አብዝቶ ማሰብና መጨነቅ የብዙ ሰው ችግር ነው:: እድሜህ 13 ዓመት ሆኖህ የሕይወት ጥያቄ መጠየቅ ከጀመርክ ጀምሮ እስክትሞት ድረስ እንደጥላ የሚከተልህ ፀባይ ነው:: ማሰብ! ፤መጨነቅ! በጣም አብዝተን የምንጠቀምባቸው ፀባያት ናቸው:: መጠኑ ይለያይ እንጂ አብዝቶ የማያስብና የማይጨነቅ ሰው የለም:: ማሰብ መልካም ነገር ነው:: ሕይወት የሚቀይር ነገር ነው:: ሲበዛ ነው መጥፎነቱ:: አብዝተህ ስትጨነቅ እንቅልፍ ታጣላህ:: አንዳንዴ የምትችለውን ሁሉ አትሠራም:: ወይ ደግሞ ብዙ ከማሰብህ የተነሳ አቅም ታጣለህ:: ስታስብ ጊዜው ይሄድብሃል::
አንዳንዴ አስበህ! አስበህ! አይደክምህም? ያውም ተመሳሳይ ሃሳቦች:: እዚህ ግባ የማትላቸው ተደጋጋሚ ሃሳቦች:: በተደጋጋሚ መልሰህ መላልሰህ ታስባለህ:: ወይ የትናንት ትዝታ ነው፣ ወይ ቁጭት ነው፣ ወይ የሚያስጨንቅህ ጉዳይ ነው፣ ወይ ደግሞ አታውቀውም:: አንዳንዴ ምን እንደምታስብ ራሱ አታውቀውም:: ግን ጊዜህን እየተሻማ ነው:: ጉልበትህን እየመጠጠው ነው:: ከሰው በታች እያደረገህ ነው:: ጭንቀታም እያደረገህ ነው:: ምን ይሻላል ታዲያ?
በዚህ ዓለም በጣም ከፍ ያለ የስኬት ደረጃ ላይ የደረሱ የሃይማኖት ወይ የቢዝነስ አልያም የምናከብራቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያስቡት በፕሮግራም ነው:: ምን ማለት መሰላችሁ? ሥራ እየሠሩ ከሆኑ ሥራቸው ላይ ነው መቶ ከመቶ ትኩረታቸው:: ከቤተሰባቸው ወይም ከፍቅረኛቸው ጋር ከሆኑ መቶ ከመቶ እዛ ቦታ ላይ ናቸው:: ቅፅበቱ ላይ ነው የሚያተኩሩት:: ማሰብ ሲፈልጉ ደግሞ ቁጭ ብለው ያስባሉ:: እኛ የከበደን እሱ ነው:: በምንፈልገው ሰዓት አይደለም የምናስበው:: ሥራ እየሠራን ሃሳቦች አለ:: የምንፈልገውን እያደረግን ሃሳቦች ይመጣሉ:: ልንተኛ ስንልም እንዲሁ::
ታዲያ ምን ይሻላል? አስበህ ሃሳብን መቆጣጠር ብትችል ተአምር እኮ ነው የምትሠራው:: ብዙ ነገር ነው ሕይወትህ ላይ የምትቀይረው:: ምን ይሻልሃል ታዲያ? እነሆ ቀላልና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት ሳይንሳዊ መፍትሄዎችን ጀባ ልበልህ::
1ኛ.ራስን ማድመጥ
አንዳንዴ ምን እንደምታስብ እንኳን አታውቀውም:: እንደውም አንዳንድ ሰው ሃሳብ ውስጥ በጣም ይሰምጥና የሚነቃው ወይ ስልኩ ሲጠራ ነው፣ ወይ ደግሞ ‹‹አንተ! የት ሄድክ በሃሳብ›› ሲባል ነው:: ከዛ ምን እያሰብክ ነው? ሲባል ምን እንደሆነ አያውቀውም:: ስለዚህ አሁን ራስህን ለማድመጥ ሞክር:: ምንድን ነው የምታስበው? ልክ ስታስብ ንቃ:: የሆነ ሃሳብና ጭንቀት ውስጥ ስትገባ አሁን እያሰብኩ ነው በል:: የሆነ ሰው መጥቶ እስኪቀሰቅስህ አትጠብቅ:: ከዛ ትነቃና ምንድን ነው እያሳሰበኝ ያለው? የምትለውን ለይተህ አውጣው::
በእርግጠኝነት በጣም አብዝተህ የምታስባቸው ነገሮች ከሁለትና ሶስት አጀንዳዎች አይበልጡም:: ወይ ኑሮ ነው፣ ወይ ትዳር ነው፣ ወይ ሥራ ነው፣ ወይ ትምህርት ነው፣ ወይ ቢዝነስ ነው፣ ወይ ገንዘብ ነው አልያ ደግሞ የፍቅር ግንኙነት ነው:: ከእነዚህ አያልፍም:: ስለዚህ ምን እንደምታስብ ነቃ ብለህ ራስህን ለማድመጥ ሞክር:: እንደዚህ የማድረግህ ዓላማው ጫፉን ለመያዝ ነው:: ስለምን እያሰብክ እንደሆነ ለማወቅ ነው:: አየህ! ያስጨነቀህን ጉዳይ ለይቶ ለማወቅ ነው:: ስለዚህ ከጭንቀትና አብዝቶ ከማሰብ መውጣት ከፈለክ ራስህን አድምጠውና ልክ ሃሳብ ውስጥ ስትገባ ነቃ ለማለት ሞክር:: ‹‹ይህን እያሰብኩ›› ነበር በል::
2ኛ.አምስት መፍትሄዎችን ፃፍ
ምን እንደሚያሳስብህ ማወቅ ከጀመርክ አሁን ወረቀት ላይ ማሰብ መጀመር አለብህ:: ወረቀት ላይ የሚያስቡ ሰዎች ሃሳባቸውን መቆጣጠር ይችላሉ:: ስለዚህ ይህ ችግር በጣም እያሳሰበኝ ነው ብለህ ትፅፍና ወደ አዕምሮህ የሚመጡትን መፍትሄዎች መዘርዘር ጀምር:: አምስት መፍትሄዎችን ፃፍ:: ለምን መሰለህ አዕምሮህ ትኩረቱን ከችግሩ ላይ አንስቶ ወደ መፍትሄው ማምጣት አለበት:: ስለመፍትሄው ማሰብ አለብህ:: ስለጨለማው አብዝቶ ማሰብ ብርሃን አይሰጥህም:: ችግሩ ላይ ጊዜ አታጥፋ::
አየህ! በዚህ ምድር ሁለት አይነት ሰዎች አሉ:: የመጀመሪያዎቹ ስለችግሩ ሲነገራቸው ለምሳሌ ኑሮ ተወደደ ተብሎ ሲነገራቸው ‹‹አቤት! አቤት! ይሄኔ ዘይቱን ደብቀውት ነው፤ ሊገሉን ነው፣ እንደው ምን አደረግናቸው የሚያስርቡን እኛ ምን በደለን፣ በላባችን ሰርተን በገባን እንደው ምን አድርጉ ነው የሚሉን›› ይላሉ:: ችግሩ ላይ ይራቀቁበታል:: አብዝተው ስለችግሩ ያስባሉ:: ሁለተኞቹ ግን ኑሮ ተወደደ ሲባሉ፣ ችግሩን ሲሰሙ ‹‹ምን ይሻላል ይበልጥ ሳይወደድ ቶሎ እንግዛ እንዴ›› ይላሉ:: ወደ መፍትሄው በቶሎ ይገባሉ:: ‹‹ምንድን ነው የሚሻለው ገቢዬን ላሳድግ፣ ሁለት ሶስት ሥራ ልሥራ ኑሮ ከተወደደ›› ይላሉ::
አንተ የትኛው ላይ ነህ? ችግሩ ላይ ነው አብዝተህ ጊዜህን የምታጠፋው ወይስ መፍትሄው ላይ? የመፍትሄ ሰው መሆን አለብህ:: ቴሌቪዥን ላይ የማትፈልገው ፕሮግራም ሲመጣ ምንድን ነው የምታደርገው? ሪሞቱን አንስተህ ትቀይራለህ አይደል! አየህ አሁንም ስለችግሩ ማሰብ ስትጀምር ትፅፈውና ስለመፍትሄው ማሰብ ትጀምራለህ:: ወደ መፍትሄው ማተኮር አለብህ:: ስለዚህ ወረቀት ላይ አምስት መፍትሄዎችን ዘርዝር::
3ኛ. ጥድፊያውን አቁም
ከጊዜ ጋር አትታገል:: ከጊዜ ጋር ስለምትታገል ነው አብዝተህ የምታስበው፤ የምትጨነቀው:: መቼም ገጥሞህ ያውቃል ለምሳሌ ፈተና ክፍል ውስጥ አስተማሪው ‹‹አሁን አስር ደቂቃ ነው የቀራችሁ እስቲ ፈጠን ብላችሁ አሰርክቡኝ›› ሲል ትደነግጣለህ:: ለምን? ያለህ አስር ደቂቃ ነው:: አንተ የቀረህ ደግሞ ብዙ ጥያቄ ነው:: ስለዚህ ትደናበራለህ:: ቶሎ ለመሥራት ስትል ጥድፊያ ውስጥ ትገባለህ:: ሁሉንም ለመመለስ ስትል የምታውቀው ሁሉ ይጠፋብሃል:: ጥድፊያ ውስጥ ትገባና ‹‹ምን ነበር አውቀዋለው እኮ›› ትላለህ:: ሳታውቀው ግን ሁሉንም ገምተህ ትወጣለህ:: መጨረሻ ላይ ጥሩ ውጤት አይመጣም::
ሕይወትም እንደዛ ነው:: አንዳንዴ አንተ የምታስበው ነገር በምትፈልገው ፍጥነት አለመሳካቱ አብዝተህ እንድታስብ ያደርግሃል:: አንዳንድ ሰው እኔ በ25 ዓመቴ፣ በ26 ዓመቴ ጥሩ ቢዝነስ ገምብቼ ጥሩ ገቢ ይኖረኛል ይላል:: ልክ 25 ዓመቱን ሲያከብር ራሱን ሲያየው እንኳን ጥሩ ቢዝነስ ሊገነባ ተቀጥሮ እንኳን እየሠራ አይደለም:: እሱን የሚቀጥረው ሰው እንኳን የለም:: ግራ ይገባዋል በጣም ይጨነቃል:: አንዳንድ ሴቶች በ30 ዓመቴ አገባለሁ፤ እወልዳለሁ ብለው ያቅዱና 30 ዓመታቸው ላይ እንኳ አግብተው ሊወልዱ ይቅርና ቅርፅ ያለው የፍቅር ግንኙነት ውስጥ አይገቡም::
ሁላችንም የሆነ ነገር እንፈልግና በምንፈልገው ፍጥነት ካልተሳካ አብዝተን እናስባለን፤ አብዝተን እንጨነቃለን:: የጭንቀታችን ጉዳይ ጥድፊያ ነው:: ሕይወት ፎቅ ይመስል ስለሊፍት እናስባለን:: አቋራጭ አጭር መንገዶችን እናስባለን:: ይሄኔ እኮ ተረጋግተንና እጃችን ላይ ያለውን ነገር አስተካክለን ብንጓዝ ነገሮች ቶሎ ተስተካክለው በምንፈልገው ፍጥነት ልንደረስ እንችላለን:: ግን ጥድፊያ ላይ ነን:: ወዳጄ ከጊዜ ጋር አትወዳደር:: የፈጀውን ይፍጅ እንጂ እኔ በሂደትም ቢሆን የምፈልገበት ደረጃ እደርሳለሁ በል::
አየህ! ትዕግስት ማለት የምትችለውን ሁሉ እያደረክ የሚሮጠውን ጊዜ ማሳለፍ መቻል ነው:: ጊዜው ይሮጣል:: ከአቅምህ በላይ ነው:: አንተ ግን የምትችለውን ትሠራለህ:: በዛ ውስጥ ግን ትጠብቃለህ:: ትታገሳለህ:: አቋራጭ ማሰብ የለብህም:: አየህ! አሁን መታገስ ስትጀምር አዕምሮህ ነፃ መሆን ይጀምራል:: አቅምህን መጠቀም ትጀምራለህ:: እንደውም ነፃ ስትሆን በምትፈልገው ፍጥነት ማደግ ትችላለህ:: ጊዜን እቆጣጠረዋለሁ፤ እንዴትም ብዬ በአቋራጭ የምፈልግበት እደርሳለሁ ስትል፣ አብዝተህ ስታስብ፣ ስትጨነቅ ጊዜ ካንተ በላይ ሃያል ነው:: ይጥልሃል:: መታገስ አለብህ::
ደስ የሚለው ጊዜ የሚወስድብህ መጀመሪያ አካባቢ ነው:: መለወጥ እስክትጀምር ነው:: በጣም ጊዜ የሚወስድብህ መሠረት እስክትዘረጋ ነው:: መሠረቱ ላይ ከተጨነክ ፎቁን ወደላይ መዘርጋቱ በጣም ቀላል ነው:: ሕይወት እንደዛ ነው:: ስለዚህ አቋራጩን ተወው:: ጥድፊያውን አቁም:: አብዝተህ የምትጨነቀው፣ አብዝተህ የምታስበው ከጊዜ ጋር እየተወዳደርክ፣ እየታገልክ ስለሆነ ነው:: መታገስ አለብህ ወዳጄ!
4ኛ.የማሰቢያ ጊዜ መድብ
በዚህ ሰዓት ለሃያና ሰላሳ ደቂቃ አስባለው በልና ፕሮግራም ያዝ:: ልክ ያ ሰዓት ሲደርስ አላርም ሙላ:: ከዛ ማሰብ ጀምር:: የባጥ የቆጡን የፈለከውን አስብ:: ከዛ ሰላሳ ደቂቃ ሞልቶ ልክ አላርሙ ሲጮህ ወደ ሥራህ ተመለስ:: ወደራስህ ተመለስ:: አሁን ለሃሳብህ ቦታ ሰጥተኸዋል:: ስለዚህ በጣም ወሳኝ ሥራ እየሠራህ ሃሳብ አይመጣብህም:: አየህ! አንዳንድ ጊዜ ለማሰብ የሚሆን ጊዜ ስላልመደብክ ወሳኝ ሰአት ላይ ጭንቀትና ሃሳብ ይመጣል:: ልትተኛ ስትል ሃሳቦች ይመጣሉ:: እንቅልፍ አይወስድህም:: በጣም ወሳኝ ሥራ ልትሠራ ስትል ሃሳብ ይመጣብሃል::
አሁን ግን ጊዜ መድበህለታል:: የማትፈልገውን ስልክ እንደማታነሳ ሁሉ የማትፈልገውን ሃሳብ አሁን አላስብህም፤ በኋላ እንገናኝ ትለዋለህ:: ለማሰብ ቀጠሮ ማስያዝ፣ ጊዜ መመደብ በጣም የሚገርም መፍትሄ ነው:: ጭንቀትህንና አብዝቶ ማሰብህን ታቆማለህ::
5ኛ.ትንንሽ ሃሳቦችን አስቀይስ
አዘርግ የተባለ ደራሲ ‹‹ትንንሽ ሃሳቦች ሁሌም ትንንሽ ናቸው:: ነገር ግን የትልቁን ቦታ ይይዛሉ›› ይላል:: አንዳንዴ ትንንሽ የሚባሉ ሃሳቦች አዕምሮህን ይቆጣጠሩታል:: ምንም ስለማይጠቅምህ ሰው አብዝተህ ትጨነቃለህ:: ወይም ደግሞ ከሰዎች ጋር ራስህን እያወዳደርክ ረጅም ሰዓት ታጠፋለህ:: እንደነዚህ አይነት ሃሳቦች በጣም ትንንሽ ናቸው:: ግን አዕምሮህ ላይ ትልቅ ቦታ ይይዛሉ:: ጊዜ ይሻሙብሃል:: ጉልበትህን ይመጡታል:: እንደዚህ አይነት ሃሳቦችን ማስቀየስ ነው ያለብህ:: መሸሽ ነው ያለብህ:: በድርጊትና በተግባራዊ ነገሮች መሸሽ:: ለምሳሌ ትናንሽ ሃሳቦች ወደ አዕምሮህ ሲመጡብህ ተነስተህ ቤትህን አስተካክል:: አልጋህን አንጥፍ፤ አፀዳዳ:: በአንዴ ትረሳዋለህ ያንን ሃሳብ:: ወይ ስፖርት ሥራ፤ ተራመድ ወይ ደግሞ በጎ ፍቃደኛ ሁንና የሆነ ቦታ አገልግል:: አልያ አጠገብህ ያለ ህፃን ልጅ አንሳና አጫውት:: ይህን ስታደርግ ትናንሽ ሃሳቦች ካንተ መራቅ ይጀምራሉ:: ትልልቅ ሃሳቦችን መሸሽ የለብህም:: ለትልልቅ ሃሳቦች ቁጭ ብለህ መፍትሄ ነው የምትፅፈው:: ትንንሽ ሃሳቦችን ግን መሸሽ አለብህ:: መፍትሄ የላቸውማ!
ስለዚህ ትንንሽ ሃሳቦች ሲመጡብህ ‹‹ኧረ! ይህን ማሰብ ለእኔ አይመጥንም በጣም የወረደ ሃሳብ እኮ ነው›› ማለት አለብህ:: አንዳንዴ ሥራ ስለፈታህ ይሆናል እንደነዚህ አይነት ሃሳቦች አዕምሮህ ውስጥ የሚመጡት:: ‹‹ሥራ የፈታ ሰው የሰይጣን መጫወቻ ይሆናል›› ይባላል:: አየህ ሥራ ስለፈታህ የማይረቡ ሃሳቦች አዕምሮህን ይሞሉታል:: ስለዚህ ወደ ሥራህ ተመለስ:: የሆነ ሥራ መሥራት ጀምር:: ያኔ ትንንሽ ሃሳቦችን ታስቀይሳቸዋለህ::
አሁን ግን ጊዜ መድበህለታል:: የማትፈልገውን ስልክ እንደማታነሳ ሁሉ የማትፈልገውን ሃሳብ አሁን አላስብህም፤ በኋላ እንገናኝ ትለዋለህ
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም