ማሻሻያው መዋቅራዊ ሽግግር ለመገንባት ያለመ ነው

አዲስ አበባ፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጊዜያዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በመገንባት ተከታታይና ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግርና ወደ ብልጽግና የሚደረግ ጉዞን በማስመልከት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር ትናንት ውይይት ተደርጓል፡፡

በዚሁ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጊዜያዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በመገንባት ተከታታይና ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አዲስና የ25 ዓመት የኢኮኖሚ ሽግግር እቅድ ማዘጋጀቷን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ይህ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥና በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና አስቻይ ሁኔታዎችን የሚያካትት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ጠንካራ ምጣኔ ሀብትና ልማትን እውን ማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የፋይናንስ፣ የግሉ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የልማት አጋሮች ትብብርን ማጠናከሩን አንስተዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ የኢኮኖሚ ሽግግር ትግበራው የሁሉም አጋር አካላት ጠንካራ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ለዚህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የዓለም አቀፍ አጋር ተቋማትና ሌሎችም አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳለጥ የልማት አጋሮች ትብብር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት እውን ለማድረግ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ጨምሮ እየተገበረች የምትገኘው የልማት መርሀ ግብሮችን አንስተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 60 ዓመታት የሄደችበትን የኢኮኖሚ ጉዞና የፖሊሲ አተገባበር በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓት ለውጦች ላይ በማተኮር ሰፊ ማብራሪያ ያለው ፅሁፍ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በእነኝህ ዓመታት የካፒታሊስት፣ የዕዝ እና የጥምር ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በተለያዩ ሥርዓቶች መተግበሯን አስታውሰው፣ ከለውጡ በኋላ ወደ ፕራግማቲክ ካፒታሊዝም እየተሸጋገረች መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በስድስት አስርት ዓመታት ጉዞዋ ያስመዘገበችው የኢኮኖሚያዊ እድገት ከሌሎች አቻ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ኋላ ቀር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ከለውጡ በኋላ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራና ሌሎችም መንግሥት በቁርጠኝነት የወሰዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን ከነበረችበት ችግሮች እያላቀቋት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ ለአብነትም በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በዲጂታላይዜሽንና በሌሎችም ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግቧል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ብቻ በገጠር መሬት ልማት፣ በሜካናይዜሽን፣ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች የግብርና ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በመድረኩ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሀ ግብርና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ኅዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You