ከሳምንት በፊት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ወሰን አካባቢ የሚገኝ አንድ አነስተኛ ሆቴል ገባን፡፡ ገብተንም ምግብ አዘዝን፡፡ ማወራረጃውንም ተጠቀምን፡፡ በመጨረሻም አስተናጋጇን ሒሳብ ሥሪልን አልናት፡፡ ደረሰኝ ስንጠብቅ መጥታ ሒሳቡን ነገረችን፡፡ በርግጥ እንዲህ ዓይነት ነገር ብዙ ጊዜ አጋጥሞኛል፡፡
የነገረችን ሒሳብ ከተጠቀምነውም ሆነ ከቤቱ አንፃር የተጋነነ ሆነብን፡፡ ብሩን ከሰጠናት በኋላ፤ ‹‹ይሄኛው ይህን ያህል ቢሆን፣ ይሄኛው ይህን ያህል…›› እያልን የተጠቀምነውን ደመርነው፡፡ ሌላ ቦታ ከምናውቀው አንፃርም ሆነ ከወቅቱ ተለዋዋጭ የዋጋ ሁኔታ ጋር አገናዝበን ስንደምረው ከከፈልነው ሒሳብ ጋር ተራራቀ፤ ቤቱም ያን ያህል የተለየ የሚባል አይደለም፡፡ እኔ አንዴ ሆኗል ብዬ ዝም ብልም ጓደኛዬ ግን አላስቻለውምና አስተናገጇን ድጋሚ ጠራት፡፡ ‹‹ደረሰኝ አምጭልን›› አላት፡፡ ችግሩ ግን ቤቱ ደረሰኝ አልነበረውም። ‹‹ደረሰኝ የለንም›› ስትል እኔም ነገሩ አላማረኝምና ‹‹እንዴት ይህን የሚያክል ቤት ያለ ደረሰኝ ይሠራል?›› አልኳት። ምክንያቱ እሷም አልገባትም መሰለኝ ባለቤቱን ልጥራላችሁ አለችን። እኛም ቢመጣም ምናልባት ተበላሽቶብን ነው ወይም አዲስ ስለሆንን ነው ከማለት ያለፈ ምንም አይለንም ብለን በቸልተኝነት ተይው ብለናት ወጣን፡፡
አሁን ግን ሳስበው ግዴለሽ መሆናችን ልክ አልነበረም፡፡ በእንዲህ ዓይነት ግዴለሽነት ነው ሕገ ወጥ አሠራሮች የሚለመዱት፡፡ በተናጠልም ሆነ እንደ ሀገር ጉዳታቸው እየተለመደ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ የእንዲህ ዓይነት ትንንሽ ግዴለሽነቶች ናቸው ትልልቅ ጥፋቶችን የሚፈጥሩት፡፡ አንድ ገጠመኝ ልጨምርና ወደ ጥቅል ትዝብቴ ልሂድ፡፡ በአንድ ወቅት መገናኛ አንድ ካፌ ውስጥ ሦስት ሆነን የሚበላ ነገር አዝዘን በላን፡፡ ሒሳቡን የከፈለው አንደኛው ልጅ ብቻ ስለሆነ ሁለታችን ሒሳቡንም መልሱንም ልብ አላልነውም፡፡ የሰጣት የሁለት የሁለት መቶ ብር ኖቶች ነበር፡፡ በሒሳቡ መሠረት መልሱ ውስጥ መቶ ብር መኖር ነበረበት፡፡ ልጁ ከመቶ ብር በታች ያሉ የ10 ብር ኖቶችን ከመልስና ደረሰኝ ማምጫ ማህደሩ ውስጥ ካወጣ በኋላ መልሱ ልክ አለመሆኑ ገባው፡፡ ወዲያውኑ ጠርቶ 100 ብር አስጨመራት፡፡
ሊያጋጥም የሚችል ስህተት ነው በሚል ልብ አላልነውም ነበር፤ በኋላ ግን አብረውን የነበሩት ሁሉ እንዲህ አይነት ማጭበርበሮች የተለመዱ መሆናቸውን ገጠመኞቻቸውን እያነሱ ነገሩን፡፡ ሰዎች መልስ ሲያነሱ ልብ አይሉትም በሚል ሆን ብለው ያደርጋሉ ይባላል። የሁለት መቶ ብር ኖት ደግሞ ለዚህ መዘናጋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በርግጥ ስህተት አያጋጥምም አይባልም፤ ሁላችንም እንሳሳታለን፡፡ ዳሩ ግን ሆን ተብለው የሚደረጉ ካሉ ግን በቤቱ ውስጥ እምነት ማሳጣት ነው፡፡ ለአስተናጋጆችም ቢሆን ጉርሻ ጭምር የሚያሳጣ ይሆናል፡፡ መልሱን ልብ ሳይሉ ያነሱታል በሚል መጓጓት ውስጥ ከገቡ ችግር ነው፤ ምክንያቱም ልብ የሚል ደንበኛ ከተገኘ ተሳስታ ነው ብሎ በየዋህነት ከሚያስበው ይልቅ ሆን ብለው ለማጭበርበር ነው ብሎ የሚጠራጠረው ይበዛል፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይም ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡
ወደ ደረሰኞች እንሂድ፡፡ በብዙ የአገልግሎት (ሰርቪስ) ቤቶች ‹‹ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሒሳብ አይክፈሉ›› የሚሉ ማሳሰቢያዎችን በየግድግዳው ላይ እናያለን፡፡ ሆኖም ግን ደረሰኝ ባይቀበሉም ሒሳብ ይክፈሉ እየሆነ ነው፡፡
በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 19(3) መሠረት የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ማንኛውም ግብር ከፋይ ደረሰኝ እንዲሰጥ ይገደዳል። ካለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ የወንጀል ቅጣቱ በሕግ ተደንግጓል፡፡
የግብር ከፋይነት ደረጃቸው ባይታወቅም፣ መቼም እነዚህ ካፌዎችና ሆቴሎች ግብር ከፋይ አይሆኑም ተብሎ አይገመትም፡፡ በርግጥ የግብር ከፋይነት ደረጃ የሚተመነው በቤቱ ዓይነትና ስም ሳይሆን በካፒታላቸው መጠን እንደሆነ ባለሙያዎች ይነገራሉ፡፡ ምናልባት ደረሰኝ የማይሰጡ ቤቶች የደረጃ ሐ ግብር ከፋይ ከሆኑ ደረሰኝ ለመቁረጥ ላይገደዱ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ዳሩ ግን የደረጃ ሐ ግብር ከፋይ ከሆነና ደረሰኝ ከሌለው ግን በዚያ ልክ የተጋነነ ዋጋ ሊያስከፍል አይገባውም፡፡ ስለዚህ ገና ለገና ደረሰኝ የለንም ብለው ያጭበረብሩበታል ማለት ነው፡፡
ተገልጋዩ የሚያየው የቤቱን ሁኔታ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ በርግጥ የሚሰጡት አገልግሎትም ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ከግብር ከፋዮች በላይ ማስከፈል ደግሞ ዝርፊያ ነው ማለት ነው፡፡ ዋናው ችግር ግን ምናልባትም ደረሰኝ መቁረጥ የሚገባቸው ሆነው ማንም አስቦት ሊጠይቀን የሚችል የለም በሚል እያጭበረበሩበት ነው፡፡
አንድ የንግድ ቤት ፈቃድ አውጥቶ ሥራ ሲጀምር መሟላት ያለባቸውን ሕጋዊ ሁኔታዎች አሟልቶ ነው፡፡ ምናልባት ግዴለሽ ያልሆነ ሰው ቢያጋጥማቸው ሊቀጡ ወይም ንግድ ቤታቸው ሊዘጋባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ለትንሽ ማጭበርበር ብለው ትልቅ ኪሳራ ውስጥ ሊገቡ አይገባም፡፡ ምናልባትም ሆን ብለው ለማጭበርበርም ላይሆን ይችላል፤ በግዴለሽነት ከሆነም፣ በተራ ግዴለሽነት ኪሳራ ላይ መውደቅ የለባቸውም፡፡
ግዴለሽነት ብቻ ነው ብሎ ለመገመት ግን ይከብዳል። ምክንያቱም የሚያስከፍሉት ሒሳብ ደግሞ የተጋነነ ነው። የተጋነነ ሒሳብ ክፈል የተባለ ሰው ደግሞ ደረሰኝ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አስተማማኙ ደረሰኙ ነው፡፡ ገና ለገና የኑሮ ውድነቱ በየዕለቱ ይጨምራል ተብሎ መሆን ካለበት በላይ መሆን የለበትም፡፡ ደረሰኝ አለመቁረጣቸው ሳያንስ የተጋነነ ዋጋ ማስከፈላቸው እንደ ግለሰብም፣ እንደ ሀገርም እያከሰሩ ነው፡፡
ብዙዎቻችን ሕጋዊ መብቶችን የመጠየቅ ችግር አለብን፡፡ ይሉኝታ እንዳለ ሆኖ በብዛት ግን ግዴለሽነት ነው፡፡ ከአገልግሎት ሰጪው ቤት ግድግዳ ላይ ‹‹ደረሰኝ ሳይቀበሉ አይክፈሉ›› የሚል ጽሑፍ እናያለን፤ ችግሩ ግን ጽሑፉን እንደማንኛውም የግድግዳ ላይ ጥቅስ እንጂ እንደ ሕጋዊ ግዴታ እያየነው አይደለም፡፡
ለመሆኑ ግን አንድ ትልቅ ቤት ያለ ደረሰኝ የተጋነነ ሒሳብ የሚጠይቀው በምን ድፍረት ይሆን? ተገልጋዩ ዜጋ መብቱን የማይጠይቅ ግዴለሽ ነው በሚል መተማመን ይሆን ወይስ ቢጠይቅም የመጣው ይምጣ በሚል ይሆን?
ከዚሁ ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ካፌዎች የምታዘበው ነገር ደግሞ፤ ደረሰኝ በእጅ ጽሑፍ የሚሰሩ አሉ፡፡ ምክንያታቸው መብራት ጠፍቶ ነው የሚል ነው። ችግሩ ግን ለማጭበርበር ስለሚያመች በተደጋጋሚ የሚጠቀሙትም እንዳሉ ነው ቅሬታ የሚነሳው፡፡ ለማጭበርበር ብለው የሚያደርጉ ካሉ፤ አንዱ ደፋር የጠየቃቸው ዕለት ጉድ ይፈላል፡፡ ለምሳሌ፤ በዚያ አካባቢ መብራት አለመጥፋቱን ካወቀና መብራት ሳይጠፋ በእጅ ጽሑፍ ከቆረጡ የምርም እያጭበረበሩ ነው ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ ሕጋዊ ግዴታዎችን የመጠየቅ ልምድ ይኑረን፡፡ ይህን የምለው ራሴን ጭምር ተወቃሽ በማድረግ ነው፡፡ እንደ ሀገር ያለውን ሁኔታ የሚቀይረው የግለሰቦች ጥረት ነውና ሕግ አክባሪም አስከባሪም እንሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም