የቆዳውን ዘርፍ ተግዳሮቶች በመፍታት ምርትና ጥራትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው

. ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ስምንት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ተገኘ

አዲስ አበባ፦ የቆዳውን ዘርፍ ተግዳሮቶች በመፍታት የቆዳ ምርትና እና ጥራትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አስታወቀ። ባለፉት አራት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ስምንት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ገለጸ፡፡

የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ መሐመድ ሁሴን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ማዕከሉ በኩል በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ማነቆዎቹን ለመፍታት በየፋብሪካዎቹ እና በየኩባንያዎቹ ደረጃ ያሉትን ችግሮች መሰረት አድርጎ ለመፍታት እየሰራ ነው፡፡ ለውጤታማነቱም የዘርፉ ባለድርሻዎች ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል።

በኢንዱስትሪዎች ዘንድ የበሬ፣ የበግና የመሳሰሉት ቆዳዎች ፍላጎት እንዳለ ጠቅሰው፣ የቆዳ ሰብሳቢዎች ከገበያ መውጣት ችግር ይህን ፍላጎት መመለስ እንዳላስቻለ ተናግረዋል፡፡

በአቅራቢዎች እና ተቀባዮች መካከል ያለው ግብይት ግልፅነት የጎደለው መሆኑንም አመልክተው፤ በዘርፉ እሴት የማይጨምሩ ተዋናዮች መበራከትና የጨው ዋጋ መወደድ የቆዳ ዘርፉ ሌሎች ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በቅርቡ ስራ ላይ የዋለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በአምራች ኢንዱስትሪው ሲጠየቀው የኖረ መሆኑን አስታውቀው፣ ተቀዛቅዞ የቆየውን የቆዳ ዘርፍ እንደሚያነቃቃ አስታውቀዋል። ማሻሻያው የቆዳና ሌጦ አምራች ፋብሪካዎች ኬሚካል ከውጭ ሲያስመጡ ለሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱን የሚያሻሽል በመሆኑና አምራቹ ወደ ውጭ በሚልካቸው ምርቶች ከሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶ በቀጥታ እንዲጠቀምበት፣ የተቀረውን 50 በመቶ ደግሞ በራሱ አካውንት አስቀምጦ በፈለገ ጊዜ እንዲጠቀምበት የሚያስችል አሰራር የተፈጠረበት ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ለሚያስመጡት ግብአት እንዲያውሉት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል ግብዓት ለማምጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር እንደነበር አስታውሰው፤ የኬሚካል ግብዓት እጥረት ባለበት ሁኔታ ለማምረት አዳጋች እንደነበር አስታውቀዋል። ማሻሻያው የግብዓት አቅርቦቱን ችግር በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀርፍ ይሆናል ነው ያሉት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሐምሌ ወር 2016 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2017 ዓ.ም ባሉት አራት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቆዳና የቆዳ ውጤት ስምንት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘቱንም ተወካዩ አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ውስጥ ወደ አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተገኘው የቆዳ ፋብሪካዎች ወደ ውጭ ከላኩት ምርት ነው። ዜሮ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ የቆዳ ጓንት አምራቾች ከላኩት ምርት የተገኘ ነው። ዜሮ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የቦርሳ፣ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከቆዳ ተረፈ ምርት እሴት በመጨመር በመላክ የተገኘ ነው።

ይህ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከሚጠበቀው በታች መሆኑን ጠቅሰው፣ በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት እንዲሁም የቆዳ ምርቱን እና ጥራቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ መሀመድ የከፊልና ያለቀለት የቆዳ ውጤት የኢትዮጵያ የገበያ መዳረሻ በአብዛኛው ቻይና መሆኗን ጠቁመው፤ ወደ ቻይና የሚላከው ምርት በኮቪድ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን አስታውሰዋል። ወደ ቻይና የሚላከው ምርት አሁን ወደ ነበረበት የመመለስ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርቶችን ለአሜሪካ በመሸጥ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ኩባንያዎች በውስጣዊ ምክንያት ማምረት አቁመው እንደነበር አስታውሰው፤ ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል ሁኣጂያን የጫማ ፋብሪካ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው የቆዳ ውጤቶችን በከፍተኛ ደረጃ ወደ አሜሪካ ይልክ እንደነበረ አስታውሰው፤ እንደገና ወደ ማምረት ስራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡ የናሙና ምርት ወደ አፍሪካ ሀገራትና ሌሎች ሀገራት መላከ መጀመሩንም አመላክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም

Recommended For You