የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ክለቦች በርካቶቹ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ከተማ እንደማድረጋቸው ከተማዋ የበርካታ አትሌቶች መዳረሻ ናት፡፡ ሀገርን በኦሊምፒክ እና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረኮች በድል ያስጠሩት እንደ አትሌት መሠረት ደፋር፣ ሚሊዮን ወልዴና ሌሎችም ጀግና አትሌቶች የከተማዋ ፍሬዎች ናቸው።ዛሬም ቢሆን የአትሌቲክስ ስፖርት ፍላጎትና አቅም ያላቸው በርካታ ታዳጊና ወጣቶች የነገን ስኬት አልመው በዝችው የአፍሪካ መዲና ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለልምምድም ሆነ ለውድድር ብቁ የሆነ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ማግኘት ለነዚህ አትሌቶች ፈተና ነው፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እጥረት ሀገራዊ ችግር ቢሆንም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ደግሞ ካለው ፍላጎት አንፃር የጎላ ሆኖ ይታያል፡፡ በአንጻራዊነት ከተማ አስተዳደሩ ችግሮቹን ለመቅረፍ በየቦታው 3 በ 1 ሜዳዎችን እየገነባ ቢሆንም ካለው የታዳጊዎችና ወጣቶች ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም፡፡ ከዚህ ባለፈ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁነቶችን የምታስተናግደው አዲስ አበባ ሀገር አቀፍም ሆነ አህጉር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማስተናገድ ረገድ እንቅስቃሴዋ ደካማ የሚባል ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ በታወቀችበት የአትሌቲክስ ስፖርት ደግሞ ለልምምድም ሆነ ለውድድር ምቹ የሆኑ ጥርጊያ ሜዳዎች፣ የአሸዋ እና ደረጃቸውን የጠበቁ መሞች እንዲሁም ለሜዳ ተግባራት ስፖርቶች የሚሆኑ ሥፍራዎችን ማግኘት እየከበደ ነው፡፡ በፕሮጀክቶች የታቀፉና በየክለቡ የሚገኙ አትሌቶች በስፖርት አዘውታሪዎች በተጣበበው ጃንሜዳ ልምምድ ማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ ወደ መኪና መንገዶች ወጥተው አስፓልት ላይ በመሥራት ለአደጋ እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሮችን በአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት እና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለውድድር ብቁ ባለመሆን የተነሳ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እያካሄደ ይገኛል፡፡ የአካዳሚው መም ደግሞ በብቸኝነት መሰል ኩነቶችን እያስተናገደ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መፍትሄ ለማበጀት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የከተማው ፌዴሬሽን በተለይም በታዳጊ አትሌቶች ልማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም ውድድርን በማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ወሳኝ የሆነው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ችግር ለመቅረፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ከሰሞኑ አዘጋጅቷል። የገቢ ማሰባሰቢያው የሚውለውም ለመገንባት ለታቀዱት ሶስት ማዘውተሪያዎች ሲሆን፤ በጃንሜዳ ስፖርት ማዕከል ለውድድር ብቁ የሆነ የአሸዋ መም ቀዳሚው ነው፡፡ ባለ ስምንት መም የሆነው የአሸዋ መሮጫ ውድድሮችን በበቂ ሁኔታ ለማካሄድ ታስቦ ዲዛይኑ ሲዘጋጅም እስከ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡
ቀሪዎቹ የልምምድ ሥፍራዎች ደግሞ በጃንሜዳ የሚገነባ ሁለት ኪሎ ሜትር የአሸዋ ሜዳ እንዲሁም ለታዳጊ ፕሮጀክት ጥቅም እንዲሰጥ የታቀደው በወንድይራድ ትምህር ቤት ጊቢ ውስጥ የሚሠራ ነው፡፡ ለዚህም መቀመጫቸውን በከተማዋ ያደረጉ የአትሌቲክስ ክለቦች፣ ማናጀሮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በመድረኩ ላይ ተገኝተው የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡ በጉልበት እና በሙያ ለማገዝ ቁርጠኝነታቸውን ከገለጹት ባለፈም 3 ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቷል፡፡
በመድረኩ ከተገኙት መካከል ጀግናውን አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ በርካቶችን ያፈራው አሠልጣኝ ጌታመሳይ ሞላ አንዱ ነው፡፡ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ችግር በተለይ በስፖርቱ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ እገዛ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በአንድ መም ላይ በርካታ አትሌቶች እየተጋፉ እየሠሩ ስፖርቱ ላይ ተጽእኖ እያደረሰ በመሆኑ ከፌዴሬሽኑ ጎን በመቆም ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም አሳውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርትን በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የክልልና የከተማ አስተዳደሮች ፌዴሬሽኖችን ይደግፋል፡፡ ድጋፉ በሙያ በገንዘብና በቁሳቁስ እንደመሆኑም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለተነሳበት የአትሌቲክስ ዓላማ አጋር በመሆን የድርሻውን በገንዘብ ለማበርከት ቃል ገብቷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፋሲሊቲ እና ማህበራት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ በቀለ፤ የሚገነባው የማዘውተሪያ ሥፍራ ለከተማዋ ብቻም ሳይሆን አትሌቶች ላሉባቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጅት ሊያደርጉ የሚችሉበትና አሁን ላይ ላለው እጥረት ማስተንፈሻ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ክለቦችና ማናጀሮችንም ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ሌሎችም ይህንኑ አርዓያ መከተል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
የከተማዋ ፌዴሬሽን በተተኪዎች እና ወሳኝ በሆነው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ላይ አተኩሮ እየሠራ መሆኑን የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ወይዘሮ እታፈራሁ ገብሬ ተናግረዋል፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲሁም የከተማዋ ፌዴሬሽን ያስጀመራቸው የታዳጊ ፕሮጀክቶች በየክፍለ ከተማው አሉ፡፡ ይሁንና ለልምምድም ሆነ ለውድድር የሚሆኑ በቂ የማዘውተሪያ ሥፍራ የለም፡፡ ችግሩ የከተማው ብቻም ሳይሆን ሀገር አቀፍ ቢሆንም ሁሉም የአትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት የተቻላቸውን ድጋፍ በማድረግ መፍትሄ ሊበጅ ይገባል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም