ወፎች በዝማሬ ንጋቱን ሲያበስሩ ሞባይሌ ደወለ።
አስደግመሽብኝ አለቃ ፈንቴን፣
ሳር ቅጠሉ ሁሉ መሰለኝ አንችን።
ተብሎ የተዘፈነላቸው ጎበዝ መዳፍ አንባቢ ናቸው፤ ሲለግሙ አይጣል ነው።
በመጀመሪያው ትውውቃችን ኮከቤን ቆጥረው መጽሐፍ ገለጡና “ረቡዕ፣ አርብ፣ እሁድ አይሆንህም፤ ጠይም ሴት ክፍልህ ናት” ሲሉኝ ለኑሮስ የትኛው አየር ንብረት ይሆነኛል? ብዬ ብጠይቃቸው “እሱን ሜትሮሎጂ ጠይቅ” ያሉኝ አይረሳኝም።
በሽቦ አልባው ስልክ የሚያነጋግሩኝ አለቃ ፈንቴ ናቸው፤ ሰላምታ እንደተለዋወጥን “እህል ሳትቀምስ በአስቸኳይ ወደ መርጦ ለማርያም አቅና፤ የቀረህ እንደሆነ ተደግሶልሃል” ሲሉኝ በፍርሀት እየተርበተበትኩ ምን? ብላቸው መልስ ሳይሰጡኝ ጠረቀሙት።
መጽሐፍ ገላጩ ሁሉ በየ ነገሩ ለምን እንደሚያስደነብሩኝ አይገባኝም።
ሞትን እንደምፈራ አውቀውብኝ ይሆን? ምን አይነት ጣጣነው።
እህል ሳትቀምስ ከቤት አትውጣ፣ ፀሀይ ሳይወጣ የታመመ ሰው አትጠይቅ፣ መንገድም አትሂድ ያሉኝን አልጣስኩም፤ እስካሁንም እያከበርኩት እገኛለሁ።
ረቡዕ፣ አርብ፣ እሁድ ቀናት እንደማይከፍሉኝ እያወቁ ምን አጠራራቸው? ቀርቼ ምን እንደደገሱልኝ ለማየት ብጓጓም ፈረንጅ የሐበሻን እግር ሲያጥብ ካላየሁ መሞት አልፈልግምና ከመኝታዬ ተነሳሁ።
እጅ መንሻ እንዲሆነኝ አረቄዬን አሸንቅሬ የመርጦለ ማርያምን መኪና ያዝሁ።
ጉዞውም ተጓዡም ተባብረው ድብርት ለቀቁብኝ፤ የጓዳ ችግሮቻቸውን ሰው ይሰማናል ሳይሉ ይዘረግፋሉ፤ አቦ የአዲስ አበባ ሰው ይምጣብኝ እንጂ በየንግዱና በየትራንስፖርት አገልግሎቱ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ሲጨዋወት እያልኩ ልዩነታቸውን አምሰለሰልሁ።
የአዲስ አበባ ሴት ባሏን በሺህና በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለኢንቨስትመንት ስትጠይቅ የክልል ሴት ደግሞ ለዕድር ሁለት ብር ጠይቃለች፤ የአዲስ አበባ ወጣት ሲኒማ ቤት የክልል ወጣት ጠላ ቤት ይውላሉ፣ የአዲስ አበባ ህጻን ልጅ ሲያለቅስ በኬክ ሲያባብል፣ የክልል ህጻን ልጅ ሲያለቅስ ደግሞ በኩርኩም ዝም ይሰኛል።
“ትኬት መልሱ” በሚለው የረዳቱ ትእዛዝ መርጦ ለማርያም መድረሳችንን አወኩኝ።
አለቃ ፈንቴ ተቀብለው ወደ ቤታቸው ወሰዱኝና ጊዜ ደራሹ ላይ ያሰናዱትን የኮቸሮ ግሽር አብረን በላን።
“ቀትሩ ይለፍና አንድ ቦታ አስጎበኝሃለሁ” አሉና ስብሐት አድርሰው ገበታውን ካነሱ በኋላ ያመጣሁትን አረቄ በፍንጃል ቀዱልኝ።
አልጠጣም ብላቸው “ይጎንጥሀል” አሉኝ።
እንግዳ ነገር ሆኖብኝ እንዲያብራሩልኝ ጠየኳቸው።
“ማንኛውም የሚበላና የሚጠጣ ነገር ሁሉ ከሸተተህ ብትወድም ባትወድም መቅመስ አለብህ፤ አለበለዚያ ባንተ ተመስሎ ለመቋደስ የሚቅበዘበዘው ቁሪ ሲቀርበት ይደቃሀል” ብለው ሲያስረዱኝ በድንጋጤ የቀዱልኝን አረቄ በአንድ ትንፋሽ ጨለጥሁት።
“ፉት ካልከው ከዚህም በኋላ እንድትጠጣ አትገደድም፤ ያን ያህል ቢሆንም የእህል ደም ነው አጣጥመው” አሉና አሰር ውሃ በሽክና አስያዙኝ።
እሳቸው አረቄያቸውን እኔ ጠላዬን እየተጎነጨን ስራ እንዴት ነው? ስል የጨዋታችንን ሀረግ መዘዝኩ።
“ምቀኛ እስካለ ድረስ በሽበሽ ነው ስራ አንፈታም” አሉ እየፈገጉ።
በጥያቄ አስተያየት ተመለከትኳቸው፤ የጀመሩትን አረቄ ከልብሰው ሌላ ቀዱና “ምን መሰለህ ገብረ ኪዳን” አሉ እየተመቻቹ።
“ይሄ ህዝብ እገሌ በትምህርት ቀደመኝ፣ እንትና በሀብት በለጠኝ፣ ማንትስ ውርስ ሊካፈለኝ ነውና ከቻልክ ሞቱን ካልሆነ ጉዳቱን አሳየኝ ይልሃል እንጂ ዝናብ ቀረብን፣ እህላችንን አውሬና ተባይ ፈጀብን ያዝልን አይልህም።
ባለው ነገር ፈጣሪውን አመስግኖ እንደመኖር ባንዱ ጸጋ ሌላው ደስ ሊለው ሲገባ ያንተ ማግኘት ያበግነውና በደረቅ ሌሊት ደጃፍህ ላይ የአይጥ አንጀት፣ የተቆረጠ የዶሮ አንገት ይጥልብሃል።
ጠዋት በርህን ስትከፍት ታየዋለህ፤ ከድንጋጤ ጋር ጋኔን ተደርቦ ይደቃህና ለከፋ ስቃይ ይዳርግሃል።
ከቻለም እድሜህን ያሳጥረዋል።
የኋላውን አስበን እኛ እንኳን እምቢ ብንልም ምቀኛ ሁሉ አሞሌ ጨው እያላሰ አዲስ ከብት እንደሚያላምድ ረብጣ ገንዘብ እያሳየ እንክ እንክ ይለናል።
አንዴ ምን ሆነ መሰለህ … ድጋሙን ገና እንደለመድኩት ባንተ እድሜ ያለ አንድ ወጣት ላይ ስራዬን ፈተንኩት፤ ቃሌ አይስትም ሄዶ ቀጭ ነው።
ይህ ወጣት መስተፋቅር እንድሰራለት ወተወተኝ፤ እግዚአብሔር አልተለየኝም ነበርና የፈተንኩትን ስራዬን እንዳልሰጠው ፈራሁ፤ እንዳልተወው ደግሞ ገበያ ሊዘጋብኝ ሆነ።
ቢጨንቀኝ በብራናው ላይ ብትወድህ ባትወድህ እኔ ምን አገባኝ ብዬ ከተብኩና ባንገቱ እንዲያጠልቀው አዝዤ ሸኘሁት።
አየህ ምቀኛ ሁሉ የሚደረግለትንም ሆነ የሚደረግበትን አያውቅም።
ደመ ነፍሱን ይነዳል ብለው ረዥም ንግግራቸውን እየቋጩ እጃቸውን ወደ መለኪያቸው ሰደዱ።
እኔም ሽክናዬን እየሞላሁ ስፈራ ስቸር አለቃ ፈቃድዎ ከሆነ ያለዎትን ጥበብ ቢያወርሱኝ? ስል ተማጸንኳቸው።
ምን ያደርግልሃል? አሉ የጋቢያቸውን ጎልፋ እያፍተለተሉ።
አሳማኝ ያልኩትን ምክንያት ሁሉ ደረደርኩ።
ስለ ኢትዮጵያ ክፉ የሚያወሩ ሰዎችን ልሳናቸውን እዘጋዋለሁ፣ በመሣሪያና በሠራዊት ብዛት የሚታበዩትን የትኛውንም መንግሥታት በቃላት ብቻ አንኮታኩታቸዋለሁ፣ ሆደ ሰፊው ህዝቤ ላይ እጁን የሚያነሳውን ምቀኛ ሁሉ በረዶ አዘንብበታለሁ፣ የዓባይን ውሀሃ አቁሜ የግብጻውያንን ትዕቢት አስተነፍሰዋለሁ፣ ብሔርን ከብሔር እያጋጩ ጥቅማቸውን የሚያጋብሱና ስማቸውን በቅጡ የማይጽፉ ነገር ግን በፎርጅድ የትምህርት ካርድ ስልጣን ጨብጠው የሀገርን አንጡር ሀብት የሚመጠምጡ ሰዎችን ከኢዮብ በባሰ ቁስል አነዳቸዋለሁ።
ብቻ እርስዎ ያስተምሩኝ ስል ዳግም ለመንኳቸው።
አበክረው ከንፈር መጠጡ።
የሚሰጡኝ መልስ ታውቆኝ ፊታቸውን ላለማየት አቀረቀርኩ።
“አንደኛ ጴጥሮስ ምእራፍ 2÷21 መከራን ስትቀበሉ ታገሱ የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌነት ትቶላችሁ መከራን ተቀብሏል በማለት እንደተናገረው ሀገርህ በሰማይ ከሆነ የምድርን ተድላ ለምን ትሻለህ? በከንቱ የዓለም ፖለቲካ ነፍስህን ከምታቆረፍዳት የማያልፈውን የክርስቶስን ቃል ብትመግባት አይበጅህም? ደግሞም ያጋጠመህን ችግር የምትሻገረው በስሜት ሳይሆን በሰከነ አስተሳሰብ ስትራመድ ነው” ብለው ዝም አሉ።
እሽም እምቢም ባይሉ ከሃሳባቸው አይሆንም ማለታቸውን ተገንዝቤያለሁ።
ማስተማሩን አያስተምሩኝ እናንተስ ብትሆኑ ባላችሁ እውቀት ሀገራችሁን የመጠበቅ ግዴታ የለባችሁም? ስል የብሽቀት ጥያቄ ሰነዘርኩላቸው።
“ገብረ ኪዳን አስተውል … የግእዝ ቋንቋን ያጠለሸው ለክፋት አገልግሎት ብቻ ማዋላችን ነበር፤ አሁን ግን ትውልዱን ከዚህ አስተሳሰብ በማውጣት ሁለንተናዊ ጥበባችንን መያዙን ልንገልጥለት ይገባል።
በብራና የተሰነዱ ሀገረሰብ መድኃኒቶችን በሳይንሱ እየታገዝን ጥቅም ላይ እናውላቸዋለን፣ የየደብራቱና የየገዳማቱ ታሪክ እየተጠና ለህዝቡ እንዲደርስ እናደርጋለን።
አንተም የተጠራኸው ለዚሁ አላማ ነው” ብለው የያዙትን መጠጥ አገባደው ቆሙ።
አስቤው የማላውቀውና ያልጠበቅሁት ኃላፊነት በመሆኑ እንደ እርጥብ ቆዳ ከበደኝ።
አለቃ ምን መሰለዎት ብዬ ላስረዳቸው ስንተባተብ ስሜን ጠርተው አናጠቡኝ።
“ገብረ ኪዳን አንተ የምታውቀኝ ሥር ስምስ፣ ቅጠል ስበጥስ ነበር፤ ዛሬ ላይ አዲስ ማንነት ለብሻለሁ።
አባ ኪዳነ ማርያም ብለህ ጥራኝ” አሉና መስቀላቸውን አሳለሙኝ።
የባሰውን እንቆቅልሽ ሆኑብኝ።
“መዘንጋት የሌለብህ ነገር ቢኖር ነብዩ ህዝቄል የፈረሰችውን ያባቱን ርስት እየሩሳሌም ከተማን የገነባት በሃያ አምስት ዓመቱ ነው።
ወጣትነትህን ለሀገርህና ለሃይማኖትህ ድከምበት፤ የማስጎበኝህም ቦታ ካንተ ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው” ሲሉኝ ደግሞ ምን? አልኳቸው፤ ግራ መጋባቴ እያየለ።
“ሄደን ብናየው አይሻልም?” አሉና እየመሩኝ ወጡ።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም