የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ሥራዎች እና ቀሪ የቤት ሥራዎች

ትምህርት የአንድን ማኅበረሰብ እሴቶችና የተከማቸ እውቀት ማስተላለፊያ መንገድም ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል በትምህርት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ቁልፍ መሣሪያ ነው የሚለውንም መርህ የዓለም ሀገራት የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን የዓለም ሀገራት በሙሉ ትምህርትን ለለውጥ ተጠቅመውበታል ለማለት ብዙም አያስደፍርም።

የትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አብሮ የሚቀያየር ስለመሆኑም ይነገራል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ላይ ለሚታየው ስብራት በርካታ ምክንያቶች አሉ። ለአብነት የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የመምህራን አቅም ማነስና መሰል ችግሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ከሰሞኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴርን የበጀት ዓመቱ የ3 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ከመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመምህራንን አቅም ለመገንባት ከ 44 ሺህ በላይ መምህራን ሥልጠና መስጠቱን በሪፖርቱ አመላክቷል። የሁለተኛ ደረጃ የተማሪ መፅሐፍት በሁሉም ክልሎች 1 መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ ለማድረስ መቻሉም ተገልጿል።

በትምህርት ዘመኑ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከ32 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ 21 ሚሊዮን 723 ሺህ መመዝገብ ተችሏል። የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ቁጥሩ በሚጠበቀው ልክ እንዳይሆን አድርጎታል ተብሏል።

በተማሪዎች ምገባ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ቁጥሩ በሚጠበቀው ልክ አለመሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል። የሁለተኛ ደረጃ መፃሕፍት ተደራሽነት ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትኩረትና ክትትል እንዲያደርግ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ወደ መምህርነት ሙያ የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ይህንን ለማስተካከል ዘርፈ ብዙ የማትጊያ ሥርዓቶች ይዘረጋሉ ያሉ ሲሆን መምህራን በአገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የራሳቸው ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችል የመምህራን ባንክ የማቋቋም ሀሳብ መኖሩን ጠቁመዋል።

የትምህርት ጥራትን ችግርን ለመቅረፍ በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ይገባልም ብለዋል። መሥሪያ ቤታቸው የዩኒቨርሲቲዎችን የተማሪ ቁጥር ለመጨመር ብሎ የትምህርት ጥራትን ጥያቄ ውስጥ እንደማይከትም ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ትምህርትና የተማረ ሰው እንዲከበር የመምህራንን አቅምና ጥቅም ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል። እንደ ሀገር የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የመምህራን ብቃት በረዥም ጊዜ ዕቅድ ሊሰራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም አንገብጋቢ የሆነውን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የትምህርት ባለሙያ እና በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር አማኑኤል ኤሮሞ እንደሚናገሩት፤ የትምህርት ጥራትን አመላካች ነው የሚባለው የተማሪዎች ውጤት ነው።

በተማሪዎች ውጤት ላይ ደግሞ ከፍተኛ ሚና ያላቸው አራት አካላት ናቸው ይላሉ። ተማሪው፣ ወላጅ፣መምህር፤ ርዕሰ መምህር እና የትምህርት ቤቱ ምቹ ሁኔታ ናቸው፤ እነዚህ አካላት ናቸው በተማሪ ትምህርት ጥራት ላይ ትልቅ ሚና ቀድመው የሚጫወቱት ሲሉ ያክላሉ።

የትምህርት ጥራት የሚለካው ብቁና መልካም ስነምግባር ያላቸውን ዜጎች በማፍራት ነው የሚሉት ዶክተር አማኑኤል፤ በተጨማሪም ከክፍል ወደ ክፍል የሚዘዋወሩ ተማሪዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት በዋናነት የትምህርት ጥራት መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል ይላሉ።

ዶክተር አማኑኤል እንደሚናገሩት፤ እንደ ኢትዮጵያ በተለይ የ12ኛ ክፍል ውጤት በትምህርት ጥራት ያለንበትን ደረጃ ማየት የሚያስችለን ነው። ምክንያቱም ተማሪዎች ደረጃውን የጠበቀ ፈተና የሚወስዱት በዚህ የክፍል ደረጃ በመሆኑ በትምህርት ጥራት እንደ ሀገር ያለንበትን ደረጃ ማወቅ የምንችለው በዚህ የፈተና ውጤት ነው።

ትምህርት ማለት በራሱ ጥራት ማለት ነው የሚሉት ዶክተር አማኑኤል፤ የትምህርት ጥራት ሲጓደል እንደ ሀገር ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ ሀገሪቱ በቢልዮን የሚቆጠር ከፍተኛ ገንዘብ ትምህርት ላይ ኢንቨስት ታደርጋለች፤ ነገር ግን የምታገኘው ውጤት አስከፊ እንደሆነ ይናገራሉ።

በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እየተመዘገበ ያለው ውጤት በመቶኛ ሶስት በመቶ ነው፤ ይህ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ለ12 ዓመታት የቆዩ ተማሪዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት ይህ ከሆነ ለዘርፉ ሀገሪቱ ያወጣችው ከፍተኛ ውጪ ለኪሳራ ተደርጓል ብለን መውሰድ እንችላለን ይላሉ።

22 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በተለያዩ ደረጃዎች በሀገሪቱ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል የሚሉት ዶክተር አማኑኤል፤ ሀገር ያላት ሀብት ውስን ነው። ይህንን ውስን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ሲገባ በተቃራኒው እየባከነ ነው። ጥራት የሌለው ትምህርት እየወሰደ ያለው ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ጉዳይ እንደ ሀገር መፍትሔ የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ይላሉ።

የአንድ ሀገር ሀብት በዋናነት ዜጎች ናቸው የሚሉት ዶክተር አማኑኤል፤ ብቁ ያልሆነ ዜጋ ደግሞ ጠንካራና የበለፀገች ሀገር መፍጠር አይችልም። ትምህርት ሀገር የሚቀርፅ መሣሪያ ነው። ይህንን መሣሪያ በአግባቡ ለመጠቀም በመሠረታዊ የትምህርቱን ጥራት ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ሥራ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።

የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በመጀመሪያ ደረጃ ተገቢነት ያለው ስርዓተ ትምህርት አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚናገሩት ዶክተር አማኑኤል፤ በሌላ በኩል ብቁ የትምህርት አመራሮችና መምህራን ያስፈልጋሉ፤ መምህሩ በትምህርት ጥራት ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፤ ከተማሪ ውጤት 35 በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው መምህር ነው። ከዚህ አኳያ ሥራውን አክብሮና ወድዶ የሚሠራ ብቃት ያለው መምህር ማፍራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

በተጨማሪም የግብዓት አቅርቦት በትምህርት ጥራት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፤ በተለያዩ ክልሎች ተማሪዎች የመመሪያ መፅሐፍት እንኳ የሏቸውም፤ ከዚህ ባለፈ የሚሰጠው ትምህርት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አይደለም በዚህ አካሄድ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ የሚከብድ ይሆናል ይላሉ።

በሌላ በኩል በአመራሩ፣ በርዕሰ መምህሩም ሆነ በመምህሩ ላይ ተጠያቂነት መኖር አለበት፤ ማለትም ጥሩ ሥራ ከሰሩ መሸለም ከደረጃ በታች ሥራ ከሰሩ ደግሞ መጠየቅ አለባቸው። አሁን በእኛ አካሄድ ይህ አሰራር የለም፤ ጠቅላላ ተማሪ ቢወድቅም እንዴት ሆነ ተብሎ ርዕሰ መምህሩ አይጠየቅም። በጠንካራ ሥራ ደግሞ ሁሉንም ተማሪ ማሳለፍ ቢችልም የሚያበረታታ አካሄድ የለም። ይህ አካሄድ መስተካከል እንደሚገባው ይናገራሉ።

የትምህርት ጥራት በቀጥታ ከመምህራን ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የመምህሩን ኢኮኖሚያዊ ችግር መቅረፍ ወሳኝ መሆኑን በአፅንኦት የሚያነሱት ዶክተር አማኑኤል፤ መምህር ከፍተኛ የኑሮ ጫና ተጋርጦባታል፤ በዚህ ሁኔታ እያለፈ እውቀቱን ለተማሪዎቹ በበቂ ሁኔታ ያስተላልፋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው ይላሉ።

በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ትምህርት እና ፖሊሲ ጥናት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር እንዳለው ፉፋ በበኩላቸው፤ የአንድ ትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ሁልጊዜ ከተማሪው ከፍተኛ ውጤት በመጠበቅ መስራት አለበት። በሌላ ጎኑ ትብብር እና ግንኙነት በመፍጠር በጋራ መሰራት መቻል አለበት። በትምህርት ቤቶች ትልቁ ነገር ሥርዓተ ትምህርቱ፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ፣ የተማሪዎች የመማር ሂደት በየጊዜው መገምገም ሲሆን፣ እነዚህ ተቀናጅተው በየዕለቱ መሰራት አለባቸው ይላሉ።

ሌላው አጋዥ ሁኔታዎች የሚባሉት ደግሞ አሉ ያሉት ዶክተር እንዳለው፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ እንዲሁም ምቹ የመማሪያ ክፍሎች እንደሚያስፈልጉ ይናገራሉ። የወላጆች የነቃ ተሳትፎም የግድ ነው፤ ወላጆች ስለልጆቻቸው ጉዳይ ከትምህርት ቤቱ ጋር በጋራና በቅንጅት መስራት መቻል አለባቸው። ይህ ካልሆነ ውጤታማ መሆን እንደማይቻልም ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዋናው አሁን መሰራት ያለበት በትምህርት አመራሩ፣ በመምህሩ ብቃት፣ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ በተማሪዎች ተሳትፎ ላይ እና በወላጆች ተሳትፎ ላይ ነው። ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት በጣም ዝቅተኛ ነው። ጥቂት የማይባል መምህር ደግሞ ተማሪውን ውጤታማ አደርጋለሁ የሚል ሞራል የለውም። የዚህ ምክንያት ደግሞ በቂ ደመወዝ እየተከፈለው አለመሆኑ ነው። ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች ለማሻሻል ከተሰራ በትክክል ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።

እንደ ዶክተር እንዳለው ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያለው ትምህርት የሚመራው በክልሎች ነው። የፌዴራል መንግሥት ፖሊሲና እስትራቴጂ ከማውጣት ባለፈ በክልሎች ስልጣን ላይ አይገባም፤ ዋናው የትምህርት እርከን ደግሞ ይህ ነው። ስለዚህ ክልሎች ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል።

የትምህርት ቤቶች ከባቢያዊ ሁኔታ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ወሳኝ ነው የሚሉት ዶክተር እንዳለው፤ አዋኪ ከሆኑ ነገሮች የፀዱ ናቸው ወይ የሚለውን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል። ከትምህርት ጋር በፍጹም አብሮ መሄድ የማይችሉ ነገሮች የትምህርት ቤቶችን ዙሪያ ሞልተዋል። እነዚህን ሁኔታዎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ የመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ማስወገድ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ የምናስበው ውጤት ሊመጣ አይችልም ይላሉ።

በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት ያደረገው ጥራት ላይ አልነበረም። በወቅቱ ተደራሽነት ስላልነበረ ይህንን ለመፍታት ሰፊ ሥራዎች ተሰርተው በትምህርት ቤቶች ብዙ ሀብት ወጥቷል። ነገር ግን የጥራቱ ጉዳይ የተዘነጋ እንደነበር ተናግረዋል። አሁን በዚህ ረገድ ጅምር ጥረቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ተደራሽነቱን እና ጥራቱን ደግሞ አንድ ላይ ማስኬድ ከባድ እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር እንዳለው፣ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ጥራት የለም ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል። የተደራሽነቱን ያህል ጥራት ማምጣት አልተቻለም። ለዚህ ምክንያቱ የተማሪው ቁጥር ብዙ መሆኑ አንዱ ነው። ይህን ሁሉ ተማሪ በክህሎትም በእውቀትም ብቁ ለማድረግ ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም።

ዶክተር እንዳለው እንደሚገልጹት፤ አሁን የምንሰራው ነገር በዘለቄታ ምን ውጤት ያመጣል የሚለውን ከግምት ማስገባት ይገባል። ወደኋላ የሚመልሰን እንዳይሆንም መጠንቀቅ አለብን። በተመሳሳይ ተደራሽነቱንም የሚገታ እንዳይሆን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ሆኖ ወደ ሥራ ቢገባ ውጤታማ ያደርጋል ይላሉ። በአጠቃላይ በለሙያዎቹ እንዳነሱት፤ ዛሬ ዓለምን የሚመሩ ሀገራት እንዴት አደጉ ብለን ብንጠይቅ መነሻቸው ትምህርት ነው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርት ሀገርን የሚለውጥ መሣሪያ መሆኑን በእርግጥ ተገንዝቦ የትምህርት ጥራት ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ መሥራት አለበት ብለዋል። የተጀመሩ የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ሥራዎች ወደ ኋላ እንዳይንሸራተቱ ክትትል ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You