-ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር
ኢትዮጵያ መልከ ብዙ የሆነች ሀገር ነች። ብሔርን፣ ቋንቋን ፣ ባሕልን፣ ሃይማኖትን፣ አስተሳሰብን፣ የአኗኗር ሥርዓትን እና ሌሎች ብዝሀነትን አቻችላ ለዘመናት ኖራለች። ያም ሆኖ በሕዝቦች አብሮ የመኖር ሂደት ውስጥ የተፈጠሩና ወደፊትም ቢሆን ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች መከሰታቸው የማይቀር ነው። የአንድ ሀገር ሕዝቦች የሚግባቡባቸው የጋራ ጉዳዮች እንዷላቸው ሁሉ የሚለያዩባቸው አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ይኖራሉ።
ሕዝቦች ልዩነታቸውን አጥብበው አንድነታቸውን ቢያጠናክሩ ሰላምና ደህንነታቸውን አጽንተው እድገታቸውን ሊያፋጥኑ እንደሚችሉ ይታመናል። ኢትዮጵያ ዛሬ ወደኋላ እንድትጎተት፤ ሕዝቦቿ ተግባብተው እንዳይኖሩና እርስ በእርሳቸው በጥርጣሬ ዓይን እንዲተያዩ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ የበዳይና የተበዳይነት ስሜት ነው። ይህን ስሜት ማጥራት፣ መተማመንና መግባባት የሻከረውን የሕዝቦች ግንኙነትም ይሁን የሀገርን ሕመም የሚያክም እንደሆነ በጽኑ ይታመንበታል።
ይህን መነሻ በማድረግና ከዓለም ተሞክሮ በመውሰድ የዛሬ ሶስት ዓመት አካባቢ በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል። አስራ አንድ ገለልተኛ አባላትን ያቀፈው ይህ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ተልዕኮውን ለመፈጸም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቶ ወደ መጨረሻዎቹ ምዕራፎች ተቃርቧል። ኮሚሽኑ እስከ ዛሬ ያከናወናቸውን የሥራ ሂደቶችና ቀጣይ እቅዶቹን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ ጋር ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡– የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሶስት ዓመታት ቆይታ እንዴት ነበር? ምን ምን ተግባራትን ሲያከናውን ቆየ?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– በኢትዮጵያ ታሪክ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሲቋቋም ይህ የመጀመሪያው በመሆኑ እንደ ሀገር በምሳሌነት የሚጠቀስ ልምድና ተሞክሮ አልነበረም። ኮሚሽኑ የዛሬ ሶስት ዓመት አካባቢ ሥራውን አንድ ብሎ ሲጀምርም ከሀገራዊ መግባባት አንጻር በዓለም ላይ የተሠሩ ሥራዎችን መለስ ብሎ ማየትን፣ መቃኘትንና ማጥናት ቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ ነው ወደ ሥራ የገባው። የምክክሩን ዲዛይን ከመሥራታችን በፊት ምን ዓይነት ምክክር ይደረግ? ማንን የሚያካትት ይሁን? ምን ዓይነትን ሂደትን ይከተል? የሚለውን ለመወሰን ኮሚሽኑ የእያንዳንዱን ክልል አውድ ለማጥናት ሞክሯል። ከክልሎች የተገኙ መረጃዎችን በመጭመቅና በመቀመር አሠራሮችን ዘርግቶ ወደ ሥራ ገብቷል።
አውድ በማጥናቱ ሂደትም ሕዝቡን እና ባለድርሻ አካላትን የማሳተፍና የማወያየት ሥራ ተሠርቷል። ምንድነው ከዚህ ምክክር የምትጠብቁት? ሀገራዊ ምክክሩ በምን መልክ ቢካሄድ ይበጃል ትላላችሁ? እናንተ ባላችሁበት አካባቢ ወይም ክልል መካተት አለባቸው የምትሏቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? ምን ምን ጥያቄዎች አሏችሁ? እነዚህን እና መሰል ነጥቦችን በማንሳት አውዱን መረዳት ተችሏል።
የየክልሉ ማህበረሰብ ክፍሎች እንዴት ሊወከሉ እንደሚችሉ፣ በየትኛው የአስተዳደር ደረጃ ሥራችንን መጀመር እንዳለብን አስቀድመን በመነጋገር ነው ወደ ሥራ የገባነው። ለምሳሌ አካታች እንዲሆንና የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት እንዲሆን በወረዳ ደረጃ ያሉ ተሳታፊዎችን ማካተት ወሳኝ ነው። ያሉትን ወረዳዎች መረዳት፤ ከነዚህ ወረዳዎች መካተት ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የትኞቹ እንደሆኑ መለየት፤ ተሳታፊዎችን የሚመርጠው ኮሚሽኑ ሳይሆን ማህበረሰቡ ራሱ እንዲሆን ማድረግ፤ የሚሉት አስቀድመው ተሠርተዋል።
ይህንን ሥራ ያግዙናል ያልናቸውን ተቋማት የመለየትና በየወረዳው የመረጣውን ሂደት እንዲያግዙ ማድረግ ተችሏል። በዚሁ መሠረት የአካባቢው እድር ኃላፊዎች፣ አስተማሪዎች፣ የሴቶች ማህበራት፣ የወጣት ማህበራት፣ ማህበረሰቡ የተለየ ከበሬታ የሚሰጣቸው ሰዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተባባሪ አካል ተደርገው ከተካተቱ በኋላ ከእያንዳንዱ ወረዳ የሚመረጠውን የተሳታፊ መረጣ ሂደት እንዲመሩ ተደርጓል።
በዚህ ሂደትም ኮሚሽኑ ክትትል እያደረገ እና አቅጣጫ እየሰጠ በጥሩ ሁኔታ እንዲከናወን አድርጓል። በአሁን ሰዓትም ከትግራይ እና አማራ ክልል ውጭ የተሳታፊዎች መረጣ ተከናውኗል። በአማራ ክልል ተባባሪ አካላት ተቋቁመው ስልጠና ወስደው ሥራ ለመጀመር ዝግጁ ሆነው እየጠበቁ ይገኛሉ።
የትግራይ ክልል አመራሮች በምክክሩ አስፈላጊነት በጽኑ የሚያምኑ ቢሆንም ክልሉ ቀደም ሲል ከነበረበት ሁኔታ አንጻር ሌሎች ፈጣን ምላሽ በሚፈልጉ ማህበራዊ ችግሮች ላይ የተጠመዱ በመሆናቸው እስከ አሁን ድረስ በሌሎች ክልሎች የተሠሩ ሥራዎችን ማከናወን አልተቻለም። በቀጣይ ግን ተመሳሳይ ሥራዎችን እንሠራለን ብለን እናምናለን።
የምክክሩ ተሳታፊዎች ከተመረጡ በኋላ ያከናወነው ሌላው ሥራ አጀንዳ ማሰብሰብ ነው። ወደ አብዛኛዎቹ ክልሎች በመሄድ ማህበረሰቡ ዛሬ ኢትዮጵያን እያወዛገባት ያለው እና ልንግባባባቸው የልቻልንባቸው አጀንዳዎች እነዚህ ናቸው ብሎ ወስኖ እንዲሰጥ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።
ይህ ሂደት ማህበረሰቦች ተመካክረው ፣ ተግባብተውና ተማመነው ክልላችን በዋናነት በምክክሩ ሂደት በነዚህ ጉዳዮች ላይ እንዲነጋገር እንፈልጋለን ብለው ያመኑበትን አጀንዳ የሚሰጡበት ነው። የአጀንዳ ማሰባሰቡ ሥራ ከሶስት ክልሎች ማለትም ከኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች ውጪ በሌሎቹ ክልሎች ተከናውኗል። በኦሮሚያ ክልል ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ ስለተፈጸመ በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የክልሉ የምክክር ሥራ የሚከናወን ይሆናል። በቀጣይም በአማራ ክልል ተመሳሳይ ሥራ እንሠራለን ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡– ኮሚሽኑ እነዚህን ሥራዎች ሲያከናውን ያጋጠሙት ችግሮች ነበሩ? ካሉስ እንዴት ማስተካከል ተቻለ?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– በአንዳንድ ቦታዎች ካለው የቦታ ስፋት አንጻር መጠነኛ የሎጂስቲክ እጥረት ከማጋጠሙ ውጭ ምንም ዓይነት ችግር አላጋጠመንም። በሄድንባቸው ክልሎች ሁሉ ፊቴ ላይ የሚደቀነው የሕዝቡ ጉጉት ነው፤ ሕዝቡ ይህ ምክክር እውን እንዲሆን ያለው ፍላጎትና የጣለብን አመኔታ በጣም የሚደንቅ ነው። ምንም እንኳን ሥራውን ለመሥራት ቁርጠኞች ብንሆንም የበለጠ ግን የሕዝቡ ጉጉት ውስጣችንን ነክቶናል። በሄድንባቸው ቦታዎች ሁሉ ይደረግልን የነበረው አቀባበልና ይሰጠን የነበረው አስተያየት እጅግ በጣም ገንቢ ነው። ለዚህም ሕዝቡንም ይሁን ባለድርሻ አካላትን በኮሚሽኑ ስም ማመስገን እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በመርሃ–ግብራችሁ መሠረት ሥራችሁን በሶስት ዓመት ውስጥ እንደምታጠናቅቁ አሳውቃችሁ ነበር፤ አሁን የቀራችሁ ሁለት ወር ነው፤ በዚህ አጭር ጊዜ የተቀረውን ሥራ ማከናወን ትችላላችሁ? ወይስ እቅዳችሁን ታራዝማላችሁ ?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ታሪክ ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት የምክክር ሂደት ተከናውኖ አያውቅም፤ ይህ በጣም ታሪካዊ አጋጣሚና የማይገኝ እድል ነው፤ ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀም ስለሚያስፈልግ በጥንቃቄ ልንይዘው ይገባል። ከዚህ አንጻር የኮሚሽኑ አባላት የተሸከምነው ኃላፊነት ከፍተኛ ነው ብለን ስለምናምን በጣም አሳታፊ ለመሆን ሞክረናል፤ በጥንቃቄ ለመጓዝም ጥረናል፤ ይህን ሁሉ ስናደርግ ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲቪል ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ እና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላት እያሰባሰብን፤ እያመካከርን፤ የሠራነውን እያሳወቅን፤ ከእነርሱም ግብዓት እየወሰድን ነው።
ይህ የሥራ ሂደት፣ የሀገሪቱ ስፋትና የሕዝቡ ብዛት ተደማምሮ ጊዜ ወስዷል። ኮሚሽኑ ሠርቻለሁ ለማለት ብቻ የችኮላ ሥራ መሥራት አይፈልግም፤ ውጤታማ የመሆን ጉጉት ስላለው እያንዳንዱን ሥራ በጥንቃቄ ለመምራት ተገድዷል፤ አብዛኛውን ባለድርሻ አካላት አሳታፊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት የሥራ ሂደት አድርጓል፤ ባለድርሻ አካላትን ለማነጋገር እና በየአውዱ አካታችነትን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት፣ የሌሎች ፕሮግራሞች መደራረብ መርሃ ግብሩ በእቅዱ መሠረት እንዳይሄድ ጊዜ ወስደዋል። ጊዜ መውሰዱ ግን ኮሚሽኑ የሚያኮራ ሥራ እንዲሠራ እድል የሰጠ በመሆኑ አናፍርበትም።
በማንኛውም መለኪያ አካሄዳችን ቢፈተሽ ተገቢውን ምርጫ እንዳደረግን የሚመሰክር ነው፤ አሁንም የክልላዊ ምክክሮችን እና ክልላዊ የአጀንዳ አሰጣጥ ሂደቶችን ለመጨረስ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነን። በአብዛኛዎቹ ክልሎች አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራ የተከናወነ ሲሆን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በኦሮሚያ እና በአማራ ቀሪ ሥራዎችን የምናጠናቅቅ ሲሆን፤ በመቀጠልም በትግራይ ክልል እንቅስቃሴ የምንጀምር ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ከማሳተፍ አንጻር የታሰቡ ወይም የተሠሩ ሥራዎች ይኖሩ ይሆን?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– አዎን ከሀገር ውስጥ የምክክሩን ተሳታፊዎች ከለየን በኋላ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የመሳተፍ ሥራም ይሠራል። ከዚህ ቀደም አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና በሌሎች አህጉሮች ከሚኖሩ ዲያስፖራዎች ጋር ብዙ ንግግሮችን አድርገናል። በዚህም ሥራችንን አሳውቀናል፤ በምን መልክ መሳተፍ እንደሚፈልጉ ጠይቀናል፤ አጀንዳቸውን እንዲሰጡን አሁንም በራችንን ክፍት አድርገንላቸዋል። በሚቀጥለው ሂደትም በምን መልክ ተወካዮቻቸውን እንደሚልኩና እንደሚያሳተፉ ተነጋግረን ተግባራዊ የምናደርግ ይሆናል። ማንም ሰው በግለሰብ ደረጃም ይሁን በማህበር ደረጃ አጀንዳ መላክ ይችላል። ይህ ሁሉ የአጀንዳ አሰባሰብ መጨረሻ ላይ በሀገር ደረጃ ለሚቀረጸው አጀንዳ ግብዓት ያደርጋል የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፡– በሰላማዊ መንገድ ትግል እናደርጋለን ከሚሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አንዳንዶች በዚህ ሀገራዊ ምክክር የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው ይገልጻሉ፤ እነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀረብ ብላችሁ በማነጋገር ወደ ሰላማዊ ንግግሩ እንዲመጡ ምን ዓይነት ጥረት አድርጋችኋል? አሁንም ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ምን ምክር መስጠት ትፈልጋላችሁ?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– ኮሚሽኑ ይህንን ኃላፊነት ተረክቦ ሥራ እንደጀመረ ሰሞን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በገለልተኝነታችን እና በተዓማኒነታችን ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ ገብተው ነበር። ሌላው ቀርቶ በኮሚሽኑ እንድንካተት የተደረገበትን አግባብ ለማመን ይቸገሩ ነበር፤ እውነታው ግን እነርሱ እንደሚያስቡት አይደለም።
ሁላችንም ቢሆን እዚህ ኮሚሽን ውስጥ እንድንካተት የተደረገው በራሳችን ፍላጎት ወይም በመንግሥት አካላት ምርጫ ሳይሆን መስፈርቶችን ያሟላሉ በሚል በሰዎች ጥቆማ እንደተመረጥን ነው የምናውቀው። ሁላችንም አንተዋወቅም፤ እንግዲህ ገለልተኝነታችን የሚታወቀው በምንሠራው ሥራ ነው። እስከ አሁን ምን ሰርተዋል? አካሄዳቸው ምን ይመስላል? የሚለውን ተመልክቶ ነው አመኔታ ማሳደር ወይም ጥርጣሬ መፍጠር የሚቻለው።
በርግጥ መጀመሪያ አካባቢ ከኮሚሽኑ ጋር ለመሥራት ፍላጎት የነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛታቸው 40 የሚደርስ ብቻ ነበር፤ ከዚያ በኋላ የኮሚሽኑን ሥራ በመከታተልና በመገምገም ራሳቸውን አግልለው የነበሩ ትላልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በአሠራራችሁ አመኔታ አሳድረናል እያሉ አብረውን መሥራት ጀምረዋል። በአሁኑ ሰዓትም አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እየሠሩ ይገኛሉ። በጣም ጥቂት የሆኑት ግን አሁንም ወደ እኛ መካተት አልፈለጉም።
በእኛ በኩል በተደጋጋሚ ጥሪ ስናቀርብላቸው ከርመናል፤ በአካልም ተገኝተን ስለጉዳዩ አነጋግረናቸዋል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የትጥቅ ትግል የጀመሩ አካላት በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ አሁንም ድረስ እየጋበዝናቸው እንገኛለን። መሳተፍ ያልፈለጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮሚሽኑ ገለልተኛ ሆኖ ሀገራዊ ችግሮች በምክክርና በውይይት እንዲፈቱ የሚያደርገውን ትክክለኛ ሂደት እየተረዱ ሲመጡ በመጨረሻው ሰዓትም ቢሆን ሊቀላቀሉን ይችላሉ ብለን እንገምታለን።
ሂደቱን ቀረብ ብለው ሳያዩ ከሩቅ ሆነው አላምነውም ማለት ተገቢ አይደለም። አሳማኝ የሚሆነው ተጠግቶ ፈትሾ ወይም አብሮ ሰርቶ እንዲህ ዓይነት ችግር አለበት እና አብሬ መቀጠል አልችልም ማለት ሲቻል ነው። በተለይም ሰላማዊ ትግል ነው የምንታገለው ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲህ ዓይነት የምክክር መድረክ ማግኘታቸው ዓላማቸውን ሊያሳካላቸው ይችላል።
ኮሚሽኑ በሰላማዊ መንገድ ትግል ለሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን የትጥቅ ትግል ውስጥ ለገቡትም ጭምር ጥሪ አድርጓል። ደህንነታቸው ተጠብቆ ምንም ዓይነት ሥጋትና ጥርጣሬ ሳይኖራቸው መጥተው ተነጋግረው እንዲሄዱ መልእክት አስተላልፈናል። ከዚህ አንጻር ከመንግሥትም ጋር ተነጋገረን ፈቃደኝነቱን ገልጾልን በማስ ሚዲያ አሳውቀናል። ምንም ዓይነት የደህንነት ሥጋት ሳይኖርባቸው መጥተው መሳተፍ እንደሚችሉ፤ ሥጋትም ካደረባቸው ይሄንን የሚያመቻቹ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስላሉ በእነርሱ አማካኝነት ተሳትፈው አለን የሚሉትን ጥያቄ በምክክር እንድንፈታው ጥሪ አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡– በሚዲያ ጥሪ ከማድረግ ባሻገር በእናንተ በኩል በአካል ተገናኝቶ ለመነጋገር ሙከራ ተደርጎ ነበር?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ቡድኖችን ከሚመሩ አካላት ጋር አሉን በሚሏቸው ጥያቄዎች ዙሪያ በቀጥታ የተነጋገርንበት አጋጣሚ የለም፤ ግን መልዕክታችንን ሊያደርሱልን ከሚችሉ ሰዎችና በየክልሎቹ ከሚገኙ ምሁራን ጋር ከግጭት ይልቅ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረናል።
አሁንም በዚህ አጋጣሚ ለእነዚህ አካላት የማስተላልፈው መልዕክት ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮም ይሁን ከሀገራችን ተሞክሮ መገንዘብ እንደሚቻለው በጦርነት የተፈታ ችግር የለም። ከሀገራችን ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው አለመግባባትን በውይይት መፍታት እየቻልን ብዙ ምሁራንና ወጣቶችን ያጣንባቸው መጥፎ አጋጣሚዎች ያስቆጩናል። እዚህ ሀገር አንድ የተማረን ዜጋ ለማፍራት ኢንቨስት የሚደረገው ገንዘብ፣ ልፋትና ድካም እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። በከፍተኛ ልፋትና ድካም ተምረው ለጥሩ ውጤት የበቁ ብርቅና ውድ ዜጎች ተነጋግረን መፍታት በምንችለው የፖለቲካ ጉዳይ ሲሞቱ ለቤተሰብም ይሁን ለሀገር ምን ያህል የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትል መረዳት አይከብድም። ወደ ትጥቅ ትግል አስገብተውናል እና አላግባቡንም የሚሏቸውን ጉዳዮቻቸውን ቁጭ ብለው በመመካከር ሊፈቱ የማይችሉበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። በምክክር መድረኩ የሚሰበሰቡትን የኢትዮጵያ ተወካዮች የሚያሳምን ጉዳይ ካላቸው፤ መጥተው በማሳመን ውሳኔ ማግኘት ይችላሉ።
ችግርን በውይይትና በሰለጠነ መንገድ መፍታት በሚቻልበት በዚህ በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ወጣትነታቸውና እድሜያቸው ግብታዊ የሚያደርጓቸውን ልጆች እያነሳሱ ማስፈጀት አይጠቅምም። የመነጋገር እድል ባይኖር እና በሮች ሁሉ የተዘጉ ቢሆን እንኳ በሩን ለማስከፈት ማንኳኳት ያስፈልጋል እንጂ ፤ ጦርነትን መፍትሔ ማድረጉ አይጠቅምም።
ማህበረሰባችን በተለያዩ ጨቋኝና አምባገንን ሥርዓቶች ውስጥ ሲያልፍ የኖረ ነው፤ ከዚህ የተነሳ የሚነገረውን ከማመን ይልቅ ይጠራጠራል። እውነት ለመናገር የኮሚሽኑ አባል ሆነን የተመረጥን ሰዎች በዚህ ጉዳይ እጃችንን ያስገባነው በሀገራችን ጉዳይ ያገባናል፤ ሕዝብ አምኖብን ኃላፊነት እስከሰጠን ድረስ ከእኛ የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት አድርገን የሀገራችንን ሰላም እናስጠብቃለን፤ የሕዝባችንን አንድነትና ፍቅር እናጸናለን በሚል እምነት ነው። ይህን ሃሳብ እውን ለማድረግ በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እስከ ዛሬም ድረስ በየትኛውም አካል ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አልደረሰብንም፤ እንደውም አይዟችሁ! በርቱ! ከጎናችሁ አለን! የሚሉን በርካቶች ናቸው።
ስለሆነም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የመጀመሪያው የሥነ ልቦና ዝግጅት አሉን የምንላቸውን ችግሮች ተነጋገሮ የመፍታት ፍላጎት ማሳደር ነው። አሉን የምንላቸው ችግሮች እንዲቆዩ የምንፈልግ ከሆነ ግን እንዲህ ዓይነት የውይይትና የምክክር አጋጣሚዎችን የመጠቀም ፍላጎት አይኖረንም። የእውነት ችግሩ እንዲፈታ የምንፈልግ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው እንዲህ ዓይነት እድሎችን የማንጠቀማቸው? ከዚህ የተሻለስ በምን ዓይነት መንገድ ነው ልንፈታቸው የምንችለው? አስፈላጊ ከሆነም እኮ መጥተው፤ ተነጋግረው፤ መግባባት ላይ መድረስ ካልቻሉና ጥያቄያቸው በሚያረካ መንገድ ካልተመለሰላቸው ተመልሰው ወደ ጫካ ወይም ወደነበሩበት እንዳይሄዱ የሚከለክላቸው ነገር የለም። የምክክር መድረኩ እስከዚህ ድረስ ነፃነት የሚሰጥ እንጂ ከዚህ ሃሳብ ውጭ ንቅንቅ እንዳትሉ የሚል አለመሆኑ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል።
ስለሆነም ይህንን እድል አለመጠቀም ወደፊት የሚያስቆጭ በመሆኑ በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት የሌላቸው ነገር ግን ሰላማዊ ትግልን ምርጫቸው ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ በትጥቅ ትግል ውስጥ የገቡ አካላት ቆም ብለው በማሰብ ይህን ተመራጭ መንገድ ሊመለከቱት ያስፈልጋል። አሁንም ቢሆን አሉን የሚሏቸውን ጉዳዮች ወደ ምክክር መድረኩ ይዘው በመቅረብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ቁጭ ብለው መክረውባቸው እንዲወስኑባቸው ጥሪ አስተላልፋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የምክክር ኮሚሽኑ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤትና በሲቪክ ማህበራት እንዴት እየታገዘ ነው? እንዴትስ ይታገዝ ይላሉ?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– ኮሚሽኑ ይህንን ግዙፍ ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ሆኖ እንዲተረጎም በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ግን ይህ ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የሌሎች ባለድርሻ አካላትም እገዛ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የምክክር መርሃ-ግብሩን በተመለከተ ኢትዮጵያ መላው ሕዝቧን ያሳተፈ ምክክር እያካሄደች መሆኗን ሚዲያዎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው በውስጥም ይሁን በውጭ ላሉ ዜጎች ተደራሽ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ሚዲያዎች አልፎ አልፎ ኮሚሽኑ የሚያካሂዳቸውን ሁነቶች ብቻ መዘገብ ሳይሆን ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠትና ቋሚ ፕሮግራም በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን ሊሠሩ ይገባል። የሀገር ጉዳይ የእያንዳንዱ ዜጋ ጉዳይ ስለሆነ ሚዲያዎች ራሳቸው የጉዳዩ ባለቤት ሆነው በየጊዜው ሽፋን በመስጠት ወደ ማህበረሰቡም ሆነ ወደሚመለከተው አካል የማስረጽ ሚናቸውን በመወጣት የኮሚሽኑን ሥራ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል።
ጉዳዩ የኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ ነው፤ ሁሉም ነገር የሚኖረው ሀገር ሲኖር እስከሆነ ድረስ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። ሁሉም ኃላፊነቱን ካልተወጣ ይህ የያዝነው ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ሊደርስ አይችልም።
ምሁራንም በሚያውቋቸው ፣ በሚገምቷቸው እና የኢትዮጵያ ሕዝብን ሳያግባቡ የቆዩት እነዚህ ናቸው በሚሏቸው ነጥቦች ዙሪያ ከስሜትና ከግል ፍላጎት የጸዱ፤ እውነትን፣ እውቀትንና ተጨባጭ መረጃን መሠረት ያደረጉ ጥናቶችን በማጥናት አንዳንድ የሚያወዛግቡ ነገሮችን አብላልተው በማብራራትና ብዥታዎችን በማጥራት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ፤ ኮሚሽኑንም ከዚህ አንጻር ሊያግዙ ይገባል።
እያንዳንዱ ሰው በጉዳዮች ላይ የየራሱ አቋም አለው፤ ያ አቋሙ በዝምድና፣ በዝንባሌ፣ በዘር፣ በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ እንጂ በጥያቄው እውነተኛ መልስ ላይ የተመረኮዘ ላይሆን ይችላል። ህብረተሰቡ እንዲህ ዓይነቱን ኋላቀር አስተሳሰብ ትቶ በእውቀትና በእውነት ላይ የተመሠረተ መረጃ እንዲጨብጥና ራሱን በዚህ መልክ እንዲገነባ ምሁራን እውቀትን የመፈለግ ባሕል ወደ ህብረተሰቡ እንዲሰርጽ አበክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። አሁን በሚያወዛግቡ ጉዳዮች ዙሪያ ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎችን አዘጋጅቶ የማቅረቡ ሥራ ገና አልተጀመረም፤ ፖለቲካውን የሚያግዙ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል።
የሲቪል ማህበራትም ቢሆኑ በሚያምኑባቸውና በወሰዷቸው አቋሞች ላይ ጥናት እያጠኑ ለሕዝቡ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፤ ሕዝብን የማደራጀት ፣ የማንቃት ፣ የማነቃነቅ ሥራ ሊሰሩ ይገባል፤ እያንዳንዱ ግለሰብም ይሁን ተቋም የሚጠበቅበትን ሲያደርግ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ታገዘ ማለት ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ምክር ቤታቸው ስለሀገርና ስለሕዝብ ሰላምና ደህንነት የቆሙና የተመሠረቱ እንደመሆናቸው የሕዝቦች ተግባብቶ መኖርና የሀገር ደህንነት ጉዳይ ያስጨንቃቸዋል፤ በዚያው ልክ መሥራትም ይጠበቅባቸዋል። ቁጭ ብሎ ተመልክችና ተች መሆን ግን ሁሉንም ሰው ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አያደርግም። ኢትዮጵያውያን ትልቁ ችግራችን አንዱ አካል ሲሠራ ሌሎቻችን ተመልካች፣ ታዛቢ እና ተቺ መሆናችን ነው። ይህ አስተሳሰባችን ወደ ችግር እየከተተን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። እውነትን መፈለግ፣ የሌላውን የማህበረሰብ ክፍል ወይም የሀገራችን ዜጋ ቁስል ማዳመጥ ፤ ለመረዳት መሞከር፣ የራስን ብቻ አለመፈለግ የመሳሰሉ ባሕሎች እንዲዳብሩ ሁሉም ሚናውን ሲወጣ ሥራችን ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።
እያንዳንዱ ሰው መረዳት ያለበት ጉዳይ በዚህ ሀገራዊ ምክክር የሚገኘው ውጤት የሚጠቅመው ሁሉንም የሀገሪቱን ዜጎች ነው። ስለዚህ ሥራውን የኮሚሽኑ ብቻ አድርጎ መመልከት አግባብነት የለውም። ሀገራዊ ምክክሩ እውን የሚሆነው የመላው ሕዝብና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሲታከልበት እንጂ ኮሚሽኑ በሚሠራው ሥራ ብቻ አይደለም። ኮሚሽኑ ከእርሱ የሚጠበቁትን እና መሠራት ያለባቸውን ትልልቆቹን ሥራ ያከናውናል፤ እንደ ዜጋ፣ እንደባለድርሻ አካል፤ ሁሉም ኃላፊነቱን ቢወጣ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ይጠቀማሉ።
አዲስ ዘመን፡– ከአጀንዳ ማሰባሰብ በኋላ ቀጣይ የኮሚሽኑ የሥራ ትኩረቶች ምንድን ናቸው?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– ከተለያዩ ክልሎች የተሰበሰቡት አጀንዳዎች ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ ነው፤ በተለይም ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሰበሰቡት አብዛኛዎቹ አጀንዳዎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ናቸው፤ ክልሎችን በተመለከት የተነሱት ደግሞ እንደየክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ የተለያዩ ናቸው። በቀጣይ እነዚህን የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በመያዝ ከኤክስፐርቶችና ከአማካሪዎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር አጀንዳዎች ይቀረጻሉ ማለት ነው።
በአጠቃላይ ከተሰበሰቡት አጀንዳዎች መሠረታዊ ናቸው፤ ለኢትዮጵያ ፋይዳ ይሰጣሉ፤ የምንላቸውን ጉዳዮች አንጥረን በማውጣት፤ የምክክሩ አጀንዳ እንዲሆኑ እንወስናለን። እነዚህ አንኳር አጀንዳዎች ሲመረጡ የተለያዩ መለኪያዎች ይኖራቸዋል። ለምሳሌ በጣም አጣዳፊና አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ወይም አብዛኛው ሰው ያነሳቸው ጉዳዮች እየተባሉ እንደየ አስፈላጊነታቸው ሊመረጡ ይችላሉ።
በመጨረሻም እነዚህ የተመረጡ አጀንዳዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገራዊ ምክክሩ የሚነጋገርባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ተብለው ለሕዝቡ ይፋ ይደረጋሉ። ከዚህ በኋላ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ይጠራል፤ በጉባዔው ላይ በሚካሄዱት ምክክሮች ጥግ እና ጥግ ወይም ዳር እና ዳር ያሉ ወገኖች ወደ መሃል መጥተው አንዱ የሌላውን ሃሳብ እንዲያዳምጥ፤ አዋቂዎችና ምሁራን መሠረታዊ ማስረጃ ወይም እውነታ ላይ የተመሠረቱ ጉዳዮችን በማቅረብ በምክክሩ ሂደት ተሳታፊዎቹ መግባባት ላይ እንዲደርሱ የማድረግ ፤ ማወቅ ያለባቸውን መሠረታዊ ነገር እንዲያውቁ እገዛ የሚያደርጉበት ሂደት ይኖራል።
እንግዲህ ምኞታችን እና ዓላማችን የተራራቁ አስተሳሰቦች የሚታረቁበት እና አንድ የሚያግባባ ቦታ ላይ ደርሰው ውሳኔ እንዲያገኙ ማስቻል ነው። ይህን ስናደርግ የምክክሩ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን በሙሉ የሚወክሉ የማህበር ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት እንደመሆናቸው ውሳኔው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውሳኔ ይሆናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ከመንግሥት ምን ይጠበቃል?
ኮሚሽነር ሂሩት፡– በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሕግ ማሕቀፍ ኖሯቸው፤ መመሪያና ደንቦች ተቀምጠውላቸው ነገር ግን በዚያው መሠረት የማይከናወኑ አሠራሮች አሉ። እነዚህ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ቅሬታ የሚፈጥሩ ናቸው። ለምሳሌ በሴቶች መብት ጉዳይ ብንመለከት፤ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦቹ ቢኖሩም ሙሉ ለሙሉ ሴቶችን ከማብቃት ወይም ወደ ላይ ከማምጣት አንጻር በበቂ ሁኔታ አይተረጎሙም።
ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም በሚገባው ልክ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ወይ? ብለን ብንጠይቅ ጥሩ ምላሽ ላናገኝ እንችላለን፤ እንዲህ ዓይነቶቹ በሰዎች አፈጻጸም ጉድለት ምክንያት የሚነሱ ቅሬታዎችና ችግሮች ወደ ሀገራዊ ምክክሩ በምናደርገው ጉዞ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
እነዚህ በየተቋማቱ ከአሠራር ጉድለት አንጻር የሚፈጠሩ ሰው ሠራሽ ችግሮች በወጣላቸው አዋጅ ፣ መመሪያና ደንብ መሠረት እዚያው በየተቋሙ ውስጥ መፈታት ቢችሉ በሀገራዊ ምክክሩ እንደ አንድ ሀገራዊ አጀንዳ ተደርገው አይታዩም። ስለዚህ መንግሥት የተቋማትን አሠራር እየፈተሸ ከወዲሁ ማስተካከያ በመስጠት ኮሚሽኑ በሌላ ጉዳይ እንዳይወጠር ማገዝ ይኖርበታል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ይህ ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው ብሎ መከታተል፤ መሳተፍ፤ ሃሳብ ማመንጨት፤ አጀንዳ መላክ፤ ለምክክሩ ሂደት የሚጠቅሙ ሥራዎችን መሥራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡– የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንግዳ ሆነው በዚህ ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ቃለ ምልልስ እንድናደርግ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ!
ኮሚሽነር ሂሩት፡– እኔም አመሰግናለሁ!
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም