አዲስ አበባ፡– የቀድሞ ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የማስገባት ሥራ በዚህ ሳምንት የሚጀምር መሆኑን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ክልሎች 371 ሺህ 971 የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መለየታቸውንም አስታውቋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን የኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ትናንት መግለጫ ሰጥተዋል።
ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በዘላቂነት በማቋቋም ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል የሀገሪቱ የሰላም የዴሞክራሲና የልማት አካል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፤ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀልና በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ ትኩረት የሚሻና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በዚህም መሰረት መንግሥት በመደበው አንድ ቢሊዮን ብር እና ከአጋሮች በተገኘ 60 ሚሊዮን ዶላር በመጀመሪያው ምእራፍ በትግራይ ክልል የሚገኙ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ ይጀመራል ብለዋል።
በክልሉ በመቀሌ፣ እዳጋ ሀሙስ እና ዓድዋ ሶስት ማዕከላት ተለይተዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በመቀሌ ማዕከል በዚህ ሳምንት 320 የቀድሞ ታጣቂዎችን መቀበል እንጀምራለን በማለት ገልጸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎች ከዛሬ ጀምሮ በስፍራው የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ስር ሂደቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን አባላት በሚታዘቡበት ለመከላከያ ሠራዊት ትጥቃቸውን ማስረከብ ይጀምራሉ ብለዋል።
በዚህም በቀጣይ አራት ወራት 75 ሺህ የቀድሞ የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ በዘላቂነት በማቋቋም ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ ይከናወናል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በሁለት ዓመታት ውስጥም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ 371 ሺህ 971 የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው በዘላቂነት ለማቋቋም ታቅዷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
መንግሥት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተውና የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማስቻል በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 525/2015 እና በተሻሻለው ደንብ ቁጥር 541/2016 መቋቋሙ ይታወቃል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም