«የመምህራን ችግሮች ቢቀንሱም አሁንም መፍትሔን ይሻሉ»

አሁን አሁን ከአለብን የኑሮ ጫናና የሥራ ቅጥር ሁኔታ አንጻር መማር ፋይዳው እንዲታየን አድርጓል። እንደያውም አንዳንዶች የቅንጦት ተግባር አድርገው ሲወስዱትም ይስተዋላል፡፡ በተለይም ኑሮው አልገፋ ያላቸው ሰዎች ‹‹ተምሬ ሥራ የለኝ፤ ተምሬ የሚከፈለኝ ደሞዝ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ስለዚህም ባልማር ይሻለኝ ነበር›› ሲሉም እናደምጣለን፡፡ ባልማር ኖሮ የብዙዎቹ እሮሮ ከሆነም ሰነባብቷል። ምክንያቱም ሳይማር ነጋዴ የሆነውና የተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማራው በኑሮው ሁኔታ ልቆ ተገኝቷል፡፡ ቢሆንም ግን ትምህርትን የሚተካው ነገር እንደሌለ ማንም ያውቀዋል፡፡ በትምህርት ያልዳበረ ልምድ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው እንደሚያመዝንም እሙን ነው፡፡

ይህ ምሬት በአግባቡ መቀየር ከሁሉም የተማረ አካል ይጠበቃል፡፡ በተለይም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ በቀጥታ ወደ ሥራው ዓለም ለመሰማራት የሚነሳው አካል ይህንን በተግባር ገልጦ ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ትምህርት አቅም እንደሆነ ማስረዳትም ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ የትምህርት አውራ የሆነውን መምህር በተለያየ መንገድ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት እንደሆነም የምናረጋግጠው የሁሉም ሙያዎች አባት የሆነውን መምህር ክብርና ሞገስን ስንሰጠው ነው፡፡ ያለበትን የኑሮ ጫና ስናቀልለት ነገሮች እየተስተካከሉ እንደሚሄዱ መቀበል ይገባል፡፡ በተለይም የትምህርት ስብራት ነው ተብሎ የሚጠቀሰው የትምህርት ጥራት ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው መምህሩ ችግሮቹን ሳይሆን ተማሪዎቹን እያሰበ ሲሰራ ነው፡፡ እናም ለዚህ ተግባር እውን መሆን ከግለሰቦች የጀመረ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በርግጥ እንደ ሀገር መምህርን የሚደግፉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ልዩ ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ አድርገው መምህራን እንዲሰሩ የቤት ባለቤት የሚሆኑበት እድል ተመቻችቷል፡፡ ተግባሩ ግን እንደ አካባቢው ሁኔታ ይለያያል፡፡ አንዳንዱ የተሠራ የመኖሪያ ቤት ሲያገኝ፤ ሌላው ደግሞ የመኖሪያ ቤቱን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲከራይ ተመቻችቶለታል፡፡ ይህ ከከበደ ደግሞ ተደራጅቶ የሚሰራበትን ሁኔታም ተፈጥሮለታል። እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሉት ደግሞ ሁሉንም አማራጮች ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ ምክንያቱም በከተማዋ ያለው የመኖሪያ ቤት ችግር ለመምህሩ ብቻ ሳይሆን ለከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይም የሚቻል አይደለም፡፡

በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ የመምህራን ጉዳይ ያገባኛል ከሚለው አካል ጋር በመነጋገር የመምህራን ቁጥር እጅግ ብዙ በመሆኑ በአንድ አማራጭ ብቻ ፍላጎታቸውን ማሳካት አይቻልምና የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ መፍትሔ የሚያገኝበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ከዚህ አንጻርም እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመምህራን ችግሮች ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ምን እንደሚመስሉ በከተማ አስተዳደሩ የመምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ ነግረውናል፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ማህበሩ ብዙን ጊዜ የመምህራንን ጩኸት ማስተጋባት እንጂ የትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረቱን ሰርቷል ለማለት ብዙ አያስደፍርም፡፡ አሁን ግን ሀገርን የማጽናቱ ኃላፈነት የመምህሩ በመሆኑ ግዴታቸውን አውቆ እንዲሰራ የማድረግን ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ አንዱ መምህራንን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ምን መሥራት አለባቸው የሚለውን ተግባር በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሥራት ነው፡፡ አሁን ላይ የትምህርት ጥራት ጉዳይ አንገብጋቢና የትምህርት ስብራት ሆኗልና መምህራን ከሁሉም በላይ ይህንን ታሳቢ አድርገው እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ይፈታል፡፡ በተለይም ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች እንደ መምህራን ማህበር በሥልጠና እና መሰል የትምህርት እድሎች ለመሙላት ይሰራል፡፡ በመምህራን አካባቢ የሚታዩ የግለሰብ ችግሮችንም በክትትል ይፈታል፡፡ በተለይም የክፍለ ጊዜ ብክነት፤ ቸልተኝነት፤ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት ለተማሪው በቂ ጊዜ አለመስጠትን የመሳሰሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለማድረግም ይጥራል፡፡ ይህን እንዲያደርጉ ስናስገድድ ለመምህራን መደረግ ስላለበትም መብትና ጥቅማቸው በመታገል የግድ ነው፡፡ ከዚህ አንጻርም ከአሏቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል ዋና ዋና የሚባሉትን ለመመለስ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ለሁሉም መምህራን ባይሆንም መፍትሔ የተገኘባቸው ተግባራት እንዳሉም ጠቅሰዋል።

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋነኛ ጥያቄ ተደርጎ የሚወሰደው የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ሲሆን፤ ከተማዋ በርካታ ሕዝቦችን አቅፋ የምትኖር በመሆኗ ቤት የሌለው መምህር እንዳይፈተን ብዙ አማራጮችን በመጠቀም መፍትሔ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ተግባርም በመጠኑ ለተወሰኑ መምህራን እፎይታን ሰጥቶ ያለፈ ነው፡፡ ለአብነት መምህራን በዝቅተኛ ዋጋ ተከራይተው ለመኖር ይረዳቸው ዘንድ በ2009 ዓ.ም አምስት ሺህ መምህራን ኮንዶሚኒየም ቤቶችን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ከዚያም አልፎ በ2014 ዓ.ም መምህራኑ ከኪራይ ተላቀው ቤቱን በራሳቸው ስም እንዲያዘዋውሩት እድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን አንዳንድ ቤቶች በተለያየ ምክንያት ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደነበር ተደርሶባቸዋል፡፡ ችግሮቹ መምህሩ ቤቱን ከተረከበ በኋላ ሥራውን መልቀቅ፤ ቤቱን እንደ ያዘው ወደ ውጭ ሀገር መሄድና መሰል ተግባራት መፈጸማቸው ነበሩ። ስለሆነም ምንም ያልተጠቀሙ መምህራን እያሉ ያለ አግባብ ቤቱን የያዙት መጠቀም ስለሌለባቸው ቤቱን ከእነርሱ በመውሰድ በ2016 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ለ435 መምህራን በእጣ እና ችግሮቻቸው ከፍተኛ የሆኑትን መምህራን በመለየት በቀጥታ እንደተላለፍ ተደርጓልም ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል፡፡

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 33ሺህ መምህራንን ይዞ ለሁሉም የመኖሪያ ቤት ምላሽ በአንድ ዓይነት አማራጭ መስጠት አዳጋች እንደሚሆን የጠቀሱት አቶ ድንቃለም፤ በመምህራን ማህበር በኩል የተለያዩ አማራጮችን የመጠቀም ሥራዎች እንዲከናወኑ ሰነድ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ ከሰነዱ ውስጥ ውሳኔ የተላለፈባቸውና ወደ ተግባር የተገባባቸው ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ከተሠሩት ተግባራት መካከልም አንዱ መምህራንን ማህበር ማደራጀት የሚለው ሲሆን፤ 23ሺህ437 መምህራን በ264ማህበራት እንዲደራጁ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ቅድሚያ ቆጥበን ወደ ሥራው እንገነባለን ያሉ 96 ማህበራት መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የመደራጀቱ ሥራ ብዙ መልሶችን የሚፈልግ እንደነበር የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ፤ እንደ መምህራን ማህበር ለዚህም ችግር መፍትሔ እንዳገኙ ያስረዳሉ። ለአብነትም መምህሩ ሲቆጥብ በምን ያህል ፐርሰንት እንደሚሆን የተቀመጠው በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ይህም ብዙዎችን የእድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን፤ እንደ ሌላው የቤት ቆጣቢ 70 በመቶ ቆጥቦ ሌላውን ከባንክ የሚበደር አይደለም፡፡ 30 በመቶ ቆጥቦ 70 በመቶው ከባንክ በሚገኝ ብድር እንዲሠራ የተመቻቸበት ነው፡፡ ከባንክ የሚገኘው ብድር ተመጣጣኝነት፤ የእፎይታ ጊዜ የሚታይበትም እንዲሆን የተቀመጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሌላው ለመምህራኑ የተመቻቸ ሁኔታ የተፈጠረበት ተግባር ቆጥበው ይደራጁ ሳይሆን ተደራጅተው ይቆጥቡ የሚለው ውሳኔ ነው፡፡ ይህ እድል ለመምህራኑ አዲስና የቤት የማግኘት መብታቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑንም አክለዋል፡፡

እንደ አቶ ድንቃለም ማብራሪያ፤ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሌላው በመምህራን በኩል የሚነሳው ጥያቄ የትራንስፖርት ጉዳይ ሲሆን፤ መምህራን ማህበሩ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሩ እልባት የሚያገኝበትን መንገድ ፈጥሯል፡፡ ይህም መምህራን በነፃ የከተማ አውቶበሶችን እንዲጠቀሙ የተመቻቸበት ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ጡረታ የወጡትን መምህራን ጭምር የሚያካትት ተደርጎ ነው የተፈቀደው። እስከ ዛሬ እነዚህ መምህራን ጡረታ ልክ ሲወጡ መታወቂያቸውን እንዲመልሱ ደረግ ነበር፡፡ ሆኖም ያሉበት ሁኔታ በግልጽ የሚታይ ነውና ችግራቸውን ለመጋራት ሲባል መታወቂያቸውን ሳይመልሱ በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

የመምህራን ሌላኛው ጥያቄ የደሞዝ እርከንን የሚመለከተው ነው፡፡ 18 ዓመትም ሆነ 40 ዓመት ያገለገለ መምህር በእኩል ደረጃ ይፈረጃል፡፡ ይህ ደግሞ ከታች ያለውንም ሆነ ብዙ ያገለገለውን መምህር የሚያነሳሳ፤ ሙያውን ፈልጎ የሚያገለግል አያደርገውም።

ይልቁንም ለዚህ ደሞዝማ አልገባም የሚል እሳቤ ውስጥ ይከተዋል፡፡ በመሆኑም ለእያንዳንዱ ሥራ የእርከን ማሻሻያ ያስፈልገዋል፡፡ ብዙ ያገለገሉ መምህራንም ዋጋቸው እውቅና ሊሰጠው ይገባል። በአነስተኛ ደሞዝ ጡረታ ወጥተው በብዙ እየተሰቃዩ ነው፡፡ በአገለገሉበት ልክ ደሞዛቸውም እያደገ ሄዶ ጡረታ ሲወጡ አቅም ሊፈጠርላቸው ግድ ነው። በዚህም መምህራን ማህበሩ የዘወትር ጥያቄው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

መምህራን ችግሮቻቸው ብዙ ናቸውና ዋና ዋናዎቹ መፍትሔ እንዲያገኙ ይፈለጋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ነፃ ሕክምናን የሚያገኙበት ሁኔታን መፍጠር አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንጻርም ለመምህራን ሕክምና አገልግሎት የሚውል ሆስፒታልና ሁለገብ ሕንጻ ለመገንባት እየተሠራ ነው፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደር ለመምህራን ማህበሩ 3,600 ካሬ ሜትር ቦታ የተሰጠ ሲሆን፤ መሠረቱ ወጥቷል። ይህም ከከተማ አስተዳደሩ ባደረገው 50 ሚሊዮን ብር እየተከናወነ መሆኑን አቶ ድንቃለም አስረድተዋል።

ሆስፒታሉ ሰባት ወለል ከፍታ ያለው ሲሆን፤ ይህንን ይደጉማል የተባለለት ሁለገብ ሕንጻው ደግሞ ዘጠኝ ወለሎች እንዲኖሩት ተደርጎ ዲዛይኑ ተሰርቷል። ሁለገብ ህንጻው የሬዲዮ ስቴሽን፤ የጥናትና ምርምር ማዕከልና ቤተ መጻሕፍት ያለው እንዲሁም ለቢሮ የሚከራዩ ሕንጻዎችን ይይዛል፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ የፋይናንስ ችግር እንደገጠማቸውና ለዚህም መፍትሔ እያፈላለጉ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። አንዱ መምህራን የራሳቸውን ዐሻራ እንዲያሳልፉ እድሉ እየተመቻቸ እንደሆነና ሥራው ከአመራሮች እንደተጀመረም ጠቁመዋል፡፡

ግንባታው ሰፊና ሀገራዊ በመሆኑ በቀላሉ የሚሠራ አይደለም፡፡ ከፍተኛ በጀትን ይጠይቃል። ስለሆነም መምህራን ማህበሩ የተለያዩ አማራጮችን እያፈላለገ ይገኛል፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደርም ውሳኔ ተላልፎልን በትብብር የመሥራት አማራጮችን ጨምሮ በፍጥነት ሕንጻውን ለማጠናቀቅ ይሠራልም ብለዋል። ይህ ሆስፒታል እንደ ከተማ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ብዙ ትርጉም ያለው እንደሆነ የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በኢኮኖሚው ብቻ ቢታይ ከመምህራን አልፎ ማህበረሰቡን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲታከሙ እድል የሚፈጥር ስለመሆኑ ያነሳሉ። መምህራንም ቢሆን ለሕክምና የሚያወጡትን ለሌሎች ግልጋሎቶች እንዲጠቀሙበት ያግዛቸዋልና ጥቅሙን ተረድቶ ለተፈጻሚነቱ ሁሉም ቢተባበር ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

እንደ መምህራን ማህበር ለመምህራን የሚደረጉ ማንኛውም ድጋፍ ከእርሱ ጀርባ ያሉትን ተማሪዎች፤ ወላጅና ቤተሰቦች እንዲሁም ሀገርን ታሳቢ ያደረገ ነውና መምህራን እየተጎዱ የሚቀጥሉበት ሁኔታ በምንም መልኩ አይፈጠርም፡፡ ለዚህም መብትና የጥቅማጥቅም ጥያቄያቸውን ለመመለስ ማህበሩ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

ጽጌሬዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You