ፊልሞቻችንና ድራማዎቻችን ዛሬም በ20ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ላይ ያሉ ይመስለኛል:: በእርግጥ ብዙ ፊልሞች ዘመንን ቀድመው በመሄድ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚሰሩም አሉ:: በተለይም የቴሌቭዥን ድራማዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀሳባዊና ቀልብን ያዝ የሚያደርግ ይዘት ያላቸው እየሆኑ እንደመጡ ከዚህ በፊት አድንቀናል:: የተቀሩትም ቢሆን የ20ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብን እያንፀባረቁ ያሉት ለማስተማር ብለው መሆኑ ግልጽ ነው፤ ዳሩ ግን የሚያስተምሩበት መንገድ በዚህ ዘመን በሌለ እምነትና በዚህ ዘመን በሌለ አስተሳሰብ ላይ ነው::ነገሩን በምሳሌ ግልጽ ላድርገው መሰለኝ!
ቀደም ባሉት ዘመናት ሥራ ይናቅ ነበር፤ የመደብ (የደረጃ) መለያ ይደረግ ነበር ማለት ነው:: እንደ ብረታ ብረት ማቅለጥ፣ እንጨት መፋቅ፣ ወንበርና ጠረጴዛ የመሳሰሉትን መገጣጠም፣ ልብስ ስፌትና የመሳሰሉት የዕደ ጥበብ ሥራዎች ብዙም ክብር የሌላቸው ሥራዎች ተደርገው የሚታዩ ነበሩ:: ጋብቻ ሁሉ ያስቀራሉ ተብሎ ይታመን ነበር:: በእነዚህ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሰዎች ለሚስትነት የሚጠይቋት ሴት ትንቃቸዋለች ተብሎም ይፈራ ነበር::
በዚህ አመለካከት በመሄድ እና የዚህ ልማድ ተፅዕኖ ይመስላል ፊልሞቻችን ላይ አንድ የምናየው ነገር አለ:: የሆነ ወንድ የወደዳትን ሴት ሲተዋወቃት ሥራውን በግልጽ አይነግራትም፤ ‹‹እሺ!›› አትለኝም በሚል ፍርሃት መሆኑ ነው:: ወይም ክብር አለው የሚባል የሥራ ዘርፍ ይነግራትና ይዋሻታል:: በመጨረሻ ግን በሆነ አጋጣሚ የሚሰራውን ሥራ ታየዋለች:: ይህኔ ይጣላሉ:: የሚጣሉት፤ በአንዳንድ ፊልሞች ሥራውን በመናቅ ሳይሆን ለምን ዋሸኸኝ በሚል ነው፤ በአንዳንዶቹ ፊልሞች ደግሞ ሥራውን በመናቅ ነው፤ የገሃዱን ዓለም ነፀብራቅ ለማሳየት መሆኑ ነው::
የዚህ ተቃራኒ ደግሞ አለ:: የሆነ ባለሀብት ይወዳትና እምቢ ትላለች:: ቀደም ሲል በነበረው ዘመን አመለካከት ዝቅተኛ ሊባሉ የሚችሉ የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማራ ወንድ ታፈቅራለች:: የሚሰራበት ሥራ ቦታ እየሄደች ታየዋለች:: የሚኖርባት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ትሄዳለች:: ይሄኛው ይዘት ብዙ ጊዜ ‹‹ድሃ ወንድ የሚወደደው በፊልም ብቻ ነው›› እየተባለ የሚቀለድበት ነው:: ለማስተማር ተብሎ መሆኑ ያስታውቃል::ፊልሙን የምትተውነው ተዋናይት በገሃዱ ዓለም ሕይወቷ ግን ድሃ ባል አግብታ አላየንም:: ቢያንስ በልቦለድ እንኳን እንዲህ ብናደርግ ብሎ የመመኘት ይመስላል::
ከላይ የተገለጹት ሁለቱም አይነት መንገዶች ዘመን ያለፈባቸው ይመስለኛል:: በዚህ ዘመን ሊታይ የሚችለው ምናልባትም የሚያገኘው የገቢ መጠን እንጂ የሥራው አይነት አይደለም:: ምናልባት በህግ የተከለከለ እና ከኢትዮጵያዊነት ባህል አንፃር ‹‹ነውር›› የሚባል ካልሆነ በስተቀር፤ ሥራ የሚናቅበት ዘመን በተጨባጭ ያለፈበት ይመስለኛል:: ዘመድ አዝማዶቼ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ስለሆኑና አሁናዊ ሁኔታውን ስለማውቀው ይህን ለመመስከር እችላለሁ:: ማንኛውም የገጠር ሰው ዛሬ ላይ ብረታ ብረት የሚያቀልጥ፣ እንጨት የሚገጣጥም፣ ልብስ የሚሰፋ ሰው እና ሸማኔ አይንቅም:: በከተሞች ደግሞ የትኛውም ሥራ የማይናቅ መሆኑ ለዘመናት የቆየ ልማድ መሆኑ ይታወቃል::
ዛሬ ላይ አንዲት ሴትና አንድ ወንድ በሆነ አጋጣሚ ቢተዋወቁና ሥራ ቢጠያየቁ፤ ምናልባት የገቢው መጠን እንጂ የሥራው አይነት የሚያናንቅ አይሆንም:: የወር ደሞዝተኛም ይሁን የቀን ሠራተኛ፣ ነጋዴም ይሁን ባለሥልጣን፣ ጠጋኝም ሆነ አቅላጭ…. ዋናው የሚያገኘው ገቢ ነው::
በሌላ በኩል አሁን ያለው ዘመን ነፃ አስተሳሰብና አመለካከት ያለበት ዘመን ነው:: ሴቶች ራሳቸውን ችለው የሚያስቡበትና የራሳቸውን ነፃ ውሳኔ የሚወስኑበት ነው:: ምን ይሉኛል ተብሎ እንደ ድሮው ዙሪያ ገባው ብቻ የሚታይበት ሳይሆን፤ የራስ ፍላጎትንና ነፃ ምርጫን የሚከተሉበት ነው:: የማይካደው ሀቅ ግን የገቢ መጠን አሁንም ቢሆን ተፅዕኖ ማድረጉ አይቀርም:: ከዚያ ውጭ ግን የሥራው አይነት በዚህ ዘመን ጉዳይ የሚሆን አይመስለኝም::
ብዙ ጊዜ የምታዘበው ግን ቀደም ሲል የተሰሩ ፊልሞችን ሳይቀር አንድ ትዕይንት (ሲን) በመቁረጥ መልዕክት ለማስተላለፍ ማህበራዊ ገጾች ላይ አያለሁ::ሥራ አይናቅም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑ ነው:: በዚህ ዘመን ሥራ የማይናቅ መሆኑን የማያውቅ አለ ወይ ነው ጥያቄው!
አንዳንድ እምነቶችና አመለካከቶች ነባራዊና ዓውዳዊ ሁኔታው ተቀይሮም ባሉበት ይቀጥላሉ:: ብዙ ጊዜ የሚገርመኝን ነገር ልንገራችሁ:: ቀደም ባለው ዘመን ሾፌርነት የጥቂት ሙያተኞች ሥራ ነበር:: መኪና የሚያሽከረክር ሁሉ ‹‹ሾፌር›› ተብሎ ይጠራል:: ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንደ ልማድ የተያዙ የሾፌር ባህሪያት አሉ:: ለምሳሌ፤ ችኩልነት፣ ተሳዳቢነት፣ አግባብ ያልሆኑ ቃላትን መናገር የመሳሰሉት የሾፌር ባህሪ ተደርገው ይታያሉ:: በዚህም ምክንያት የሚያሽከረክር ሰው ሁሉ የሚያደርገውን ነውር ነገር ‹‹ድሮስ ከሾፌር›› የሚባል ልማድ አለ፡፡
አሁን ግን እንደዚያ ለማለት አያስችልም:: ‹‹ሾፌር›› የሚባሉት እስከ ዛሬ ድረስ የስንቱን ነውረኛ ነውር ተሸክመው ኖረዋል ለካ! አሁን ብዙ አሽከርካሪዎች በነውር ቃላት ሲሳደቡ እየሰማን ነው:: እነዚህ ሰዎች በሙያቸው ‹‹ሾፌር›› አይደሉም:: በየትኛውም ሙያ ውስጥ የተሰማራ ሰው መኪና መያዝ ይችላል፤ ብዙ ሰዎችም ባለመኪና ሆነዋል:: በየመንገዱ አንገቱን አሾልኮ ሲሰዳደብ የምታዩት ሁሉ በሾፌርነት ሙያ የተቀጠረ ነው ማለት አይደለም:: ወይስ የራሱን መኪና የሚያሽከረክር ሰው ‹‹ሾፌር›› መባል አይችልም?
አንድ በሌላ ሙያ ላይ የተሰማራ ሰው እያሽከረከረ ወደ ሥራው እየሄደ ነው እንበል:: ይህ ሰው አንገቱን አሾልኮ ዜብራ የሚሻገሩ ሰዎችን ተሳደበ እንበል:: ስለዚህ በተለመደው ልማድ እግረኞቹ ‹‹ድሮስ ከሾፌር…›› ሊሉ ይችላሉ ማለት ነው:: ሰውየው ግን በሙያው ሾፌር ሳይሆን፤ የተቋም ኃላፊ ሊሆን ይችላል፣ ሐኪም ሊሆን ይችላል፣ ጠበቃ ሊሆን ይችላል፣ መሃንዲስ ሊሆን ይችላል፣ ነጋዴ ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ ችግሩ የጥቂት ሰዎች ሳይሆን እንደ ሕዝብ ያለብን ችግር ነው ማለት ነው::
ይህ ልማድ የመጣው ቀደም ባለው ዘመን ሾፌር የጥቂት ሰዎች ሙያ ስለነበር ነው:: እንደ ሀገር አቋራጭና ሌሎች ከባድ ተሽከርካሪዎችን ለሚያሽከረክሩ ባለሙያዎች የተሰጠ ዘርፍ ስለመሰለ ነው:: በዚህ ዘመን ግን መኪና ያለው እና ራሱ የሚያሽከረክር ሰው ሁሉ ሾፌር ነው ማለት ነው:: ወይስ ተቀጥረው ሲሰሩትና የራስን መኪና ሲሾፍሩ ይለያይ ይሆን?
ወደ ፊልሞችና ድራማዎች ስንመለስ፤ በዚህ ዘመን ሥራ የሚናቅበት አመለካከት ያለ አይመስለኝም:: ምናልባት በጣም በጥቂቱ በግለሰቦች ደረጃ ሊኖር ቢችል እንኳን እንደ ባህል ግን አለ ለማለት አያስደፍርም::
አሁን ላይ ያለው ትውልድ ‹‹እነዚህ ሥራዎች ለካ ነውር ነበሩ እንዴ!›› የሚል ስሜት ሊፈጠርበት አይገባም:: ምክንያቱም በተግባር ነውር ሲደረጉ አላየምና! ስለዚህ ለማስተማር ተብሎ የሚደረጉ የፊልምና ድራማዎች ይዘት የዘመኑን ዓውድ ያገናዘበ ይሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም