ያልተቀየረ ወገን የማይቀይረው እውነታ!

እንደ ማህበረሰብ ወይም ሀገር በተፈጥሮ አደጋ፣ በጦርነት፣ በወረርሽኝና በመሳሰሉት ሳቢያ ለተወሰነ ጊዜ ለተረጂነት ሊጋለጥ ይችላል:: ይህ ሁኔታ የምልልስ፣ የቆይታ ልዩነት ከሌለ በስተቀር ተፈጥሯዊ ክስተት ነውና እዚህም እዚያም የነበረ፣ ያለ፣ ሊኖር የሚችል ነው::

ይህ በሚያጋጥምበት ጊዜ አደጋውን ሊያደርስ የሚችለውን ቀውስ ለመቆጣጠር በሚደረግ ጥረት ፈተናዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ:: አደጋ ድንገተኛ ነገር ነውና በእጅ ያለውን እምቅ አቅም ማሰብ ጭምር ሊሳን ይችላል፤ ለክፉ ቀን በሚል የተቀመጠም ቢኖር ላይበቃ ይችላል፤ የተከሰተው አደጋ ነዋ::

ይሄኔ ወዳጅ ሀገሮች ብቻም ሳይሆኑ ጥሪ የተደረገላቸው ሀገሮች፣ ማህበረሰቦች፣ ወዘተ በአስቻጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝን ማህበረሰብ በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለመድረስ ይረባረባሉ፤ አደጋው እንዲሁም አደጋው ሊያደርስ የሚችለው ቀውስ በቁጥጥር ስር ውሎም፣ አልፎም ተርፎ ወደ መደበኛው መስመር መመለስ እስከሚቻል ድረስ የምግብና የመሳሰሉት ድጋፎችን ሲያደርጉም ይስተዋላል::

ሀገራችን በአንዳንድ ክልሎቿ በተደጋጋሚ በተከሰተባት አስከፊ የድርቅ አደጋ ሳቢያ ይህን በሚገባ ታውቀዋለች:: የደርቅ አደጋዎቹ የዜጎችን ህይወት የቀጠፉባቸው፣ አቅማቸውን የሰለቡባቸው፣ አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን ሰብላቸውን አጥተው ቄያቸውን ጥለው እስከመሰደድ የደረሱባቸውም ወቅቶች እንደነበሩ ይታወሳል::

የሀገሪቱ መንግሥታት በአደጋዎቹ ለተጎዱ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ እርዳታ ሲያቀርቡ አስተውለናል:: የ1977ቱን የድርቅ አደጋ ተከትሎ የነበረውን ርብርብ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል:: ግዙፍ የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ተቋቁሞ ለዓመታት ሠርቷል::

ከዚህ በተጓዳኝም ችግሩን ለዘለቄታው ለመቀልበስ የተፈጥሮ ሀብታቸው ከተመናመነባቸውና በድርቅ አደጋ በቀላሉ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን /አርሶ አደሮችን/ ወደ ተለያዩ ለም አካባቢዎች ወስዶ እስከ ማስፈር የደረሰ እርምጃ ወስደዋል:: በወቅቱ ሰፈራው ሌላ ፖለቲካዊ ትርጉም ቢሰጠውም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በሰፈራው እንዲካተቱ ተደርጓል:: በዚህም ራሳቸውን እስከሚችሉ ድረስ የተለያዩ ድጋፎች እየቀረበላቸው በኖሩበት የግብርና ሥራ እንዲሰማሩ ተደርጓል:: በዚህም በርካታ ሀገሮች፣ ማህበረሰቦች ከእነዚህ ተጎጂዎች ጎን በመቆም አጋርነታቸውን፣ ኃላፊነታቸውን ፣ የወገን አለኝታነታቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል::

ሀገሪቱ ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት ተከትሎ በዜጎች ላይ የደረሰው አደጋ የበለጠ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግም በገዛ ራሷ ዜጎችና በመንግሥት አቅም ብዙ ጥረት አድርጋለች፤ በወዳጅ ሀገሮች፣ በእርዳታ ሰጪ ተቋማት ድጋፍ ሲደረግላት እንደነበር ይታወቃል:: ይህ ርብርብ ዜጎችን ከከፋ ሞት፣ ጉዳት፣ ሀገርንም ከከፋ ቀውስ መታደግ ችሏል::

ገጽታዋንም በእጅጉ የጎዳባቸውን ጊዜያት ታስታውሳለች:: ይህ ጉዳት ጥሎባት ያለፈውን መጥፎ ጠባሳ መቼም አትረሳውም:: በእነዚህ ክፉ ቀናት ከአጠገቧ ሆነው አለን ያሏትንም አትዘነጋም፤ ሀገሪቱና ሕዝቧ ለእዚህ ታላቅ ውለታም በየወቅቱ በእነዚያ ክፉ ቀናት ከአጠገባቸው ሆነው ድጋፍ ላደረጉላቸው ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል:: ምስጋናውንም ድጋፍ ያደረጉ ሀገሮች ድረስ በመሄድ ጭምር ያቀረቡበት ሁኔታ እንዳለም ይታወቃል::

ድጋፍ ያደረጉ አካላት ፣ የሀገሪቱ መንግሥትና ዜጎች ጥረታቸው እልቂትን፣ ስደትን፣ ወዘተ ከመቀነስ አልፎም ተርፎ ማስቀረት የቻለ ብቻ አይደለም:: ሰፋሪዎቹም ጠንክረው በመስራት የድርቅ አደጋን እንዲበቀሉ አስችሏቸዋል::

ድርቅ እየተመላለሰ እናት አባታቸውን ወንድሞች እህቶቻቸውን ልጆቻቸውን ቢበላባቸውም፣ ለእንግልት ቢዳርግባቸውም፣ ሀብት ንብረታቸውን ቢያሳጣቸውም በተፈጠሩላቸው ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም፣ ጠንክረው በመስራት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፈው ለገበያ የሚያመርቱ ወይም ትርፍ አምራች እስከመሆን የደረሱበት ሁኔታም ታይቷል:: በአንዳንድ ክልሎች ከሚገኙ እነዚህ ህብረተሰቦች የሚሰማውም ዜና ይህንን ያረጋገጠ ነው::

መንግሥት የድርቅ አደጋ ከሚመላለስባቸው አካባቢዎች ተጎጂዎችን ወደ ሌላ አካባቢ ወስዶ ከማስፈር ይልቅ ለድርቅ አደጋ ተጋላጭነታቸውን የሚቀንሱ ስትራቴጂዎችን በመንደር በሴፍቲኔት መርሀ ግብር አማካይነት ጥሪት እንዲያፈሩ ለማድረግም ሠርቷል፤ ልማታዊ ሴፍቲኔት በተሰኘው በዚህ መርሀ ግብር አርሶ አደሮች ከመደበኛው የግብርና ስራቸው ጎን ለጎን በእንስሳት እርባታ፣ ንብ ማነብ፣ ሌሎች ስራዎች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ ድርቅ ቢከሰት በቀላሉ ለጉዳት የማይዳረጉበትን ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፤ ድርቅ ኮሽ ባለ ቁጥር ዜጎች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ወደሌላ አካባቢ ይሰደዱ የነበረበትን ሁኔታ ለማስቀረት ተሰርቶ ውጤታማ መሆን ተችሏል::

የድርቅ አደጋን ለመከላከል እነዚህና እነዚህ ላይ ብቻ አይደለም ሲሰራ የቆየው:: ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ግድቦችን በመገንባትና ውሃ በማቆር፣ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል እና የመኖ ልማት በማካሄድ የድርቅ ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እየተቻለ ነው::

ዜጎች ድርቅ ሲከሰት አካባቢያቸውን ለቀው የሚሄዱበትን ሁኔታ ማስቀረት እየተቻለ ነው:: ባሉበት ቦታ ድጋፍ በማድረግ ለሚቀጥለው ምርት ዘመን ማዘጋጀት ላይ በትኩረት ይሰራል:: ለዚህ ሁሉ ስራ የተለያዩ አካላት ድጋፍ ስራ ላይ ውሏል:: ድጋፉን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ተሰርቷል፤ የድርቅ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ስራ ውሎም ውጤታማ ተግባር ተከናውኖበታል:: ይህ ሁሉ ግን የድርቅ አደጋ ጉዳት ያደረሰባቸውንና ጉዳት ሊያደርስባቸው የሚችሉትን ለመታደግ የተካሄደ ስራ ነው::

ሀገሪቱ ድርቅ በተደጋጋሚ ያደርስባት የነበረውን ጉዳት ለመቀነስ ስታከናውናቸው ከነበሩ ተግባሮች ጎን ለጎን በግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ አጥብቃ ሰርታለች:: ሀገሪቱ እየጨመረ የሚመጣውን የግብርና ምርቶች ፍላጎት ለማሟላት፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብአቶችን በስፋት ለማቅረብ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየወጣባቸው ወደ ሀገር ውስጥ ይገባ የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ የስንዴ ምርት ለመተካት እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች ምርታማነት ለመጨመር በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል፤ እየተሰራም ይገኛል:: የምግብ ዋስትናንና የምግብ ስርአትን አልፎም ተርፎ የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የዚህ ዘመን ቁልፍ ተግባር ተደርገው እየተሰራባቸው ናቸው::

በስንዴ ልማት እየተከናወነ ያለው ስኬታማ ተግባር ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል:: ሀገሪቱ ለስንዴ ልማት የሚሆን ሰፊ ለም መሬት፣ አየር ንብረት፣ ውሃ ሰፊ ጉልበት እያላት ስንዴ ለዚያውም ለተቀረው ልማቷ በእጅጉ የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሪ እየገፈገፈች ስትገዛ ኖራለች:: ግዥው የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተደረገ እንደመሆኑ መደረግ ያለበት ነው::

ሀገሪቱ በአንድ ወቅት በተፈጠረባት ጫና የተነሳ ለዜጎቿ የሚያስፈልገውን ይህን ስንዴ ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ መድባ ስንዴ አምራቾች ወይም አቅራቢዎች እንዳይሸጡላት ጫና ተደርጎባቸው እንደነበር ይታወሳል:: ይህ ችግር የምግብ ሉአላዊነት ችግርም አስከተለ ማለት ነው:: ይህ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው:: ምን ይሄ ብቻ፤ ማዳበሪያ ለመግዛት አቅሙ እያላት እንዳይሸጥላት በአቅራቢዎች ላይ ጫና ተደርጎ እንደነበርም ይታወሳል::

ሀገሪቱ በለውጡ መንግሥት ይህን ፈተና ለዘለቄታው ተሻግራዋለች:: በእርዳታ ስንዴ ተጠፍንጋ የኖረችውን ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ ስንዴ ከዓለም ገበያ እንዳትገዛ ተደርጋ የነበረችው ኢትዮጵያ ፣ ማዳበሪያ መግዣ እንድታጣ ተደርጋ የነበረችው ኢትዮጵያ ከእዚህ ሁሉ እስር ውስጥ ፈልቅቃ ወጥታ በስንዴ ምርት ውጤታማ መሆኗን ዓለም ጭምር የመሰከረላት ለመሆን በቅታለች::

በመኸርና በበልግ ብቻ ይመረት የነበረው፣ ምርታማነቱም እዚህ ግባ ይባል ያልነበረው ስንዴ ፣ በእነዚህ የምርት ወቅቶች በስንዴ የሚሸፈነው ማሳ በእጅጉ እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ በሄክታር የሚመረተው ስንዴ መጠንም እየጨመረ መጥቷል::

የስንዴውን ልማት ይበልጥ ከፍታ ላይ ያወጣው ደግሞ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ነው፤ ይህ በቆላማው የሀገሪቱ አካባቢ የተጀመረ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በወይና ደጋና ደጋ አካባቢዎችም እየተስፋፋ ይገኛል:: ከመስኖ ስንዴ ልማት የሚገኘው ምርትም በየዓመቱ እየጨመረ ይገኛል::

በመኸር፣ በበልግና በመስኖ ልማት በየዓመቱ በስንዴ የሚሸፈነው መሬት በእጅጉ እየሰፋ፣ የሚያስገኘው የምርት መጠንም እየጨመረ መጥቷል:: ባለፈው በጀት ዓመት በአጠቃላይ 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የተመረተ ሲሆን፣ ዘንድሮ ደግሞ ይህን አሀዝ 300 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው::

በስንዴ ልማቱ በተገኘው ውጤት ሀገሪቱ ስንዴ ከውጭ ማስመጣት አቁማለች፤ የስንዴ ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ችላለች:: ከዚህም አልፋ ለጎረቤት ሀገሮች ስንዴ መሸጥ ጀምራለች:: በሰሜኑ ጦርነት ማግስት በተፈጠረ የውጭ ኃይሎች ጫና ለሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልግ ስንዴ አቅራቢ እንዳይኖር በሀገሪቱ ላይ ዘመቻ በተከፈተበት ወቅት ይህን አቅርቦት የሞላችው ራሷ መሆኗም አቅሟ ምን ያህል እንደጨመረ ከሚያመለክቱት መካከል አንዱ ነው::

ይህን ምርታማነት ለማስቀጠልም በስፋት እየተሰራ ነው:: ይህን ለማድረግ ደግሞ ተፈጥሮም፣ የመንግሥት ዝግጁነትና ቁርጠኝነትም፣ ያለፉት ዓመታት የስንዴ ልማቱ ተሞክሮ ከበቂ በላይ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው:: የስንዴ ልማቱ በስንዴ ብቻ ተወስኖ አልቆመም:: ልማቱን በቢራ ገብስ መድገም ተችሏል፤ የቢራ ገብስ ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት ተሸፍኗል:: ይህን ውጤታማነት በሩዝ፣ በሰሊጥ፣ በለውዝ፣ በአኩሪ አተር፣ በቦሎቄ ልማት ለመድገም እየተሰራ ነው::

እነዚህ ሁሉ የሀገሪቱ ስኬቶች በተለይ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ታላቅ እምርታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማትና ያደጉት ሀገሮች ጭምር መስክረውለታል:: የአፍሪካ ልማት ባንክ መሪዎች የሀገሪቱን የስንዴ ልማት ስኬት ሁሌም ይጠቅሳሉ:: ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ይህንኑ ይናገራሉ::

ሀገሪቱ በቅርቡ ከርሃብ ነጻ የሆነች ዓለም መፍጠርን ያለመው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ማስተናገዷ ይታወቃል፤ ለእዚህ ጉባኤ አዘጋጅነት ስትመረጥ በምክንያት ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ የስንዴ ልማቱ ስኬት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: በመድረኩም የተለያዩ ወገኖች ይህን ስኬት ጠቅሰውታል:: ቀደም ሲልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በእዚህ የስንዴ ልማት ባከናወኑት ተግባር የዓለም እርሻ ድርጅት ሽልማት የሰጣቸው መሆኑም ሌላው ታላቅ ምስክርነት ነው::

የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚቻል ካለፉት የዘርፉ ስኬቶች ብዙ ተሞክሮዎች ተገኝተዋል:: ግብርናው ሜካናይዝድ እንዲሆን፣ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ እየተደረገ ነው፤ በቂ የማዳበሪያ አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ መንግሥት ድጎማ እያደረገ ይገኛል፤ አርሶ አደሩ መሬቱን በባንክ አስይዞ በመበደር ምርትና ምርታማነቱን የሚያሳድግበት ሁኔታም እየተፈጠረ ነው፤ እንደ ማዳበሪያ ያሉ ግብአቶች፣ ባለሙያ፣ ገበያ በሀገር ውስጥም በውጭም ተመቻችቶለታል፤ ዓመታዊ የግብርና ምርትን በእጅጉ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራም ነው::

የግብርናውን ዘርፍ ስኬቶች ጠቀስኩ እንጂ በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት በተለይ በዓባይ ግድብ የተከናወነው ተግባር፣ በኢንዱሰትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም ከነበረበት እየጨመረ ያለበት ሁኔታ፣ ከውጭ የሚመጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በመተካት በኩል እየታየ ያለው እምርታ ፣ ሀገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ያለችበት ሁኔታ፣ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ከምሥራቅ አፍሪካ ያላት የመሪነት ስፍራ፣ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገሮች እንዲሁም ከዓለምም የምትገኝባቸው ደረጃዎች ሀገሪቱ ምን ያህል በልማቱ ርቃ እየተጓዘች መሆኗን የሚያመላክቱ ሌሎች ጉልህ ማሳያዎች ናቸው::

እነዚህ ስኬቶች እየተመዘገቡ ባሉበት በእዚህ ዘመን ሀገሪቱ በአንድ ወቅት የነበረችበትን አስከፊ የድርቅ ታሪክ ዛሬም ያለ በሚያስመስል መልኩ መተረክ ውስጥ የገቡ ደካሞች ታይተዋል:: የሀገሪቱን የ1977ቱን ታሪክ እንደ አዲስ በመቀስቀስ የሚወዛወዙ አካላት ከወደ ምእራባውያኑ ብቅ ብለዋል:: ይህ የሀገሪቱን አሁናዊ ለውጥ ዞር ብሎ ያልተመለከተ የቀድሞ ታሪክን በዚህ ወቅት እንደ አዲስ ማቀንቀን ምን ለማለት ተፈልጎ እንደሆነ መገመት አይከብድም::

በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን እውነታ ለመቀበል ፈቃደኛነቱ የሌላቸው ሆኖ እንጂ ያን ታሪክ አንስተው መቆም አልነበረባቸውም:: አሁን በጥሩ እየተገነባች ለምትገኘው ኢትዮጵያ የበኩላችንን ሚና ተጫውተናል፤ ጠጠር አቀብለናል ቢሉ ይሻላቸው ነበር:: ድጋፉ እዚያ ደረጃ ይደርሳል ከተባለ ማለቴ ነው::

ከዚያ ውጪ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እነሱም ሆኑ ሌሎች ተመሳሳይ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ሲያደርጉ የኖሩትም ሆነ እያደረጉ የሚገኙት አሳ መስጠት እንጂ አሳ እንዴት እንደሚጠመድ ማሳየትን አይደለም፤ ከእነሱ ይልቅ እኛ ድጋፋቸውን እንደ ልማታዊ ሴፍቲኔት ላሉ ተግባሮች እያዋልን የዜጎችን የድርቅ አደጋ ተጠቂነት ለመቀነስ፣ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ለማድረግ ሰርተንበታል::

የድርቅ አደጋ እዚህም እዚያም እየተከሰተ ይገኛል:: ያ አደጋ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች አስቀድሞም አደጋው ከተከሰተ በኋላም በሀገሪቱ ይሰራል:: በዓመታት ጊዜ ውስጥም ያን አስቀያሚ ታሪክ መቀየር የተቻለበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገሪቱ በተለይ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ስኬት በስኬት እየሆነች ትገኛለች::

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሊነገሩላት ሊተረኩላት የሚገባቸው እነዚህ ስኬቶችና ለስኬቶቹ ያበቋት መንገዶች፣ በእነዚህ ላይ የተመሰረተው ቀጣይ ብሩህ ተስፋዋ እንጂ ያለፉት የክፉ ቀን ታሪኮቿ ብቻ አይደሉም:: እነዚህ በ1970ዎቹ ታሪክ ላይ የቆሙ ወገኖች/ እነዚያ ወገኖች ባለውለታዎቻችን እንደመሆናቸው አሁንም ወገኖች ብንላቸው ችግር የለውም/ ያልተቀየሩ ናቸው:: ያልተቀየረ ወገን ደግሞ የተቀየረውን የኢትዮጵያ እውነታ ሊነግር ሊመሰክር አይችልምና እኛ ለከፍታ ያበቁንን ስራዎቻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን!

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You