አዲስ አበባ፡- በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ለማጠናከር ህብረ ብሔራዊነትን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማና በጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤቶች አዘጋጅነት 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የፓናል ውይይት ትናንት ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር በማድረግ ህብረ ብሔራዊ አንድነት መገንባት ወሳኝ ነው፡፡
አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የኢኮኖሚ፣የባህል፣የፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች የስህበት ማዕከል ናት ያሉት አፈ ጉባኤዋ፣የህብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዋና ከተማ ናት ብለዋል፡፡
ከተማዋ በዙሪያዋ ከሚገኙ ክልሎችና ከተሞች ጋር ሥነ ምህዳራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ግንኙነት እንደምታደርግ ጠቅሰው፤ በዓላትን በጋራ በማክበር እህትማማችነትና ወንድማማችነትን ለዓለም ማስመስከር መቻሏንም ገልጸዋል፡፡
ብዝሃነታችን ጸጋችን፣ባህሎቻችን መድመቂያችንና ልዩ ልዩ መሆናችን የጠንካራ አንድነት ምክንያት መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ፣እየተገነባ ያለውን እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም በጽኑ መሰረት ላይ በማቆም ጠንካራ ሀገር መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን በበኩላቸው፤ አዲስ አበባና የሸገር ከተሞች በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሰላም፣ በፍቅር በጋራ የሚኖሩባቸው በመሆኑ የአብሮነት ማሳያ ከተሞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአንድነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ብዝሃነት የተረጋገጠባት ሀገር ናት ያሉት አፈ ጉባኤዋ፣ኢትዮጵያን የሚመስል ሀገር ለመገንባት እየተሰራ ሲሆን፤ ለስኬቱም የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ድርሻ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ትናንት የነበሩ ጀግኖች ያለምንም ልዩነቶች ደምና አጥንታቸውን አፍሰው የዛሬዋን ኢትዮጵያ ለትውልዱ ማስረከባቸውን ጠቅሰው፤ሉዓላዊነቷን በመጠበቅ ምሳሌ የሆነች ሀገርን በመገንባት በደማቸው ታሪክ መጻፋቸውን አውስተዋል፡፡
የተገኘው ድል በመላው ኢትዮጵያዊያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተሳትፎ መሆኑን በመግለጽ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድ የሕግ ጥላ ሥር በመሰባሰብ እውነተኛ አንድነትና ወንድማማችነት በጋራ መኖር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ዓለም ኢትዮጵያ መሆናችንን ያውቃል፤ ኢትዮጵያ ደግሞ የሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ምልክት ናት ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩ ቢሆንም፤ የጋራ በሆኑ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የተገነባ ነው ብለዋል፡፡
ሀገራዊ አንድነትን በመፍጠር የሀገርን ብልጽግና ለማፋጠን መግባባት አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ፤ በህብረ ብሔራዊ አንድነት ሀገርን ለመገንባት ምርጫ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ መግባባት በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ እንደሚከበር መገለጹ ይታወሳል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም