“የትግራይ ክልል የሚያስፈልገው ሰላም ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- መንግሥት በተለያዩ ችግሮች ተወጥሯል፤ የሚያግዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን ነው በሚል ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ አሉ። ይህ የተሳሳተ አካሄድ ነው የትግራይ ክልል የሚያስፈልገው ሰላም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ የትግራይ ሕዝብ ጦርነት ፈጽሞ አይፈልግም። ሆኖም የዓለምን ሁኔታና የዘመኑን ውጊያ ባለመገንዘብ፣ መንግሥት በተለያዩ ችግሮች ተወጥሯል፤ የሚያግዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን ነው በሚል ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ አሉ። ይህ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ ትግራይ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ችግሮችን በውይይትና በንግግር መፍታት ነው ብለዋል።

መንግሥት አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ ጦርነት እንዳይገባ አሁኑኑ የሰላም ሚናችሁን ተወጡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

መልማት ነው ፍላጎታችን። ሁሉም ሕዝብ ማወቅ ያለበት ጦርነት አያስፈልግም። ትግራይ ክልልን ጨምሮ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሚና ማበርከት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት ለትግራይ ሕዝብ እፎይታ አምጥቷል። የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን በየቀኑ ከማጣት ታድጓል። ለኢትዮጵያ ሕዝብና ብሎ ለተዋጉት ኃይሎች ዕድል ይሰጣል የሚል አዲስ ባህል መፍጠሩን ተናግረዋል።

በክልሉ አገልግሎትን በሚመለከት ቴሌኮም፣ ባንኮች፣ አየር መንገድና ሌሎችም አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ መጀመራቸውን ገልጸው፤ የተፈናቀሉ ሰዎችን በሚመለከት ራያ መቶ በመቶ ፀለምትም ተመልሰዋል። ቀሪ ወልቃይት ያልተመለሱ አሉ፤ መንግሥት ያልተመለሱ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የጸና አቋም አለው ብለዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋምና ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀልም በፍጥነት መፈጸም አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ጥቅሙ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጭምር ነው። የፌደራል መንግሥት ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በሰላም የመፍታት ፅኑ አቋሙን በተደጋጋሚ ማሳየቱንም አስታውቀዋል።

በጌትነት ምሕረቴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You