አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በጅምር የቆሙ የጤና ተቋማት እንዲጠናቀቁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ። ለረዥም ዓመት ያገለገሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ወደ አጠቃላይ ሆስፒታልነት እንዲያድጉም ጠይቀዋል።
ምክር ቤቱ ትናንት መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት፣ አባላቱ ለጤና ሚኒስትር ባቀረቡት ጥያቄ ፤ በርካታ ከፍተኛ የጤና ተቋማት በጅምር ቆመዋል። በዚህም የተነሳ በርካታ ዜጎች ሊያገኙ የሚገባቸውን የጤና አገልግሎት እያገኙ ባለመሆኑ በተደጋጋሚ ቅሬታዎች እያቀረቡ ይገኛሉ ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል በሀረሪ ክልል የሚገኘው የሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንዱ እንደሆነ አመልክተው ፤ ከዓመታት በፊት የሆስፒታሉ የማስፋፊያ ግንባታ ተጀምሮ 80 በመቶ ከደረሰ በኋላ ግንባታው መቋረጡን አስታውሰዋል። በዚህም ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ባልተጠናቀቀው ማእከል ውስጥ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
ሆስፒታሉ ለምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ትልቁ ሪፈራል ሆስፒታል ነው ፤ በዓመት ሶስት መቶ ሺህ ለሚደርሱ የካንሰር ህሙማን አገልግሎት የሚሰጥ እንደሆነ ጠቁመው ፤ አገልግሎቱን ከጂቡቲ፤ ከመቋዲሾ፤ ከሀርጌሳ እና ከፑንት ላንድ ለሚመጡ ታካሚዎች እንደሚሰጥም ገልጸዋል። በተመሳሳይ በክልሉ እየተገነባ ያለው የላብራቶሪ ማእከልም ግንባታው 80 በመቶ ደርሶ መቆሙን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በቦዲቲ ከተማ አስተዳደር በጤና ሚኒስቴር በኩል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በ2008 ዓ.ም ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ፣ የህንጻ ግንባታ ቢጀመርም እስካሁን አለመጠናቀቁን አንስተዋል። ግንባታው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብበትም ሊጠናቀቅ አለመቻሉን የምክር ቤቱ አባላቱ ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ክልል የባኮ ሆስፒታል ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል ይደግልን ጥያቄ በአካባቢው ባለው ማህበረሰብ በተደጋጋሚ መነሳቱን ያስታወሱት አባላቱ ፤ የአካባቢው ነዋሪ ለወባና ተያያዥ በሽታዎች በስፋት ተጋላጭ መሆኑ ፤ ከዛም ባለፈ ሆስፒታሉ በርካታ ወረዳዎችን የሚሸፍን ከመሆኑ አኳያ የማህበረሰቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ማግኘት እንዳለበት አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን አብዛኛው ነዋሪ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለህክምና እየተንቀሳቀሰ ለበርካታ እንግልቶችና ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ ይገኛል። እንዲህ አይነት ችግሮች ከተጠቀሱትም ባለፈ በሌሎችም አካባቢዎች እንዳሉ አባላቱ አንስተው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ ጥያቄዎቹ ተገቢ ናቸው። ከዚህ ቀደምም በተለያየ አግባብ ቀርበዋል። በጅምር የቆሙ የጤና ተቋማትን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት እየሠራባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል ናቸው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ያሉት አብዛኛዎቹ ትልልቅ ሆስፒታሎች ከሃምሳ ዓመት በላይ የቆዩ ናቸው ፤ እነሱን የማደስና የግብዓት የማሟላት ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ ፤ባለፈው ሩብ ዓመት 140 የጤና ኤክስቴንሽን የሚሰጡ ኬላዎች ወደ ሥራ ገብተዋል። አንድ ሺህ 986 ጤና ኬላዎችን ከጤና ጣቢያዎች ጋር በማቀናጀት ደረጃቸውን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል
ግጭት በነበረባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የነበሩ 251 የህክምና ተቋማትን ቀድሞ ከነበሩበት በተሻለ መልኩ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሰራ ነው ፤ ከዚህ በተጨማሪም የላብራቶሪ አገልግሎትና የመድሃኒት አቅርቦትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2017 ዓ.ም