በስፖርት ማህበራት ምርጫ ላይ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል!

የኢትዮጵያን ስፖርት ወደ ኋላ እየጎተቱ ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖች አስተዳደራዊ ጉዳይ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። አስተዳደራዊ ጉዳይ ሲባል ደግሞ በቀጥታ የሚገናኘው ስፖርቱን በፍቃደኝነት ለመምራትና ለማገልገል ካለ ምንም ክፍያ ወደ ኃላፊነት ከሚመጡ ሰዎች ጋር ነው:: እነዚህ ሰዎች ስፖርቱን በመሪነት ለማገልገል ወደ ኃላፊነት የሚመጡት የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖች በሚያደርጉት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በሚደረጉ የፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ መሆኑ ይታወቃል::

በዚህ መንገድ ተመርጠው ወደ ኃላፊነት የሚመጡ ሰዎች ስፖርቱን ለማገልገል እውቀት፣ ልምድና ገንዘባቸውን ለማውጣት ፍቃደኛ የሆኑ ናቸው የሚል በመርህ ደረጃ የተቀመጠ ነገር አለ:: ነገር ግን እነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ በትክክል በዚህ መርህ መሰረት ስፖርቱን ለማገልገል ነው ወደ ኃላፊነት የሚመጡት? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነው::

በሀገር አቀፍ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖች የተለያዩ ስፖርቶችን ለማገልገል ተመርጠው ወደ ኃላፊነት ከሚመጡ ግለሰቦች መካከል በትክክልም እውቀት፣ ልምድና ገንዘባቸውን ለማውጣትና ዘርፉን ለማሳደግ የሚጥሩ የሉም ማለት አይቻልም:: በተቃራኒው እውቀቱም፣ ልምዱም የሌላቸውና እንኳን የገዛ ገንዘባቸውን ሊያወጡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው ኪሳቸውን ለመሙላት ሲጥሩ የሚታዩትን ቤቱ ይቁጠራቸው:: በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን መፍረድ አይቻልም:: ከእነሱ ይልቅ ተጠያቂ መሆን ያለበት መርጦ ለኃላፊነት ያበቃቸው ጠቅላላ ጉባዔ ነው:: እንዲመረጡ እጩ አድርጎ የሚያቀርባቸው አካልም ከዚህ ተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም::

ከሀገር አቀፍ እስከ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ የተለያዩ ስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖች በኃላፊነት እያገለገሉ የሚገኙና ወደ ኃላፊነት ለመምጣት መንገድ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ግለሰቦች ከስፖርቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው፣ እውቀቱም ልምዱም ያልደረሰባቸው እንደሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው:: የኢትዮጵያን ስፖርት መቀየርና ማሳደግ ከተፈለገ ይህን መሸፋፈን አያስፈልግም::

ሰሞኑን የአዲስ አበባን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለመምራት የተመረጡ ግለሰቦችን ማየት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው:: የከተማዋ ፌዴሬሽንን ለመምራት ሁለት ሴት አርቲስቶች በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በአቃቤ ንዋይነት መመረጣቸው ዛሬም ድረስ አነጋጋሪና በብዙዎች እየተተቸ የሚገኝ ጉዳይ ነው:: ሁለቱ አርቲስቶች ከዚህ ቀደም ከእግር ኳስ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም:: ስፖርቱን ለመምራት እውቀቱም ይሁን ልምዱ እንደሌላቸው ለማንም ግልፅ ነው:: ታዲያ ስፖርቱን በምን መልኩ እንዲያገለግሉ ተመረጡ? የብዙዎች ጥያቄ ነው:: የስፖርት ቤተሰቡ ይህን ጥያቄ በማንሳቱ አንዳንዶች ጉዳዩን ‹‹ሴት ስለሆኑ ነው›› በሚል ለመጠምዘዝ ይሞክራሉ:: ጥያቄው ሴትነታቸው ወይም ፆታ ላይ አይደለም:: ስፖርቱን ለመምራት እንዴት መጡ የሚለው ነው:: እንዲመረጡ የወከላቸውና የመረጣቸው ጉባዔ ምን አይቶ፣ ምን መዝኖ ነው? እውነት የአዲስ አበባን እግር ኳስ ለመምራት ከአርቲስቶቹ ይልቅ ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ እውቀቱም፣ ልምዱም ያላቸው ሰዎች ጠፍተው ነው?

ይህ ብቻ አይደለም ጥያቄው፣ ከተመረጡት አርቲስቶች አንዷ ስለ ምርጫው እንደማታውቅ በማህበራዊ ትስስር ገጿ ላይ አሳውቃለች። አርቲስቷ በፌስቡክ የማህበራዊ ትስስር ገጿ ባሰፈረችው መልዕክት “መመረጤን ያወቅኩት እኔም በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ ነው›› በማለት ምርጫው ሲደረግ በቦታውም እንዳልነበረችና ጥሪም እንዳልደረሳት በመግለፅ፤ በስፖርቱ ላይ ምን እየተሰራ እንደሚገኝ እንድንጠይቅ አድርጋናለች:: በዚህ ልትደነቅ ይገባታል:: በማያውቁትና በማይወጡት ጉዳይ ላይ ኃላፊነት ስለተሰጠ ብቻ መቀበል እንደማይገባ ትምህርት ነው:: የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአንድ ከተማ ጉዳይ አይደለም፣ እንደ ሀገር ያለው ተፅዕኖ ከፍ ያለ ነው:: አዲስ አበባ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መቻል፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎችም በሚሊዮን የሚቆጠር ደጋፊ ያላቸው የሀገሪቱ ትልልቅ ክለቦች መዲና መሆኗ መረሳት የለበትም:: እነዚህ ክለቦች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ትልቅ አሻራ የሚያሳርፉ በብሔራዊ ቡድንም ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል:: የአዲስ አበባን እግር ኳስ መምራት ማለት ቀላል ነገር አይደለ ም::

ይህ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፌዝ ብቻ አይደለም:: እንደ ሀገር በስፖርቱ ላይ እየታየ የሚገኘው ኪሳራ ነፀብራቅ ነው:: ከዚህ ቀደም ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ይሁንታው ሳይጠየቅ በሌለበትና በማያውቀው ሁኔታ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ተደርጎ መመረጡን ከራሱ አንደበት ሰምተን ጉድ ብለናል:: በብሔራዊም ይሁን በክልልና ከተማ አስተዳደር ደረጃ ያሉ የተለያዩ የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖችን የሚመሩ ሰዎች የመጡበትና እየመጡ የሚገኙበት መንገድ ከዚህ የተለየ አይደለም::

በዚህ መንገድ የሚመጡ ሰዎች ናቸው ስፖርቱን ወደ ቁልቁለት ከመስደዳቸው ባሻገር ስፖርቱ ዘወትር ከውዝግብ እንዳይፀዳ እያደረጉ የሚገኙት:: በአንድ ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፓርላማ ንግግራቸው ላይ “ኢትዮጵያ ውስጥ ስፖርት የለም፣ በሌለ ስፖርት ውስጥ ግን ሽኩቻው አለ:: በሌሎች ሀገራት ስፖርቱ አለ ውዝግቡ ግን የለም” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። የዚህ ውዝግብ ምንጭ ስፖርቱን ለመምራት እውቀቱም፣ ልምዱም የሌላቸው ገንዘባቸውን አውጥተው ለማገልገል ሳይሆን ለመገልገል የሚመጡ ሰዎች መሆናቸው የሚታበይ አይደለም::

ስፖርቱን በመሪነት ለማገልገል ተወክለው ወደ ምርጫ የሚመጡ ሰዎች የግዴታ ስፖርተኛ ወይም ከዚህ ቀደም በስፖርት ያለፉ ይሁኑ ማለት አይደለም። ቢያንስ ስፖርቱ ምን ይፈልጋል፤ አሁን የተሳሳተው ነገር ወይም የስፖርቱ ችግር ምንድነው? የሚለውን ጉዳይ አውቀውና ተረድተው የማስተካከል አቅም እንዲሁም የመምራት ችሎታ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚልኳቸው ተወካዮች እንዲህ አይነት ሰዎች መሆናቸውን የማረጋገጥ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል።

ስፖርቱን ለመምራት ተወክለው የሚመጡ ሰዎች ጋር ብቻ ግን አይደለም ችግር ያለው። በምርጫ ወቅት ድምፅ እንዲሰጡ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና የተለያዩ ስፖርት ተቋማት የሚወከሉ ግለሰቦች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ድምፅ የሚሰጡት ሰው ስፖርቱን ለማገልገል ተገቢ መሆኑን የማረጋገጥ አደራ እንዳለባቸው ማስታወስ ተገቢ ነው። ምርጫዎች ላይ ድምፆች እንደሚገዙና እንደሚሸጡ ለስፖርት ቤተሰቡ የተሸሸገ ጉዳይ አለመሆኑን ማደባበስ አያስፈልግም። ስለዚህ ስፖርቱን ለማገልገል እጩ አድርጎ ሰዎችን ከሚያቀርበው አካል ጀምሮ፣ ድምፅ ለመስጠት ተወክለው በምርጫ ጉባዔ ላይ የሚመጡ ሰዎች እንዲሁም ለስፖርቱ የማይበጁ ሰዎች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ይሁንታ የሚሰጠው አጠቃላይ ጉባዔ የሕዝብ አደራውን ሳይወጣ ሲቀር የሚጠየቅበት መንገድ ሊኖር ይገባል::

ልዑል ከካምቦሎጆ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You