ኦዳ በአፍሪ ሜዳ

ውቧ ወርቃማ ወፍ በጥበብ ሰማይ በራሪ እንደ ኦሮዮን ኮኮብ መስላ የአፏን ፍሬ ከለምለም መስኩ ላይ ጣል አድርጋው ነበር፡፡ ፍሬው እንቡጥ ያማረ ዘር ሆኖ ዛሬ ልክ እንደ ኦዳው ዛፍ ከሜዳው ላይ ተንዠርግጓል። ለምለሙ አረንጓዴ ሜዳ በኦዳ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች ከላይ ተንጣሎ፣ ከስር ጥላው ለጥበብና ጠቢባን ማረፊያ ሆኗል፡፡

ሜዳው ኦዳ አፍሪ፣ ጥበብ አፈራሽ ነው፡፡ ኦዳም ስሩን እየሰደደ፣ ግንዱ ሽቅብ ወደላይ፣ ቅርንጫፎቹም በአራቱም ማዕዘናት “አፍሪ! አፍሪካ!” ሲሉ በኅብረ ዝማሬ እየተንሰራፉ ከሀገር ወጥተው ጉዞ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ብለዋል፡፡ ትንሽዬዋ ኦዳ በቅላ ሰማይ ጠቀስ መምዘግዘጓን ቀጥላለች፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት ከምለሚቷ የኦሮሚያ ጥበብ፣ ከተዋበው ሜዳ ላይ ብቅ ያለው ኦዳ ከክልል አጥር ዘሎ፣ ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያም ወጥቶ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በጥበብ ተራሮች አናት ላይ እንደ ችቦ በርቶ ከሩቅ ይታያል። ኦዳ ቅርንጫፎቹን በነፋሻማው ንፋስ እንደ ባንዲራ እያውለበለበ “አፍሪ አፍሪካ ላምባዲና፤ ኑ! ወደኛ ኑ! መዲና” እያለ ይጣራል፡፡ እስከ ዘንድሮው ዓመት ድረስ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ ድምፁ ከፍ ብሎ ተደምጧል። ቀጣይ እያየለ መላውን አፍሪካ እንደሚያጥለቀልቀው ተስፋ ብቻ ሳይሆን ከልብ የሞላ እምነትም አይዋዥቅም፡፡

አሁን አሁን የሀገራችን የጥበብ ዋልታና ካስማ ጠንከር ማለት መጀመሩን እያስመለከተን ይመስላል፡፡ የጥበብ ባለውለታ ክዋክብቶቻችን በየዘመናቱ አስታዋሽ አጥተው እዬዬ! ሲያስብለን እንዳልነበር አሁን ከኛ አልፈን ወደ ጎረቤት ሀገራት ወደ አፍሪካ አደባባይ እየወጣን ያለን መስሎ ይታያል፡፡ ብርታት በወኔ ታላቅነትና ጥበብ አፍሪ መጋቢ ነው፡፡ “በርታ!” ያሉት ፈረስ እንኳን ቁልቁለት አዳልጦ፣ ዳገት አይዘውም፡፡

ደግ ደጉን በሠራ ቁጥር ሁሉ “በርታ አለንልህ!” ያሉት የጥበብ ልጅም ግዛቱ እስከዓለም መዳረሻ ነው፡፡ እነኚህ “በርታ!” ባዮችም ዛሬ ላይ በሀገራችን በርከት እያሉ መጥተዋል፡፡ ስራቸውን ስር እየሰደዱም አፍሪ ጠቢብ ሆነው፤ አኩሪ ጥበብ ክዋክብትን እያበዙ ናቸው፡፡ ከአንድ ወር በፊት የ10ኛውን የጉማ በረከት በልተን ጠጥተናል፡፡ አሁን ደግሞ ከኦዳ ሜዳው ላይ ዱብ! ዱብ! ጀምሯል፡፡

ከጉማ የ2 ዓመት ታናሽ የሆነው ኦዳ ስምንት ዓመት ሆነው፡፡ 8ኛውን ዙሩም አክሮ መጥቷል፡፡ ከኦሮሚያ ብቅ ብሎ ከመሐል አዲስ አበባ ፈንድቷል፡፡ ሀገራዊ ሆነ ከማለታችን በመግነጢሳዊ ፍጥነትና ለውጥ ፍንጥርጣሪው በመላው የምሥራቅ አፍሪካ ያደረገበትን ሁለተኛ ዓመት፣ 8ኛው ዙር የሚጠብቀው ኅዳር 27 ቀንን ነው፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ የምንለውና የሚያስፈልገንም ይኼው ነበር፡፡ መዲናነት የበኩርነት ነውና ጅማሬውን አስቀጥለን ገና መላውን አፍሪካ ማዳረስ ይጠብቀናል፡፡

በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ ከፍ ብሎ መውለብለብ ያለበት ባንዲራዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ጥበቦቻቸው ጭምር ነው፡፡ ሠገነቷ ለአፍሪካ የጥበብ ልጆች መናገሻ ማማ መሆን አለበት፡፡ ‹‹ማማ አፍሪካ…››

ጉዞው ተጀምሯል፡፡ ዓመታዊው ኦዳም ከክልል ተነስቶ የዚህ ጉዞ መሪና ጀማሪ ሆኗል፡፡ እንደ ክልል ጀምሮ እንደ አሕጉር ሊከሰት አስቧል፡፡ በባለፈው ዓመት የ7ኛ ዙር ላይ በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ለማሳካት ችሏል፡፡ አጀማመሩ ሲታይ በ2010 ዓ.ም ሲነሳ ዓይኖቹን በኦሮሚኛ ቋንቋ በተሠሩ የጥበብ ሥራዎች ላይ ብቻ አድርጎ ነበር፡፡ ግን በረገጠበት እግሩን ተክሎ አልቀረም፡፡ በየዓመቱ አዳዲስ ነገሮችን ነስነስ እያደረገ ይበልጥ ጣፋጭ አድርጎታል፡፡

እስከ ሦስተኛ ዙር ድረስ በክልል ዛቢያ ተሽከርክሮ በመስፈንጠር በአራተኛው ዙር አንድ ከፍ ብሎ በሌሎች ቋንቋዎች የተሠሩ ሥራዎችንም በማካተት ሀገራዊነቱን አሳየ፡፡ ሁለት ዓመታትን በሀገር ቤት ቆይቶ በ7ኛው ዙር ወደጎረቤት አለ፡፡ ከመጀመሪያው አንስቶ 3…2…እያለ መጥቷልና ለመጪው አንድ ደግሞ አንድ ብሎ ክብረ ወሰኑን በመስበር አፍሪካ አደባባይ ላይ እንጠብቃለን፡፡

በሄደው ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም አዘጋጆቹ የሚዲያ ጥሪ አድርገው ነበር፡፡ ሚዲያው ሁሉም ጠሪ አክባሪ ነውና ደርሶ ካሜራና ጆሮውን ሰጥቷል፡፡ የዚህ ዝግጅት ፊት ዘማቹ በሻቱ ቶሎማሪያም መልቲሚዲያ ጉዳዩን ከማብራሪያ ጋር አውግቶታል፡፡ ለዚህ ሽልማት ለእጩነት ያበቃው ቀን መቁጠር የጀመረው በ2016 ዓ.ም መስከረም 1 ቀን ሲሆን መጥቶ መጨረሻውን የገጨው በጳጉሜ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ነው፡፡ 365 ቀናት ድፍን አንድ ዓመት ሞላ ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት መካከል ከተሠሩ ሥራዎች ተመራርጠው ለመሸለም ተዘጋጅተዋል፡፡

ጠቅለል ባለው ቁጥራዊ መዳረሻው 14 ዓይነት ሽልማቶች በሦስት መቅረዞች ተቀምጠዋል፡፡ እኚህ ሦስት መቅረዞችም ሙዚቃ፣ መጽሐፍ እና የሕይወት ዘመን ናቸው፡፡ ከ14ቱ ስምንት ያህሉ በሙዚቃ የሰፈሩ ናቸው። ምርጥ አልበም፣ ነጠላ ዜማ፣ የቪዲዮ ክሊፕ፣ ድምፅና ምርጡን ጥምረት ያካተት ነው፡፡ በመጽሐፍ ዘርፍ “የዓመቱ ምርጥ ልቦለድ” እና “የዓመቱ ምርጥ የግጥም መድብል” በሚል በሁለት ጎራ ተመድበዋል፡፡ በሕይወት ዘመን ተሸላሚነትም ሦስቶቹ ነጥረው ወጥተዋል፡፡

ደግሞ ሌላም አለ፤ “ኢስት አፍሪካን ሱፐር ስታር” የሚል፡፡ በኦዳ ቤተኛው ብቻ አይደማምቅም፤ የጎረቤት ጀመአው ሁሉ ሽር ብትን ሊልበት ነው፡፡ ከቀድሞዋ ልጅ ከኤርትራ፣ ከኬንያ፣ ግራና ቀኝ ከቆሙት ሁለቱ ሱዳኖች፣ ከሶማሊላንድ፣ ከዩጋንዳና ከሲሸልስ ታጅበው አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡

መግባታቸው እንዳለ ሆኖ በባሕልና ቋንቋ ለየቅል የሆኑትን እኚህን ኦዳ በምንስ መስፈርትና እንደምን አድርጎ መረጣቸው? የብዙዎች ጥያቄ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የራቁትን ቀርቶ እዚሁ በራስ ቋንቋን ባሕል የሠሩትንም አበጥሮ ማውጣቱ ምርኩዝ ያልተያዘበት ተራራ ነው፡፡ ይሁንና የምሥራቅ አፍሪካ ታላላቅ ክዋክብቱን በመመልመል ሂደቱ አዘጋጆቹ የተጠቀሙት መላ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙት በየሀገራቱ ኤምባሲዎች በኩል ማለፍን ነበር፡፡ እነርሱም ልክ እንደኛው በኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ዘርፍ የሚሠራ መንግሥታዊ ተቋም አላቸውና ከኤምባሲው ጋር ተጣምሮ የቤት ሥራውን ለተቋሞቻቸው ማስረከብ ነበር፡፡

የነርሱን ኮከብ የመምረጥ ኃላፊነቱን የወሰዱት ተቋማት እንደራሳቸው ፍላጎትና የኦዳን ቅኝታዊ እሳቤ በሚጣረስ መልኩ እንዳይሆን አስቀድሞ በዳኞቹ የተቀመጠው መስፈርት ተልኮላቸዋል፡፡ የቋንቋና ባሕል ሁኔታው እያንገዳገደም ቢሆን ዳኞቹም በተቻላቸው ሁሉ ተጨማሪ እይታና ግምገማ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡

በዘንድሮው ኦዳ ስምንት የዝግጅቱ አጋሮችም በርከት ብለዋል፡፡ ከመካከል የኢትዮጵያ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ብቅ ብሏል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ኦዳ ሽር ሲል የነበረው ከኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ነበር፡፡ እርምጃውን አፈጣጥኖ ከክልል ሲወጣ በሀገር ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ተቃቅፏል፡፡ ከእንግዲህ ወዲያም የሚለያዩ አይመስልም፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ዕለትም የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፤ ክብርት ነፊሳ አልማህዲ ተገኝተው የጽ/ቤቱን እቅድ ሀሳብ አጋርተዋል፡፡ “አንጋፋዎቹን መሸለም ማለት ተተኪን ማፍራት ማለት ነው፡፡ ይህን ሲመለከቱ ከውስጣቸው ተነሳሽነትና የአዕምሮ ለውጥ ለመፍጠር ይቻላል፡፡ መሸለም ያለባቸው አካላት ያለምንም አድሎ መሸለም እንዲችሉም እኛ በሙሉ ደጋፊነት ከአዘጋጁ ጎን እንቆማለን” ብለዋል፡፡ እኛም የቆሙበት አያዳልጣቸው ብለናል፡፡

ከሙያዊ ድጋፍ ባሻገር በገንዘብ ቢሆን ወሳኝ ለሆኑ ጉዳዮች እጁን አጣምሮ እንደማይመለከት አንስተውታል። በጎን ደግሞ የበሻቱ ቶሎማሪያም መልቲሚዲያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ራሷ በሻቱ ቶሎማሪያም ነበረች፡፡ “ኦዳ አዋርድ መለያው ያደረገው ታማኝነቱን፣ የውድድር ሂደቱን ከአድሎ የፀዳ፣ ሥራና ሥራን ማማከል ብቻ ነው” ብላለች።

ሁለቱ አካላት ከሌሎች ጋር ተጣምረው ከብሔር ብሔረሰቦች የጥበብ ጫካ ይገባሉ፡፡ የመንግሥት እንደራሴው የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ካለው ልምድ መራጮቹን ይመርጣል፡፡ ተመራጭ ዳኞችም ምርጥ ምርጡን የጥበብ ሰው አድነው ያቀርባሉ፡፡ ከሀገር ውስጥ ትልቁ ኮታ በኦሮሚኛ ለተሠሩ ሥራዎች ቢሆንም ሌሎቹም ቀላል አይደሉም፡፡

ኦዳ በአንድ ቋንቋና ብሔር የተሠራ ቅርጫት እንዳይሆን በኅብር ተውቧል፡፡ በባለፈው ዓመት አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ ሶማሌ፣ ሐረሪና ሲዳማ ገብቶ ታላላቆችን አውጥቷል፡፡ በዘንድሮው ደግሞ ከኦሮሚያ ባሻገር ወደ ትግራይና ቤተ ጉራጌ ገብቷል፡፡

የኦዳ ትልቁ ዓላማ የሠራውን በሥራው መሸለም ስለሆነ ሥራን ከሥራ፣ ሠሪን ከስሩ መመልመሉ እንደመሸለም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ከመሸለም ከባዱ የሚሸልሙትን አንጥሮ ማውጣቱ ላይ ነው፡፡ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርም ለታላላቅ የሀገራችን የሙያ ጠበብት ካለው ቅርበት በመነሳት ይህቺን አቅጣጫ ለማሳለጥ ማሰቡ መልካም ነው፡፡ በዚህ የሁለትዮሽ መረጣም ዓይኖቻቸው ያረፈው በጥበብ ብቻ ሳይሆን በቀለምም ወደመጠቁት ሆኗል፡፡ በምርምር ሥራዎቻቸው ልቀው የሄዱትንና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በመምህርነት የቀለሙትን መርጠዋል፡፡ እንግዲህ በኦዳ መድረክ ላይ ሲምነሸነሹ የምንመለከታቸው ሁሉ የእነዚህ ዳኞች የፍርድ ውሳኔ ናቸው፡፡ ዳሩ ግን በሙዚቃው ዘርፍ በምንመለከታቸው ላይ 30 ከመቶው በሕዝብ ውሳኔ የሚጸና ነው፡፡ ለምርጫው የምርጫ ካርድ ሳያወጡ በእጅ ስልክ 8030’ን ጠቅ በማድረግ የፈለገ ሁሉ የራሱን ጀግና ለማንገስ ይችላል፡፡

ኦዳ 2017 ለክብር አጭቶ በሕይወት ዘመን ተሸላሚነት ያሰፈራቸውን አስቀድሞ ይፋ አድርጓል፡፡ ብሔር ብሔረሰባዊ አድርጎ ለሁሉም የወጣው ወደ ሙዚቃው ተራራ ነው፡፡ ታዲያ ከመካከል አንዱ የሆነውን ድምፃዊ ኪሮስ ዓለማየሁን ሲጠሩ፤ ከሞተ ስንቱ ዓመት አልፏልና ምን ነካቸው ያስብል ይሆናል፡፡ ግን ጠቢብ እንጂ ጥበብ ሞታ አታውቅም፣ ሠሪን እንጂ ሥራንም አፈር አይበላውም፡፡ መቃብርም ችሎ አይውጠውም፡፡

የሽልማቱ ገበታዎች ሥራዎቹ ናቸውና እርሱ በሕይወት ኖሮ ባይቀበልም ሥራዎቹ ቆመው በጭብጨባና ፉጨት ያግሉታል፡፡ እነርሱ ተቀብለው በማይሞተው ስሙ አናት ላይ እንደ ክብር አክሊል ያኖሩለታል፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግለትና በትግርኛ ሙዚቃዎቹ አብዝተን የምንወደው ኪሮስ ዓለማየሁ አንደኛው ነው፡፡ ሴቷ ድምፃዊት እልፍነሽ ቀኖ በኦሮሚኛ ትከተላለች፡፡ ሰቦ ሶሬሳ ደምሴ ተካ ደግሞ በጉራጊኛ ሙዚቃ ለሦስት አብረው የክብር ጃኖ ይለብሳሉ፡፡

የኦዳ አካሄድ አንድም በጋራ መቆም ስንችል ምንም ነገር ያለምንም ገደብ ለማድረግ እንደምንችል የሚያሳየን ነው፡፡ ወጪ ካሉ በጠቅላላው ለዚህ ዝግጅት የሚያስፈልገው ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ አንስተውታል፡፡ ነገር ግን ኦዳ ባለው አቅም ይሄ የሚታሰብ አይደለም፡፡ አንድነት ኃይል ያደረገው ነገር ከግማሽ በላይ ወይም ግማሽ ያህሉ የተሸፈነው በአጋር አካላትና በሌሎች ሙያዊ፣ ቁሳዊና የጉልበት በመሳሰሉትን የበጎነት ችሮታ ነው፡፡

መንገዱን ቀይሶ፣ ንድፉን በቦታና ጊዜ፣ ምስለ መልኩን በልብ ወረቀት ካሰፈሩት ሕንፃውን የሚያቆመው አይጠፋም፡፡ አነሳሽ ይኑር እንጂ የሚነሳው ብዙ ነውና ለሌሎችም ብርታት ይሆናል፡፡

በ2016 ዓ.ም ጀንበር፣ ከመስከረም 1 ንጋት እስከ ጳጉሜ 5 አመሻሽ በየወራቱና ሳምንታቱ ከሥራዎቻቸው ብልጭታ ጋር ብቅ እያሉ ሲያበሩ ከነበሩት የኦርዮን ክዋክብት መካከል ኦዳ 2017 ሌላ እነማንን መርጠ…ከኢትዮጵያ አይድል ተነስቶ በማይጠገብ የኦሮሚኛ አልበሙ መላው የሙዚቃ አፍቃሪ በእግሮቹ ቆሞ ያጨበጨበለት አንዷለም ጎሳ (ቢሊሌ) በምርጥ የቪዲዮ ክሊፕ እንዲሁም በሁለቱም ዘርፎች ተካቷል፡፡ ለምለም ኃይለሚካኤል (ዋለኔ) በምርጥ የቪዲዮ ክሊፕ፣ በዓመቱ ምርጥ ሴት ድምፃዊት፣ ቀጥሎም በሦስተኛው የነገ ተስፋ ከተጣለባቸው ምርጦቹ እንቡጥ መካከል ተካታለች፡፡

ሌላኛዎቹ ባለተስፋ ደግሞ አዳዲስ ባለተስፋዎች አሳንቲ አስቹ (ሚራራ ኮ)፣ ሐና ተስፋዬ (ሎቴ)፣ መሳይ በቃሉ (ሌሎ)፣ ኦብሳ አዱኛ (ታካ ታካ) ናቸው፡፡ በዓመቱ ምርጥ ሴት ድምፃውያን ጉብታ ላይ በእጩነት አሳንቲ አስቹ (ሚራራ ኮ)፣ ኤልሳ ንጉሴ (ጉዲን)፣ ሐና ተስፋዬ (ሎቴ)፣ ያኔት ድንቁ (ዳማ ዳሙ) ተቀምጠዋል፡፡

ሹክሪ ጀማል (ፍርቱ)፣ አብራር እንዳለ (ዳዎ)፣ ሌንጮ ገመቹ (ዋላቡ)፣ ሌንጮ ጉዲና (ሲን ማራሩ) በነጠላ ዜማዎቻቸው የዓመቱ ምርጥ ለመሆን በዕጩነት ተካተዋል፡፡ አብዲ ሃጫሉ (ኪሊማንጃሮ)፣ ጉቱ አበራ (ኢዮሌ)፣ ዮናን ብሩክ (አዋሽ) የምርጥ የቪዲዮ ክሊፕ ዕጩዎች ሆነዋል፡፡ ሌላኛውና ከፍ ያለው የ2016 ዓ.ም ምርጡ የአልበም ሥራ የማን ይሆን የሚለው ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ጉቱ አበራ (ጋፊኮ)፣ ሞቲ ሮባሌ (ዱጋ)፣ ተስፋዬ ጥላሁን (ኤባ) አልበሞች ናቸው። እያንዳንዱ ሙዚቀኛ በሜዳው መምና በዙሪያው ማራቶን ሁሉ ሮጦ በግል ክብረወሰኑን ለመስበር ከምርጥ ሥራው ጋር ሜዳዩን ይጠባበቃል፡፡

ከግል ጥረት ወጣ ብሎ በኦዳ ምርጡ ጥምረት እንደ ቡድን ሥራ እነማን ነበሩ? ይላል፡፡ ጣምራዎቹ ዕጩዎችም አዳም መሐመድና ጫልቱ ቡቶ (በጋዳ ማሌ)፣ አወል ሲሮና ሃሊማ አብደላ (በሻኒ ኬሳ)፣ ጫልቱ ናኔሶና ባሮ ዲዳ (በኬ አና)፣ ካሊድ አማንና ሌንጮ አብዱሻኩር (በ ና አማን)፣ ተስፋዬ ጥላሁንና ሃልኮ ቃሳሮ (በአርሲ ባሬዳ) አንደኛው ጥምረት ዋንጫውን ከፍ ያደርጋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ክዋክብትም ከፍ ብለው ይቀጥላሉ፡፡

ከሙዚቃ ሥራዎች ውጪም ባለቅኔዎቹ ገጣሚያንና ብዕረኞቹ ደራሲያን ይቀጥላሉ፡፡ የክብር ካባ ደርበው፣ ለውለታቸው ትንሽ ትልቁ ሁሉ ከፍ ዝቅ ብሎ የሚያመሰግናቸው የሕይወት ዘመን ተሸላሚዎችም የምንጊዜም ምርጦች ሆነው ይነግሳሉ፡፡

ከአንጋፋው እስከ አዳዲስ ጀማሪ ክዋክብት በዚህ ልክ ሁሉም ልኩን ያገኛል፡፡ ዕጩዎች በታዛቢነት ቆመው ሥራዎቻቸው ከሌሎች ሥራዎች ጋር አንገት ላንገት ከሜዳው ላይ ትግል ይገጥማሉ፡፡ ዳኞች በትኩረትና በጥንቃቄ እያንዳንዱን እየመረመሩ ያወዳድራሉ፡፡ የአሸናፊዎቹ ሁሉ አሸናፊ ሆነው በድል የረቱ ሥራዎች፤ ለባለቤቶቻቸው የኒሻን ዓርማ ሆነው ድል በድል ይደምቃሉ፡፡ የዋርካ ጥላው ኦዳ ነው፡፡ ሜዳው የጥበብ ነው፡፡ ጥበብና ጥበበኛው ሁሉ ወደ ሜዳው ገብቷል፡፡

ከሜዳው በላይ ከፍ ብሎ የቲፎዞው ድምፅ ይሰማል። ካታንጋ የለ ሚስማር ተራ፤ አኩሪና አፍሪ ሁሉም ሸራተን አዲስ ነው፡፡ ሁሉም በነገው እለት ችቦውን ያበራል፡፡ ደማቁ አመሻሽም በኦሪዮን ኮከብ፣ ከክዋክብቱ ጋር ሽር ብትን ይላል፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You