ሀገራችን የዓባይ ወንዝ ውሃን በኃላፊነት እና በፍትሐዊነት ለመጠቀም የሚያስችል አዲስ የትብብር ማሕቀፍ ለመፍጠር ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሰፋፊ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች። በብዙ ውጣ ውረድ እና ፈተናዎች የተሞላው ጥረቷ አሁን ላይ ፍሬ አፍርቶ በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ተደርሷል።
ሀገራችን ለናይል ወንዝ 80 ከመቶ የሚደርሰውን የውሃ መጠን ከማበርከቷ አኳያ፤ ከወንዙ ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በቀደሙት ዘመናት ሆነ አሁን ላይ የሚነሱ አጀንዳዎች በብዙ መልኩ ይመለከቷታል ።በተለይም የወንዙን ውሃ በፍትሐዊነት ለማልማት ያላትን መሻት ለመተግበር በምታደርገው ጥረት ውስጥ ለጉዳዩ የምትሰጠው ትኩረት ከፍ ያለ ነው።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ በሀገራትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረሱ ስምምነቶችም ሆኑ፤ ስምምነቶቹ የሚገዙለት አስተሳሰብ ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገ እና ለዚሁ የተገዛ ነው። በእነዚህ ወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ የሚነሱ የትኛውም አይነት ጥያቄዎችም ተገቢውን ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት ይህንኑ እውነታ ታሳቢ ባደረገ መንገድ ነው።
በተለይም ፍትሐዊነት ዓለም አቀፍ መርህ በሆነበት በዚህ ዘመን፤ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች፤ ዘላቂ እና ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ምላሽ ማግኘት የሚችሉት ዘመኑን በሚዋጀው የፍትሐዊነት እሳቤ ሲገሩ ብቻ ነው።
ከዚህ ውጪ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የወለዳቸው ፣ በአንድም ይሁን በሌላ የቅኝ ገዥዎችን ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ለማስፈጸም ተግባራዊ የሆኑ ፣ የሀብቱ ባለቤት የሆኑ ሕዝቦች ውሳኔ የሌለባቸውን ውሎች ስምምነቶችን ታምኖ በእነርሱ ላይ ቆሞ ለመራመድ መሞከር ከዘመኑ ጋር በተቃርኖ ከማቆም ባለፈ፤ የቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብ ሰለባ መሆን ጭምር ነው።
የናይል ወንዝ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት ነው። ከአንተ በላይ ለእኔ ያስፈልገኛል፤ ከአንተ በላይ ለኔ የህልውናዬ መሰረት ነው … ወዘተ የሚሉ፤ ከዘመናት በፊት የነበረ ማኅበረሰብ የፈጠራቸው ስጋቶች፤ ባለንበት የሰለጠነ ዓለም ትርጉም የሚሰጥ የአደባባይ መደራደሪያ ሊሆን አይችልም።
የናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀም የተፋሰሱ ሀገራት አሁናዊ ትልቅ አጀንዳ ነው። አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች ካሉበት ድህነት እና ኋላቀርነት በልማት ለመውጣት ለሚያደርጓቸው ጥረቶች የወንዙ ውሃ አንዱ የመልማት አቅማቸው ነው። ይህን ተፈጥሯዊ አቅማቸውን በፍትሐዊነት መጠቀም የማንንም ይሁንታ የማይጠብቅ መብታቸው ነው።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሀገራችን አነሳሽነት ተግባራዊ የሆነው የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍ ዋነኛ ዓላማም ይሄው ነበር፤ የወንዙን ውሃ በፍትሐዊነት እና በኃላፊነት መጠቀም የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ መድረስ፤ የቅኝ ገዥዎች ጥላ ያጠላባቸውን የቀደሙ ውሎች ዘመኑን በሚመጥን ስምምነት መለወጥ ዋነኛ ግቦቹ ነበሩ።
እንዲህ አይነት ጥረቶች ባለንበት ዘመን እና ዘመኑ ከሚገዛበት አስተሳሰባዊ ልቀት አኳያ፤ ብዙ የማያለፉ ፤ በቀላሉ ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢታመንም ፤ከተፋሰሱ የታችኛው ሀገራት፤ በተለይም በግብጽ በኩል ካለው የአስተሳሰብ ዝንፈት ብዙ ፈተናዎችን ለማለፍ ተገድዷል።
የግብጽ መንግሥት ገና ከጅምሩ በአንድ በኩል የተፋሰሱ ሀገራት በወንዙ ፍትሐዊ አጠቃቀም ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ እንዳይደርሱ፤ ከዚያም አልፎ የፍትሐዊነት እሳቤ የተፋሰሱ ሀገራት አጀንዳ እንዳይሆን ረጅም ርቀት ተጉዟል።
በቅኝ ገዥዎች የተቀመጡ ኢፍትሀዊ ውሎች/ስምምነቶችን ለማስቀጠል ፣ የተለያዩ ትርክቶችን በመፍጠር የገዛ ሕዝቡን ጨምሮ ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያለ እረፍት ሠርቷል ። በተፋሰሱ ሀገራት ሉዓላዊ መብት ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠርም በስፋት ተንቀሳቅሷል።
አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በግብጽ በኩል የተፈጠሩ ጫናዎችን እና የመከፋፈል ሴራዎችን በጽናት ተሻግረው ፣ የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍን ፈርመው በሀገራቸው ደረጃ የሕጋቸው አካል አድርገዋል። በዚህም ለፍትሐዊነት ያላቸውን የጸና አቋም በአደባባይ አሳውቀዋል።
ሀገራችን የላይኛው የተፋሰሱ ሀገር ብትሆንም ጉዳዩ ፍትሐዊ እንዲሆን ለማድረግ እና ማሕቀፉ ስኬታማ እንዲሆን ከሌሎቹ ሀገራት ጋር በጋራ ስትሠራ ቆይታለች። ተሳክቶላትም ማሕቀፉ አስገዳጅ ሕግ ወደሆነበት ታሪካዊ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ውጤቱም እንደ ሀገር ያሳካነው እና የምንኮራበት ትልቅ ስኬት ነው።
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም