደተሻለ ሕክምና ተጻፈለት::
ቀጣዩ ጉዞ አዳማ ላይ ሆነ:: የወጋየሁ ሕክምናና ውጤት ተመሳሳይ ሆኖ ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ሊላክ ግድ አለ:: በሚሊኒየሙ 2000 ዓ.ም:: አባትና ልጅ አዲስ አበባ ከሆስፒታሉ ደርሰው ሕክምናው ተጀመረ:: የተገኘው ውጤት ከቀድሞዎቹ ምርመራዎች የተለየ ነበር:: የወጋየሁ ሁለቱም ዓይኖች በዓይን ብሌን ጠባሳ መጎዳታቸው ተረጋገጠ:: ይህ እውነት ለእንግዶቹ አባትና ልጅ አዲስ ቃል ነበር:: ከዚህ ቀድሞ ዓይኖች በጠባሳ እንደሚጎዱ ሰምተው አያውቁም::
በወቅቱ ወጋየሁ ልጅ ቢሆንም ሐኪሞቹ ስለ ዓይን ብሌን ንቅላ ተከላ በትኩረት ማውራታቸውን ያስታውሳል:: ብዙ ታካሚዎች እንዳሉ፣ ብሌኑ ከሌሎች እንደሚለገስና ለጋሾቹም በቂ አለመሆናቸውን ጭምር ሰምቷል::
ስለሕክምናው ጥቂት ግንዛቤ የጨበጠው ልጅ የሰማውን በውስጡ ይዞ ዓይኖቹን መታከምና መዳን እንዳለበት ወሰነ:: ከታሰበው ለመድረስ መመዝገብና ወረፋ መያዝ የግድ ይላል:: ወጋየሁ ሙሉ ምዝገባውን አጠናቆ ወረፋውን መጠበቅ ጀመረ:: ተመልሶ ወደ ትውልድ ሀገሩ አልሄደም:: የክርስትና አባቱ አዲስ አበባ ናቸው:: ኑሮው በቤታቸው ሆነ::
ብርሃን አልባው ጉዞ…
ወጋየሁ ውሎአድሮ የመንገዱን ፈታኝ እርምጃዎች መጋፈጥ ያዘ:: እግሮቹ ሜዳ ገደሉን፣ ጉድጓድ፣ ጉድባውን ተላመዱት:: እየወደቀ፣ እየተነሳ፣ እየሳቀ፣ እያዘነ የብርሃን አልባውን ጎዳና ተራመደበት:: አንዳንዴ የአንድ ዓይኑ ፈዛዛ ብዥታ ለጉዞው ያግዘዋል:: ያለነጭ በትር ባልተመቸው መንገድ ይመላለሳል::
በመንገዱ ጉቶው፣ ድንጋዩ፣ ግንዱ ይመተዋል:: ሲያደናቅፈው ይወድቃል:: ሲነሳ ተስፋ አይቆርጥም:: የተመታ እግሩን፣ የደማ ጉልበቱን እያሻሸ ጉዞውን ይቀጥላል:: ደግሞ በሌላ ቀን ከሌላ መንገድ ይገኛል:: አካባቢው ለማንም እግረኛ አያመችም::
ወጋየሁ ብዥ እያለበት በግምት መራመድ ልምዱ ነው:: መንገዱ አያዝንለትም:: ሳሩ፣ ሰርዶው ይጠልፈዋል:: ድንጋይ፣ ጠጠሩ ይመታዋል:: የተላጠውን የእግሩን አንጓ አስታሞ፣ ራሱን በራሱ አባብሎ ከወደቀበት ይነሳል:: እንደገና መንገዱን መጥኖ፣ ግራ ቀኙን ገምቶ ጉዞ ይጀምራል:: ከፊቱ ስለተጎለተው ትልቅ ድንጋይ፣ ስለተቆፈረው ጥልቅ ጉድጓድ አያውቅም::
ጓደኞቹ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ እሱ ተቀምጦ ይቆያቸዋል:: ሳቅ ጨዋታው ይደራል:: ስለውሏቸው ያወጉታል:: ስላሰበው ይነግራቸዋል:: በወጋየሁ ውስጠት ያለው የኪነጥበብ ፍቅር ለሙዚቃው ያደላል:: የግጥም ተሰጥዖው ፈክቶ ይወጣል:: ችሎታውን የሚያደንቁለት በቅርበት ያሞግሱታል:: ይህን የሚረዳው ታዳጊ ብርሃን አልባ መሆኑን አሳስቦት አያውቅም:: ከእነሱ አንዳች ሳያጎድል መሳተፉ ያበረታዋል::
ወጋየሁ ነገሮችን ለመድፈር ወደ ኋላ አይልም:: ጓደኞቹ የሚያደርጉትን ሁሉ ይሞክራል:: ቢገፉት፣ ቢገፈትሩት አይወድቅም:: አብሯቸው እግር ኳስ ይጫወታል፣ ቴሌቪዢኑ ባይታየውም ይዝናናበታል:: እንደውም አንዳንዴ ባልንጀሮቹ የዓይኑን ጉዳይ እስኪረሱት ይዘናጋሉ:: ከእነሱ ያለው ቅርበት ያለልዩነት በመሆኑ ለእገዛ እጃቸውን ዘርግተውለት አያውቁም::
የሚሊኒየሙ ስጦታ…
በሚሊኒየሙ መጨረሻ አካባቢ ወጋየሁ ከሆስፒታሉ ድንገቴ ጥሪ ደረሰው:: የመጠራቱ ምክንያት በለጋሾች በተገኘው ብሌን በአንድ ዓይኑ ላይ ንቅላ ተከላውን ለማካሄድ ነበር:: በወጋየሁ ውስጠት ያደረው ስሜት የተለየ ሆነ:: ይህ እውነት ለእሱ ከስጦታ በላይ ነው::
ያለፉት ጊዜያት ብዙ ለሚሻው ታዳጊ መልከ ብዙ ሆነው አልፈዋል:: እስከዛሬ በጨለማ ሲኖር፣ ሲራመድ ነበር:: እስከአሁን ሳይወድ በግድ ከትምህርቱ ታቅቧል፣ ፍጹም ሳይገባውም በብቸኝነት ቆዝሟል፣ በትካዜ አንገት ደፍቷል::
ዛሬ ደግሞ ዓለምን ተሰናብተው ካለፉ ልበ ቀናዎች ‹‹እነሆ!›› የተባለውን በረከት ሊቀበል ነው:: ደስታ፣ ጉጉትና ብሩህ ተስፋ በፊቱ ተመላለሱ:: በቀላሉ ሊገልጸው ከማይችለው ስሜት ጋር እጅ ለእጅ ተጨባበጠ:: ወጋየሁ በሆስፒታሉ ተገኝቶ ከሐኪሙ ፊት ቀረበ:: ሙሉ ምርመራ ተደርጎለት የብርሃን መንገዱን ለመጀመር ተዘጋጀ::
የወጋየሁ ሁለቱም ዓይኖች ከእይታና ብርሃን የታቀቡ ናቸው:: ለሕክምናው የቀደመውን ዕድል ያገኘው ግን አንደኛው ዓይኑ ብቻ ነበር:: በሕክምናው ተሞክሮ በአንድ ጊዜ ሁለቱንም መሥራት አይቻልም:: የሚሆነው ሊሆን ጊዜው ደርሷል:: ብርሃን ናፋቂው ልጅ ግራ ዓይኑን ለንቅለ ተከላው ሰጥቶ ውጤቱን በጉጉት ጠበቀ::
ተናፋቂው ቀን…
በዕለተ ቀጠሮው የሕክምናው ሂደት በልዩ ስኬት ተጠናቀቀ:: ወጋየሁ በሆስፒታሉ ለስምንት ቀናት ተኝቶ ነበር:: እሽጉ ተፈቶ ቅኝት እንደጀመረ ዓይኑ ማየት የሚሻውን ሁሉ አነጣጠረ:: አባቱን፣ እህት ወንድሞቹን፣ ጓደኞቹን ለማስተዋል፣ በአካል ለመተዋወቅ ናፈቀ:: ወዲያው የልቡ ሀሳብ ሙሉ ሲሆን ተሰማው::
የብርሃንና የጨለማን ልዩነት ለመረዳት አፍታ አልቆየም:: ቀድሞ ፈዛዛ የሚመስለው ቁስ ፍክት፣ ድምቅ ብሎ ታየው:: የተፈጥሮን ውበት ለማድነቅ አልዘገየም:: በሚያየው እውነት አብዝቶ ተገረመ:: የሰዎች ቁንጅና፣ የከተማው ውበት፣ የፎቆቹ ብዛት አስደመመው:: ሁሉም አስቀድሞ ከነበረው ግምት የተለዩ ሆኑበት::
በመንገዱ ዞር ብሎ አንድ ነገር ላይ አተኮረ:: በትልቁ የተለጠፈ ማስታወቂያ ነበር:: እየገረመው ከጽሑፉ ነጥሎ ምሥሉ ላይ አፈጠጠ:: ስላልተማረ ፊደላቱን ማንበብ አልቻለም:: እንዲያም ቢሆን ደስ አለው::
አዲስ ትውውቅ ከቤተሰብ ጋር
ከጊዜያት በኋላ ወደ ሐረር ተመለሰ:: የናፈቃቸውን ሁሉ እንደ አዲስ አወቃቸው:: ከመዳሰስ፣ በድምፅ ከመለየት አልፎ በትኩረት ያስተዋላቸው ያዘ:: አባቱን፣ አክስት አጎቶቹን አተኩሮ አያቸው:: እህቶቹን በአካል ባገኘ ጊዜ መልክ ቁመናቸው ተለየበት:: እስከዛሬ በአዕምሮው እንደሳላቸው አይደሉም:: ሁሉም ቀያዮች፣ ውቦች ሆኑበት:: መለስ ብሎ የራሱን ፊት አስተዋለ:: ከእነሱ ጋር አይመስልም:: መልኩ ጠቆር ይላል::
ወጋየሁ ዓይን ይሉት በረከት የሕይወት ዋልታ፣ የመኖር መሠረት መሆኑን ተረዳ:: የእግሮቹ ላይ ጠባሳ፣ ያሳለፋቸው ክፉ ደግ ጊዜያት የማንነቱ ማስታወሻዎች ናቸው:: ዛሬ የ‹‹አሁን አየ ዓይኔ›› ዜማ ለእሱ ትርጉሙ ይለያል::
ያሰብኩት ተሳካ…ያለምኩት ደረሰ
ወጋየሁ አሁን የልቡ ደርሷል:: ያሰበው ተሳክቷል:: ለዓመታት የተነፈገውን ትምህርት ‹‹ሀ..›› ብሎ ሊጀምር ደብተር እስክሪብቶ አዘጋጅቷል:: የዓመታት ጥያቄው መልሰ ሊያገኝ ነው:: እኩያ ጓደኞቹ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል:: እነሱ የደረሱበት፣ እሱ ወደ ኋላ የቀረበት ጊዜ አላስቆጨውም:: በሆነለት ሁሉ ፈጣሪውን አመስግኖ ለትምህርት ራሱን አዘጋጀ::
አሁን ተማሪው ወጋየሁ ቀለም ሲቆጥር፣ ፊደል ሲለይ ይውላል:: ጎን ለጎን የሕክምና ክትትሉን አልተወም:: ከሌሎች እኩል በትኩረት ይማራል:: በበሰለ አዕምሮ፣ በመልካም ዕድሜ ላይ የያዘው ትምህርት እያዋጣው ነው::
ከስድስት ዓመታት በኋላ…
ወጋየሁ ካሳለፈው የጨለማ ጉዞ ተላቆ በአንድ ዓይኑ የብርሃን ሕይወትን ከጀመረ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል:: በእነዚህ ጊዜያት የትምህርትን ጣዕም ለይቷል:: የብርሃንና ጨለማን ልዩነትን አውቋል:: ከምንም በላይ ሊያያቸው የናፈቃቸውን ቤተሰቦቹን በአካል አግኝቶ ፍቅሩን ተወጥቷል:: ያለፉት ዓመታት ለእሱ የአዲስ ምዕራፍ አዲስ ዓለም ነበሩ::
2006 ዓ.ም:: ይህ ዓመትና ወጋየሁ የተገናኙት ሕይወት የሰጠችውን ሁለተኛ ዕድል በሚጠቀምበት አጋጣሚ ነበር:: አሁን የቀኝ ዓይኑ ብርሃን የሚመለስበት ጊዜው ደርሷል:: ንቀላ ተከላው እንደተጠናቀቀ ወጋየሁ በሁለቱም ዓይኖቹ ሙሉ እይታውን ቀጠለ:: ትምህርቱን በወጉ የያዘው ወጣት ከሥነጽሑፍ ዝንባሌው ሲገናኝ አልዘገየም:: እያሰባቸው ያጣቸው፣ እንደ ጓደኞቹ ያልከወናቸው ስኬቶች መምጣት ጀም ረዋል::
ወጋየሁ እስከዛሬ ያለፉትን ፍላጎቶች እግር በእግር አሳዶ ያዛቸው:: የውስጡ ስሜት ራሱን ፈልጎ ለማግኘት አገዘው:: በሚኒሚዲያውና መድረክ በመምራት ታዋቂ ሆነ:: አሁን ታስሮ የቆየው ፍላጎቱ ከብርሃን መንገዱ ተገናኝቷል:: ፈተና ሆኖ የቆየበት ታሪክ በእሱ ጥረትና ትግል እየታለፈ ነው:: ሁለቱም ዓይኖቹ በመነጽር እየታገዙ አጥርተው ያያሉ::
ብርሃናማው ዛሬ …
ወጋየሁ ዛሬ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ነው:: ልጅነቱን ሙሉ ሲመኘው ከነበረው ፍላጎቱ ተገናኝቷል:: በማርኬቲንግና ማኔጅመንት ዘርፍ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነው:: እንደእሱ የዓይን ብሌን ተለግሰው ብርሃን ካገኙ ወገኖች ጋር ማኅበር በማቋቋም የድርሻውን ይወጣል:: የዛሬ ሕይወቱ ከቀድሞ ማንነቱ የተሻለ መሆኑ ሀሳቡን በተግባር እንዲከውን ምክንያት ሆኗል:: በዚህ እውነታ የወጋየሁ ደስታ ልዩ ነው:: እሱ የወደፊት የሕይወት አቅጣጫው በዚህ የምዕራፍ መንገድ ተጋምዶ እንደሚቀጥል ያምናል::
መልዕክት-ለሌሎች
የወጣቱ ጥንካሬ በእጅጉ አስደንቆኛል:: በማንነቱ ውስጥ የሰው ልጅን ፍላጎትና ስኬት አስተውዬ እያየሁበት ነው:: ከወጋየሁ ፈጠነ ጋር ከመሰነባበቴ በፊት ለአንባቢያን የማደርስለት መልዕክት እንዳለው ጠየኩት:: ለምላሹም አልዘገየም::
እሱና መሰል ወገኖች ዛሬ ለደረሱበት የብርሃን ዓለም መሠረቱ የዓይን ብሌን ልገሳ ነው:: ይህ ልገሳ የሚገኘው ደግሞ ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች እንደሆነ ይታወቃል:: በርካቶች ይህን ታላቅ ስጦታ ለማበርከት ፍላጎት ቢኖራቸውም ደፍረው አይወስኑም::
ማንም እንደሚያውቀው ስጦታው በሕይወት ካለፉ በኋላ የሚበረከት ነው:: ይህ እውነት በሕይወት ላሉት ብርሃን አልባዎች ሕይወትን እንደመስጠት ይቆጠራል:: እናም ሁሉም ብርሃን ለመለገስ ልቡ ይፍቀድ ብሏል:: ወጋየሁ በመልዕክቱ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም