በዕድሜ ማምሻ ላይ…

ወደምገባው ማዕከል ለመግባት ጉዞ ከጀመሩት በርካቶች መሀል የአንዱ አዛውንት ሁኔታ ዓይን ይስባል፡፡ ዕድሜ የሰበረውን አንገታቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ውስጥ ያማትራሉ፡፡ በእጃቸው የያዙትን የምሳ ዕቃ እንዳጠበቁ ነው፡፡ በጥልቅ ሃሳብ መናዋዛቸው ያስታውቃል፡፡ በልቦናቸው ምን እንዳለ ባላውቅም ውስጣቸው በትካዜ ስለመያዙ ነጋሪ አላሻኝም፡፡

አስተውሎ ላያቸው ገጽታቸው በእጅጉ ያሳዝናል። የዕድሜ ጅረት ያለፈበት አካላቸው የትናንቱን ውጣውረድ እየመሰከረ ነው፡፡ በአዛውንቱ ውስጠት ብዙ ድካም መኖሩ ያስታውቃል፡፡ የእስከዛሬው ህይወታቸው ስለማንነታቸው ይመሰክራል፡፡

እሳቸው እስካሁን በበዛ ችግር ተንገላተዋል፡፡ በመከራ ተፈትነዋል፡፡ ኑሯቸውን ላስተዋለው አሁንም ዛሬም ህይወታቸው ከዚህ እውነት የራቀ አይደለም። ከዕድሜ፣ ከኑሮና ሕይወት ጋር ትግል ገጥመዋል፡፡ በሕይወት ለመዝለቅ የሁል ጊዜ ትግላቸው ቀጥሏል፡፡ ሁሌም ይታትራሉ፣ ላለመውደቅ ይታገላሉ፡፡

አሁን ላይ በእጃቸው የጨበጡት ሰሀን ደግሞ ለእሳቸው ውስጡ እንጀራ ብቻ አይደለም፡፡ ውስጡ ዕልፍ ሚስጥር የተቋጠረ ታሪክ ፣የሚነገር ሕይወትን ይዟል፡፡ ..ገመቹ አመንሲሳ

በአቃቂ ሰፊ መስክ ላይ እሱን ከመሰሉ ህጻናት ጋር ሲዘል፣ ሲጫወት፣ አድጓል፡፡ እረኝነት ለእሱ የቀደመ ሕይወቱ ነው፡፡ ዕድሜው ከፍ ሲል መልካም ገበሬ ሆነ፡፡ ከእርሻው ውሎም እንደወጉ ምርቱን አፈሰ፡፡ ጎተራውን ሞላ፡፡ ጥቂት ዓመታትን የዘለቀበት የግብርና ውሎ ከኪሳራ አልጣለውም፡፡ በጉልበቱ ድካም፣ በላቡ ወዝ አሳድሮታል፡፡

አሁን ግን ልቡ የመሀል ሀገር ኑሩን ሽቷል፡፡ ጧት ማታ ከተማ ሄዶ መኖርን እያሰበ ነው፡፡ የገጠር ሕይወት መሠረቱ ቢሆንም ዛሬ ላይ ልቡ ለውጥ እየፈለገ ርቆ መሄድን አስቧል፡፡ ገመቹ በውሳኔው ጸንቷል፡፡ ልቡ መንገድ ካሰበ ወዲህ ዕንቅልፍ ይሉት ርቆታል፡፡ ከቀዬው ተቀምጦ ከመቆዘም ራቅ ብሎ ቢሠራ እንደሚበጅ ከገባው ቆይቷል፡፡

ከአዕምሮው ደጋግሞ መከረ፤ ከውስጡ ተስማማ፣ ከቤቱ ወጥቶ ከቀዬው ራቀ፡፡ ገመቹ አሁን የከተሜ ሰው ሆኗል፡፡ አቃቂንና አካባቢውን ርቆ መሀል ሀገር በገባ ጊዜ የመጀመሪያ መተዳደሪያው የቀን ሥራ ሆነ፡፡ ውሎ አድሮ ከአንድ ድርጅት በቋሚነት ተቀጠረ፡፡ ያም ሆኖ ውሎው ከጉልበት ሥራ አላለፈም፡፡

ከቀን ሥራ በወር የሚያገኘው ገቢ በቂው ነው። የቀድሞ ህልሙ መልካም ገበሬ ሆኖ ምርት ማፈስ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እግሮቹ ሌላ ዓለም ላይ ቆመዋል። እንዲያም ሆኖ ባለበት ሕይወት አልተከፋም፡፡ ጉልበቱን ከፍሎ በላቡ ወዝ ያድራል፡፡

ገመቹ ዓመታትን በገፋበት የአዲስ አበባ ኑሮ አዲስ ሕይወትን ጀምሯል፡፡ አብሮት የቆየው የጉልበት ሥራ ልምድ ሆኖትም በአዲስ ሥራና መሥሪያቤት በደሞዝ ተቀጥሯል፡፡ ይህ አይነቱ ለውጥ ለገመቹ ሌላውን የሕይወት ምዕራፍ ከፈተ፡፡ የግራ ጎኑን ባገኘ ጊዜ ትዳር ይዞ ጎጆ ቀለሰ፡፡ ጅማሬው መልካም ሆነለት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ዓይኑን በዓይኑ አየ፡፡ የግራ ጎኑን ካገኘ ወዲህ ብቸኝነቱ ቀረ፡፡ ለእኔ ማለት ተወግዶ ለእኛ ማለትን ያዘ፡፡

በትዳራቸው አራት ልጆችን ያፈሩት ጥንዶች ‹‹አንተ ትብስ፣ እኔ እየተባባሉ ኑሮን መግፋት ይዘዋል። ለሚኖሩበት የቀበሌ ቤት ብዙ ክፍያ አይጠየቁም። ገቢያቸውን አቻችለው ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ፡፡ በህንጻ ግንባታ ሥራዎች ለበርካታ ዓመታት የቆየው ገመቹ አሁን በዕድሜው ገፍቷል፣ በሥራ ብዛት ደክሟል፡፡

እንደትናንቱ ሮጦ ለማደር፣ ለፍቶ ለማግኘት እየጣረ አይደለም፡፡ ድካም እየረታው፣ ዕድሜ እየፈተነው ቤት መዋል ከያዘ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዛሬ የቀድሞው ጎልማሳ በቀድሞ አቋሙ አይደለም። ከሥራው በጡረታ ከተሰናበተ ቆይቷል፡፡ እሱና ባለቤቱ ኑሮ እየከበዳቸው ሕይወት እየፈተናቸው ነው፡፡

ልጆቻቸው ከጎናቸው አይደሉም፡፡ ሁሉም በራሳቸው ዓለም ለራሳቸው ሕይወት እየሮጡ ነው። አዛውንቶቹ ባልና ሚስት ዛሬም በፍቅር ይኖራሉ፡፡ የዘንድሮ ኑሮ በአቅማቸው ልክ አልሆን ቢል በችግር ሊያልፉ ግድ ብሏል፡፡ ከጡረታ ክፍያ የሚገኘው ገንዘብ ከዕለት ወጪ አይዘልም፡፡ አንዱን ቀዳዳ ሲደፍኑት ሌለው ተከፍቶ ይታያል፡፡ ሌላውን ሞላ ሲሉት ጎዶሎው ይሰፋል፡፡ በቂ ገቢ የሌላቸው ዕድሜ ጠገቦች ችግር እያንገላታ ድህነት ይፈትናቸው ይዟል፡፡

የገመቹ ባለቤት ጤና ካጡ ቆይቷል፡፡ ቤት መዋል ከጀመሩ ወዲህ ተስፋና ረዳታቸው ባለቤታቸው ብቻ ናቸው፡፡ የሁለቱም ዕድሜ ገፍቷልና፡፡ አቅማቸው እየደከመ ነው፡፡ ይህ እውነታ ገመቹን በአክብሮት ‹‹አንቱ›› ብዬ እንድጠራቸው አስገድዶኛል፡፡ አሁን ከአቶ ገመቹ ጋር ጭውውት ይዣለሁ፡፡

የተገናኘነው ልደታ ክፍለከተማ ከሚገኘው የምገባ ማዕከል ውስጥ ነበር፡፡ አረፍ ብለን ጨዋታ ከመጀመራችን በፊት በእጃቸው አጥብቀው የያዙትን የላስቲክ ቋጠሮ በዓይኖቼ መረመርኩ። አልተሳሳትኩም፡፡ በፌስታል የታሰረው ቋጠሮ ምግብ የያዘ የምሳ ዕቃ ነው፡፡

በምገባ ማዕከሉ በርካታ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ እናቶችና ልጆች የያዙ ሴቶች በሰዓታቸው ተገኝተዋል፡፡ ቤቱ በእንጀራና በትኩስ ወጥ ሽታ እየታወደ ነው፡፡ ከቀረበው ማዕድ ተካፍለው፣ ከልብ አመስግነው የሚወጡትን አስተዋልኩ፡፡

የአዛውንቱ ገመቹ ሁኔታ ግን ከሌሎች ሁሉ ይለያል፡፡ እሳቸው እንደሌሎች እንጀራቸውን በትኩስ ወጥ እየጎረሱ፣ ከውሃው ሲጎነጩ አልተመለከትሁም። ከወሰዱት ምግብ አንዳች ሳይቀምሱ በምሳ ዕቃ ቋጥረው ከአዳራሹ ለመውጣት ተዘጋጅተዋል፡፡

የመጡበትን በወጉ አለማድረሳቸው እያስገረመኝ ነው፡፡ ስለምን እንዲህ ሆነ? ጥያቄው በአዕምሮዬ ተመላለሰ፡፡ አይቼ ዝም ማለት አልቻልኩም። የውስጤን ሃሳብ ፈጥኜ አወጣሁት፡፡ አዛውንቱን በቀስታ እያወጋሁ ጠየኳቸው፡፡

ገመቹ ክፉና ደጉን በእኩል የተጋሩት ባለቤታቸው በህመም ከአልጋ መዋል ከያዙ ቆይቷል፡፡ በሽታቸው የከፋ ነውና መላ አካላቸው አይታዘዝም። ሚስታቸውን ከማስታመም ባለፈ የቤቱን ሥራ የሚከውኑት ሽማግሌው አባወራ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ከቤት የሚላስ የሚቀመስ ሲጠፋ ጥንዶቹ የዘመድ ጎረቤቱን እጅ ሊያዩ ግድ ይላቸዋል፡፡

ባለቤታቸው በህመም አልጋ ይዘው ቤት ከዋሉ ወዲህ የገመቹ የዓመታት ግዴታ እሳቸውን መንከባከብና የቤቱን ሥራ መሸፈን ሆኗል፡፡ አሁን ባሉበት ዕድሜ ጎንበስ ቀና ማለቱ በእጅጉ ይከብዳል። ዓመታትን በትዳር ከእሳቸው የዘለቁት ሚስት ከባለቤታቸው ሌላ ‹‹አለሁ›› ባይ አጋር የላቸውም፡፡

ገበና ሸፋኛቸው፣ አልባሽ ፣አጉራሻቸው አዛውንቱ፤ ግማሽ አካላቸው፣ የልጅነት ባላቸው ብቻ ሆነዋል፡፡ ከዓመታት ወዲህ ሕይወት በሁለቱ አዛውንቶች ቤት ከባድ ሆኖ ዘልቋል፡፡ አሁን የአዛውንቱ የምሳ ዕቃ ምስጢር ተገልጦልኛል፡፡ ሰውዬው አንዳች ሳይቆርሱ፣ ሳይቀምሱ ይዘው መውጣታቸው እንደሁልጊዜው ከሚስታቸው ጋር በእኩል ለመጋራት ነው፡፡

ሽማግሌው በምገባ ማዕከሉ የመጠቀም ዕድል ካገኙ ወዲህ የሚሰጣቸውን ምግብ እንደቋጠሩ ከቤት ይወስዳሉ፡፡ ሁሌም ለታማሚ ባለቤታቸው ያጎርሳሉ፡፡ ለእሳቸውም ይቀምሳሉ፡፡ የዚህ የምገባ ማዕከል በረከት የአዛውንቶቹ ባልናሚስት የዘወትር ልምድና የብዙ ችግራቸው ማቅለያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You