ወደ ሰላም የሚደረግ ጉዞን ማበረታታት ያስፈልጋል !

መላው ሕዝባችን የሚሻውን ብልፅግና እውን ለማድረግ ከሁሉም በላይ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ያስፈልገናል። ከግጭት አዙሪት ወጥተን ሰላምን በሁለንተናዊ መልኩ ማጣጣም የሚያስችል ማኅበራዊ ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ የአስተሳሰብ ልዕልናን እውን ለማድረግ ም ፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር ግድ ይለናል።

የትናንት ተጨባጭ ታሪካችን እንደሚነግረን ፤ በቀደሙት ዘመናት ከነበርንባቸው የሥልጣኔ ማማዎች / ከፍታዎች ያወረዱን እና ዛሬ ላይ ሆነን የተገኘነውን እንድንሆን ያደረጉን በየዘመኑ የነበሩ የሰላም እጦቶች ናቸው። እነዚህ የሰላም እጦቶች ካስከፈሉን ቁሳዊ እና ሠብዓዊ ያልተገባ ዋጋ ባለፈ የእያንዳንዱን ትውልድ ተስፋዎች ነጥቀዋል።

ስለ ራሳቸው ሆነ ስለሀገራቸው ነገዎች ብዙ ህልም የነበራቸውን ትውልዶች ፤ በሰላም እጦት ምክንያት ሕልሞቻችውን መኖር ሳይችሉ ቀርተዋል። ግጭቶች በፈጠሯቸው ግራመጋባቶች ተስፋዎቻቸውን ተነጥቀው ፤ ተስፋ መቁረጥ በፈጠረው ባዶነት ወደመቃብር ወርደዋል፡፡

እንደ ሀገር የመጣንበት የግጭት አዙሪት ማንንም አላተረፈም። የግጭት ምንጭ ከሆኑ የአስተሳሰብ መዛነፎች ያተረፉ የመሰላቸውም ቢሆን ፍጻሜያቸው ያማረበት ሁኔታ አልተፈጠረም። ችግሩ ሀገር እና ሕዝብን ከአንድ የፈተና የታሪክ ምዕራፍ ወደሌላ የፈተና ምዕራፍ ከማሸጋገር ባለፈ ያተረፈው ፋይዳ አልነበረም።

ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ ያጋጠመንን ተጨባጭ እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ይዘነው ከመጣነው እና በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ካስከፈለን የአስተሳሰብ ዝንፈት የተቀዳ ነው። ከትናንት ካለመማራችን የሚመነጭ ፤ ለታሪክ ያለንን የተሳሳተ ግንዛቤ አደባባይ ይዞ የወጣ ፤ ያስከፈለንም ዋጋ በብዙ መልኩ ከቀደሙት ዘመናት የከፋ ነው።

በለውጡ ዋዜማ እንደ አንድ በለውጥ ውስጥ ተስፋን እንደሰነቀ ሀገር እና ሕዝብ ፤ በብዙ መነቃቃት የጀመርነው አዲስ የታሪክ ጉዞ ፤ የተዛነፉ አስተሳሰቦች በፈጠሩት ግራ መጋባት ፤ ግራ መጋባቱ በፈጠረው ጥላ፤ በተለመዱ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ እና ለመንገጫገጭ ተገድዷል። መንገጫገጩ በፈጠረው ጥፋትም ብዙዎች ከተስፋቸው ጋር ተጋጭተዋል።

የተዛነፉ አስተሳሰቦች እና አስተሳሰቦቹ በወለዷቸው ግራ መጋባቶች ፤ አንዳንዶች አምጠው የወለዱትን የለውጥ አስተሳሰብ ፤ አስተሳሰቡ የወለደውን ተስፋ በአደባባይ በጠብመንጃ አፈሙዝ ተገዳድረዋል። በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችን ተስፋ ባመከነ መልኩ መንገድ ላይ ቆመው የራሳቸውን እና የሕዝባቸውን ከዚያም አልፎ የሀገርን ተስፋ ለማምከን ረጅም ርቀት ተጉዘዋል።

ሁሉም የዜሮ ብዜት ከመሆን ባለፈ እንደ ሀገር የፈጠረልን አንዳች ነገር የለም። በብዙ የመስዋዕትነት ተጋድሎ አሁን ላይ የደረሰችውን ሀገር ህልውና ስጋት ውስጥ ከመጨመር ፤ ስጋቱን ለመቀልበስ ያልተገባ የከፋ ዋጋ ከመክፈል ባለፈ ያመጣልን አዲስ ነገር የለም።

እንደ ትናንቱ ያለንን ከማሳጣት ባለፈ የጨመረልን ምንም ነገር የለም ፤ እንደ ትናንቱ እንደሀገር መኖራችን ሁሌም ስጋት ለሚሆንባቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን፤ ለጥፋት ተልዕኳቸው ተጨማሪ ዕድል ፈጠርንላቸው እንጂ ተስፋችንን ተጨባጭ ለማድረግ አቅም አልሆነንም። እንደ ትናንቱ ለለውጥ መነቃቃታችን ጥላ ሆነን እንጂ ጉልበት አልፈጠረልንም ።

አሁን ግን ከትናንት፤ ከዛም ባለፈ ዛሬ ላይ በራሳችን ከፈጠርናቸው ስህተቶቻችን በመማር ለሰላማችን ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን ልንቀሳቀስ ይገባል። ከተዛነፉ አስተሳሰቦች እና አስተሳሰቦቹ ከሚወልዷቸው ግራ መጋባቶች ትውልዱን በመታደግ ፤ የሕዝባችንን የለውጥ ተስፋ ተጨባጭ ለማድረግ ከራሳችን ጋር መታረቅ አለብን።

መላው ሕዝባችን የሚሻውን ብልፅግና እውን ለማድረግ ከሁሉም በላይ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ለማስፈን፤ ከግጭት አዙሪት ወጥተን ሰላምን በሁለንተናዊ መልኩ ማጣጣም የሚያስችል ማኅበራዊ ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ የአስተሳሰብ ልእልናን እውን ማድረግ ብሎም ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅብናል።

በቀደሙት ዘመናት ከነበርንባቸው የሥልጣን ማማዎች / ከፍታዎች ያወረዱን እና ዛሬ ላይ ሆነን የተገኘነውን እንድንሆን ያደረጉን፤ እንደ ጥላ የሚከተሉን የሰላም እጦቶች በቀጣይ እኛንም ሆነ ቀጣዩን ትውልድ ተመሳሳይ ዋጋ እንዳያስከፍሉ በኃላፊነት መንፈስ ፤ በሰከነ አዕምሮ ልንቀሳቀስ ይገባል ።

ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ እየሆነ እንዳለው ፤ በሀገር እና በሕዝብ ተስፋ ላይ ጠብመንጃ አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ወደ ሰላም የሚያደርጉትን ጉዞ በሚቻለው እና ባለው አማራጭ ሁሉ ማበረታታት ያስፈልጋል ፤ ወደዚህ መንገድ ለመምጣት ከቀልባቸው ያልሆኑትንም ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ በተመሳሳይ መልኩ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል!

አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You