አበረታች ለውጦች የታዩበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወርቅ ምርት

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወርቅ ማዕድን ሀብትና ምርት ከሚታወቁ የአገሪቷ ክልሎች ተጠቃሹ ነው። ክልሉ በወርቅ ክምችቱና ምርቱ የታወቀ ይሁን እንጂ፣ የወርቅ ሀብቱን በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ማዋል ግን አልተቻለም። ከኋላቀር የወርቅ አመራራት ጋር በተያያዘ የወርቅ ማዕድኑ በሚፈለገው መጠን እንዲለማ አልተደረገም፤ በሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ ሳቢያ የሚመረተው ወርቅም ቢሆን ለብሔራዊ ባንክ እንዲገባ እየተደረገ አይደለም። በዚህ የተነሳም አልሚዎቹም፣ ክልሉም አገሪቷም የሚገባቸውን ጥቅም ማግኘት ስላለመቻላቸው ሁሌም ይገለጻል።

ይህ በወርቅ ላይ ሲስተዋል የቆየው ሕገወጥነትና የኮንትሮባንድ ንግድ በዚህ ክልል ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ይታወቃል። እንደ ሀገር ያለ ችግር እንደ መሆኑ ሀገሪቱ ከወርቅ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝና ተጠቃሚ እንዳትሆን ተደርጋለች።

መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ለውጥ ሊያመጡ የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች ሲሰራ ቆይቷል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባትና ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ይጠቀሳሉ።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በማዕድናት ምርታማነት በተለይ በወርቅ ምርት ምርታማነትና አቅርቦት ላይ ለውጦች እያመጣ ነው። በአነስተኛ ደረጃ የሚመረተውን የማዕድን ምርት በከፍተኛ መጠን እያሳደገው ይገኛል። በተለይም የወርቅ ምርታማነትና ለብሔራዊ ባንክ እየቀረበ ያለበት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ማደግ ችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ በኋላ በወርቅ ምርት ኤክስፖርት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል። በውጭ ምንዛሬ ማስገኘት በኩል በተለይ ቡናና ወርቅ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።

በሩብ ዓመቱ ለውጭ ገበያ የቀረበው ወርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና በላይ ትልቁን ድርሻ የያዘበት ሁኔታ መፈጠሩም ተጠቅሷል። ለብሔራዊ ባንክ እየቀረበ ካለው ወርቅ ምን ያህል ወርቅ ሲዘረፍ እንደ ነበረ መረዳት እንደሚቻል ገልጸው፣ አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ገደማ ወርቅ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል።

የወርቅ ምርት ሲዘርፋባቸው ከቆዩ አካባቢዎች ጥቂቶቹ ምላሽ እያመጡ ነው። ገና ብዙ ለውጥ ይመጣል። የምንበዘበዝባቸው ብዙ ቀዳዳዎች አሉ። ከእነሱ ውስጥ አንዱ የሆነው ወርቅ መልስ እየሰጠ ይገኛል። ወርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ትልቁን ድርሻ ይዟል ሲሉ አብራርተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወርቅ ምርት ላይ ለውጥ እንዲታይ ማድረግ መጀመሩን የክልሉ ማዕድን ቢሮ አመልክቷል፤ የክልሉ የማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ሞርካ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ ምርት እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ባለፈው በጀት ዓመት ከክልሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን 274 ኪሎ ግራም ነበር። በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ባንኩ የገባው ግን 548 ኪሎ ግራም ወርቅ ነው።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ በርካታ ሥራዎች ለመስራት ታቅደው እየተሰሩ ናቸው። ይህን ተከትሎም በወርቅ ምርት ከባለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ አበረታች ለውጥ ታይቷል።

በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያ ሩብ ዓመት 413 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ታቅዶ ነው 548 ኪሎ ግራም ወርቅ ማስገባት የተቻለው። ይህም አፈጻጸሙን ከእቅዱ በላይ እንዲሆን አድርጎታል። አፈጻጸሙ ከእቅዱ በላይ ብቻ ሳይሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅትም በእጅጉ የላቀ ወርቅ ማስገባት የተቻለበት ነው። ባለፈው በጀት ዓመት ከተገኘው 274 ኪሎ ግራም ወርቅ አኳያም ሲታይ የሩብ ዓመቱ አፈጻጸም በእጥፍ ብልጫ ያለው ነው።

በክልሉ የወርቅ ምርት ላይ ለውጥ ለመምጣቱ ዋንኛው ምክንያት ተደርገው ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው የሚሉት አቶ አድማሱ፤ ማሻሻያው ከተደረገ ጀምሮ በክልሉ የወርቅ ምርት እየጨመረ መጥቷል ይላሉ። በዚህም ምክንያት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠንም እየጨመረ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይ ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ አዘዋዋሪዎች ወርቅ በሚገዛበት ዋጋ ላይ ማስተካከያ ካደረገ በኋላ የወርቅ ምርት በሕጋዊ መንገድ ወደ ብሔራዊ ባንክ እየገባ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የወርቅ ምርትና ግብይት ላይ የሚፈጸመውን ሕገወጥ እና የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱም ሌላው ለወርቅ ምርት መጨመር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ስምንት ወረዳዎች የወርቅ ማዕድን ክምችት እንዳላቸው እንደሚታወቁ ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል በአሶሳ ዞን፣ ከማሼ እና በመተከል ዞን ባሉ ወረዳዎች በወርቅ አምራችነት እንደሚ ጠቀሱ ይ ገልጻሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በክልሉ 421 ባሕላዊና ልዩ አነስተኛ ማኅበራት ወርቅ የማም ረትና የማዘዋወር ፍቃድ ወስደዋል። በክልሉ በሩብ ዓመቱ ከክረምት ወቅትና በአጎራባች አካባቢዎች ካለው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ያቀዱትን ያህል ያልፈጹሙ አምራቾች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በከፍተኛ ደረጃ ወርቅ የማምረት ፍቃድ ያለው ሲሆን፣ ይህ አምራች በሩብ ዓመቱ ለማምረት ካቀደው 13 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት፣ ሁለት ኪሎ ግራም ብቻ ማምረቱን ጠቅሰዋል።

ይህን ከፍተኛ ደረጃ ወርቅ አምራች በሩብ ዓመቱ የነበረው የዝናቡ ወቅት በሚፈለገው መጠን ወደ ማምረት ስራ እንዳይገባ ያደረገው መሆኑን ተከትሎ እቅዱን ማሳካት እንዳልቻለ የቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል። በቀሪዎቹ ጊዜያት ወደ ምርት በመግባት የተሻለ ለማምረት እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። በሩብ ዓመቱ አብዛኛው የወርቅ ምርት የተገኘው ከባሕላዊና ከልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ማኅበራት እንደ ሆነ አመላክተዋል።

በተለይ ወርቅ ለሕገወጥነት የተጋለጠ በመሆኑ በሕገወጦች ሲፈተን ቆይቷል ያሉት ኃላፊው፣ ቀደም ሲል የነበረው የወርቅ መሸጫ ዋጋ ሰፊ ልዩነት ሕገወጥነት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኖ እንደነበር ጠቅሰዋል። አሁን ብሔራዊ ባንክ ባደረገው የዋጋ ማስተካከያ የተነሳ ዋጋው መንግሥት እየተቆጣጠረው ነው ለማለት የሚያስችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ። እርምጃው የወርቅ ምርት በአግባቡ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ውጤቶች እንዲመዘገቡ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አድማሱ በክልሉ ወርቅ ለማምረትም ሆነ ለማዘዋወር ፍቃድ የሚወስዱ አካላት ሊከተሉ የሚገባቸውን አሰራር እንዳለም አስታውቀዋል። እነዚህን አሰራሮች ተግባራዊ ማድረግ ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ይጠቅሳሉ። በተለይ የአካባቢ ጥበቃ መመሪያዎች ጠብቆ በመስራት ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ ተናግረው፣ ለወርቅ ፍለጋ ተብለው የሚቆፈሩ ቦታዎችን አፈር ሳይመልሱ መተው ትልቅ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።

የማዕድን ቁፋሮ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ሊፈጠር በሚችለው ጥልቀት የተነሳ የላይኛዋ፣ የመካከለኛው እንዲሁም የታችኛው የአፈር ክፍሎች መንካታቸው እንደማይቀር ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም በአካባቢና በሰው ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አመላክተዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም በተለያዩ ጊዜያት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው አስረድተዋል።

ከወርቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላኛው ተግዳሮት የወርቅ አምራቾችም ሆኑ አዘዋዋሪዎች የሚያደርጉት ሕገወጥ የወርቅ ዝውውር መሆኑን አመልክተው፣ በዚህ የተነሳም ምርታቸውን በሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ በማስገባት በኩል ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ይጠቁማሉ። እነዚህን ክፍተቶች በመድፈን ችግሮችን ለመቅረፍም በክልሉ ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህን ሥራዎች በመገምገም፣ ቁጥጥርና ክትትል የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መደረጉን ይገልጻሉ።

በተለይ በዘርፉ በተሰማሩ ሕገወጦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ በተለይ ወርቅ ከመቆፈር አንስቶ በሚካሄዱ ሥራዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። ወርቁ በትክክል ተመርቶና በአግባቡ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል። የባሕላዊና ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ወርቅ ከመቆፈር ጀምሮ እስከ ማምረት መከተል ያለባቸውን አሰራር አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን በመስራት መግባባት ላይ እየተደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፉት ይጥል ከነበረው ዝናብ ጋር በተያያዘ ለባሕላዊና ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ወርቅ የሚያወጡበት ቦታ ድረስ በመሄድ ድጋፍ ለማድረግ ሳይቻል መቆየቱን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ጊዜያት ሙያዊ ድጋፎችና የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች በመስጠት ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል። በተለይ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት ከማዕድን ዘርፉ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ በየዓመቱ የማዕድን አለኝታ ቦታ እና የማዕድን ልየታ ጥናት እንደሚካሄድ የቢሮ ኃላፊው ጠቁመው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ይህንኑ ለማከናወን ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ክልሉ ከወርቅ በተጨማሪ ሌሎች ብዙ አይነት የማዕድናት ሀብቶች እንዳሉና በሁሉም ማዕድናት ላይ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በተለይ የድንጋይ ከሰልና እምነበረድ ለማምረት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ የገቡ አምራቾች እንዳሉም ገልጸዋል ።

እሳቸው አንዳብራሩት፤ የድንጋይ ከሰል ለማምረት 159 አምራቾች የምርት እና የምርመራ ፍቃድ ወስደዋል። በጸጥታና ከአለመረጋጋት ጋር በተያያዘ አሁን ሥራ ላይ ያሉት ውስን አምራቾች ናቸው። እምነ በረድ ላይም እንዲሁ 258 አምራቾች የምርትና የምርመራ ፍቃድ ወስደዋል፤ ከእነዚህም መካከል በሥራ ላይ ያሉት ውስን ናቸው። በቀጣይም ወደ ሥራ ያልገቡት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ይሰራል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 15ሺ ቶን የድንጋይ ከሰል ለማምረት ታቅዶ፤ ከ27ሺ ቶን በላይ ማምረት ተችሏል። በእምነበረድም በሩብ ዓመቱ 600 ሜትር ኪዩብ ለማምረት ታቅዶ ፤ 459 በላይ ሜትር ኪዩብ ተመርቷል።

በሩብ ዓመቱ የተፈለገውን ያህል ለመስራት የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመው እንደነበር ጠቅሰው፤ በአጎራባች ክልሎች አካባቢዎች ባለው የጸጥታና የአለመረጋገት ችግሮች ምክንያት የመንገድ መዘጋቱ እና የመሳሰሉ ችግሮች ማጋጠማቸው በማዕድን ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት የሚፈልጉትን ግብዓት እንዳያስመጡ ተግዳሮት እንደሆነባቸው አመላክተዋል። እንዲያም ሆኖ የተሻሉ ሥራዎች መስራታቸውን ነው ኃላፊው የጠቀሱት።

የማዕድን ዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ የቆየው የጸጥታና አለመረጋገት ችግር አሁን እየተፈታ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም በዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዲሰራ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አስገንዘበዋል።

የማዕድን ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥር ይታወቃል የሚሉት ኃላፊው፤ በክልሉ በሩብ ዓመቱ ከታቀደው አንጻር 80 በመቶ ለሚሆኑ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደተቻለ አመላክተዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You