የስፖርት ማዘው ተሪያዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እየተገነቡ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ያሉና የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እየተገነቡ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው በመሰራታቸው ላይ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው።

ከሰሞኑ ከተማ አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ስፖርት ፌስቲቫል እና ውድድርን ለ14 ጊዜ በማካሄድ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ አካል ጉዳተኞችን በስፖርቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማድረግ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል። በየደረጃው የሚሰሩ የማዘውተሪያ ስፍራዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ እየተገነቡ መሆኑንም ጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ፤ በአሁኑ ወቅት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ መስራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ግዴታ መሆኑን ይጠቁማሉ። በከተማዋ የሚገነቡ የስፖርት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ከጅምሩም አካል ጉዳተኞችን ከግምት የሚያስገቡ መሆናቸውን የሚያስረዱት ኃላፊው፤ ቀደም ብለው የተገነቡትም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ በመስተካከል ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት የሁሉም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ቀዳሚው መለኪያ ዓይነ ስውራን፣ ዊልቸር ተጠቃሚዎችና እና ሌሎች የጉዳት አይነቶች ያሉባቸውን ያማከሉ መሆኑን ነው የገለፁት። ከዚህ ውጪ ከሆኑም የደረጃ ማረጋገጫና እውቅና ማግኘት አይችሉም። ይህ የክትትልና ቅድመ ሁኔታን የማሟላት ጉዳይ ትልልቅ ሜዳዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ሌሎች ሜዳዎች ለአካል ጉዳተኞች የማይመቹ ከሆኑ የማስተካከል ስራው እንደሚከናወንም ኃላፊው አስረድተዋል።

በዚህም የስታዲየም መግቢያዎችና መጸዳጃዎችን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲደረጉ በትኩረት እየተሰራ ነው። ከተማዋም ዘመናዊ ከተማ የምትባለው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባማከለ ሁኔታ ስትሰራ እንደሆነ አቶ ዳዊት ያስረዳሉ። ከተማ አስተዳደሩም የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር አንዱ አጀንዳው አድርጎ እየሰራ መሆኑን አክለዋል። የሚገነቡት የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችና መንገዶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እያደረጉ በመሆኑም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች እኩል ትኩረት የመሰጠቱ ማረጋገጫ ነው ይላሉ።

በተጨማሪም በከተማዋ የሚገኙትን አካል ጉዳተኞች ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ቢሮው ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ እነሱን ያማከለና ታሳቢ ያደረገ አደረጃጀቶችም ይገኛሉ። መስማት የተሳናቸው እና የአካል ጉዳተኞች ማህበር ሕዝባዊ አደረጃጀት በአካል ጉዳተኞች ከሚመሩት ውስጥ ይጠቀሳሉ። የውድድር ተሳትፎውን ለማረጋገጥም 11ዱም ክፍለ ከተሞች የውስጥ ውድድሮችን አካሂደው ወደ ከተማ አቀፍ የሚሄዱ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ተሳትፎን ለማረጋገጥ የተካሄዱት ውድድሮች ምን ዓይነት ፋይዳ እንደነበራቸው ጥናት ተደርጎ ወደዚህ መገባቱም ተጠቁሟል። ከዚህ ቀደም ለመርሃ ግብር ማሟያ ብቻ የሚካሄደው ወድድር አሁን ሁሉም ክፍለ ከተሞች ለአካል ጉዳተኞች ስፖርት በቂ ዝግጅትና ቁሳቁስ እንዲያሟሉ ማድረግ ተችሏል። ከከተማው ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ከመስማት የተሳናቸው፣ ከአካል ጉዳተኞች እና አይነስውራን ማህበራት ጋር በቅንጅትና በትብብር የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ በመሰራቱም ተሳትፎው እንደጨመረ አቶ ዳዊት አክለዋል።

እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፤ በቢሮ በኩል በዓመት አንዴ መሰል ውድድር የሚካሄድ ሲሆን በፌዴሬሽኑ በኩልም የፋይናንስ ድጋፎች በማድረግ ተጨማሪ ውድድሮችን ለማካሄድም ታቅዷል። በቀጣይም የስፖርት ዓይነቶቹን ቁጥርና የጉዳት ዓይነቱን ጨምሮ ለማካሄድ ታቅዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይንሸት ግርማ (ዶክተር)፣ ለአካል ጉዳተኞች ስፖርት ትኩረት መሰጠቱንና እነሱን ያማከለ ውድድር እየተካሄደ መሆኑን ይናገራሉ። የአካል ጉዳተኞች ውድድር በከተማ ደረጃ አንዴ ብቻ የሚካሄድ በመሆኑ ሁለት ጊዜ ለማካሄድ ጥረት ይደረጋልም ብለዋል። የአካል ጉዳተኞች አካታችነትና ተጠቃሚነት ላይ የሚታይ ክፍተት በመኖሩ ይህንን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶና መሬት ላይ ወርዶ መሰራት እንደሚኖርበትም ገልጸዋል።

14ኛው ከተማ አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ስፖርት ፌስቲቫልና ውድድር በወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና የከተማው ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ቢሮ በትብብር ከኅዳር 24/2017 ዓ.ም አንስቶ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተናጋጅነት በድምቅት እየተካሄደ ሲሆን፤ እስከ ታህሳስ 6/2017 ዓ.ም በፉክክሮች ታጅቦ ይቀጥላል። ውድድሩ “የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችነትን እና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል በአትሌቲክስ፣ በዳርት፣ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ ክብደት ማንሳትን ጨምሮ በ7 የስፖርት ዓይነቶች ከ10 ሺ በላይ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞች ይሳተፉበታል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You